አንዳንድ የእስር ቅጣቶች ከመቶ እስከ ሁለት መቶ ዓመት ለምን ይረዝማሉ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሰዎች ለሚፈጽሟቸው የተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች በፍርድ ቤት የተለያዩ ቅጣቶች ይወሰንባቸዋል። በተለይ የእስር ፍርድ የተለመደው አይነት ቅጣት ሲሆን ይህም ከጥቂት ቀናት አስከ ዓመታት ሊደርስ ይችላል።
አንዳንድ ጊዜ ጥፋተኞች ሰው በየትኛውም ሁኔታ በዚህ ዓለም በህይወት ሊቆይበት ከሚችለው ዓመት በላይ ፍርድ ሲሰጥ ለብዙዎች ግራ ያጋባል።
ለምሳሌ አንድ ጥፋተኛ ለፈጸመው ወንጀል "የሁለት መቶ ዓመት የእስር ቅጣት ተወሰነበት" የሚል ዜና ሲሰሙ ምን አይነት የቅጣት ውሳኔ ነው? በማለት መጠየቅዎ አይቀርም።
እንደዚህ ዓይነት ዜናዎችን በተደጋጋሚ እንሰማለን። በፈረንጆቹ የካቲት ወር መጀመሪያ አካባቢ በአሜሪካ ሆዜ አልቫሬዝ ፈርናንዴዝ የተባለ ሰው የሁለት መቶ ዓመት የእስር ቅጣት ተፈርዶበታል።
ይህ የ58 ዓመት ጎልማሳ አንዲት የስድስት ዓመት ሕጻንን ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላት ድረስ ባደረሰባት ተደጋጋሚ ጾታዊ ጥቃት ነበር የ200 ዓመት እስር የተፈረደበት።
በዚህ ቅጣት መሰረት ታዲያ ይህ ሰው የእስር ቅጣቱን ሲጨርስ እድሜው ሁለት መቶ ሃምሳ ስምንት ይሆነዋል ማለት ነው።
ይኹን እንጂ በዓለም ላይ የሰው ልጅ የእድሜ ጣርያ እንኳን ሁለት መቶ ሊሞላ 100 የሞላቸው ቢቆጠሩ ከሁለት እጅ ጣት በላይ አይሆኑም። ታዲያ የሰው ልጅ ኖረ ከተባለ ቢበዛ ቢበዛ 100 እና 120 ዓመት ነው።
ስለዚህ ጥፋት የተገኘበትን ሰው በመቶዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ወይንም አንዳንዴ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት ይፈርድባቸዋል።
ታዲያ ለዚህ ነው ብዙዎች፤ ሰዎች ለፈጸሙት ከባድ ወንጀል ሊፈጽመት የማይችሉትን ቅጣት መወሰን ውጤቱ አልታይ ሲላቸው በአስፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ የሚያነሱትል።
ይግባኝ የሌለው እድሜ ልክ ቅጣት ቢፈርዱባቸው በቂ አይደለምን?
የቅጣት ዓይነቶች በተለያዩ አገራት ልዩነት አላቸው። አንዳንዱ የሞት ቅጣት ሌላው ደግሞ የእድሜ ልክ እስራት እንዲሁም ሌሎች የቅጣት አይነቶች በጥፋት ፈጻሚዎች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆኑ ፍርድ ይሰጣሉ።
የረዥም ዓመታት እስር ፍርድ ግን በብዛት የሚሰማው ከአሜሪካን ነው። በዚህች አገር በአንድ ሰው የተሰሩ የተለያዩ ወንጀሎች ክብደት እንዲያገኙ ለማድረግ ሲባል የረዥም ዓመታት የቅጣት ውሳኔ በፍርድ ቤት ይሰጣል።
ይህ ምን ማለት ነው?
በአጭር እና ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስቀመጥ ጥፋት የተገኘበት ግለሰብ ለፈጸማቸው የተለያዩ ተደራራቢ ወንጀሎች ለእያንዳንዱ ወንጀል በተናጠል ቅጣት ስለሚጣልበት ነው የቅጣት ዓመታቱ ግለሰቡ በምንም ዓይነት ሁኔታ በህይወት ከሚቆይበት በላይ በጣሙን የተጋነነ የሚሆነው።
በምሳሌ እንየው፡
ሆዜ አልቫሬዝ በሕጻኗ ላይ ተደጋጋሚ ጾታዊ ጥቃት በመፈፀም ወንጀል ቅጣት የተፈረደበትን ግለሰብ ነው። ይህ ግለሰብ የስድስት ዓመቷን ሕጻን ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላት ድረስ ጾታዊ በደል አድርሶባታል።
በዚህም የተከሰሰበባቸው የተለያዩ ወንጀሎች አስራ ዘጠኝ ነበሩ።
ስለዚህ ይህ ሰው በአስራ ዘጠኙም ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ለእያንዳንዱ ክሶች ለየብቻ የቅጣት ዓመታት ተፈርዶበት እነዚህ የወንጀል ቅጣቶች ሲደማመሩ ሁለት መቶ ዓመት ሊሆኑ በመቻላቸው ነው ከፍተኛው የእስር ቅጣት የተበየነበት።
ነገር ግን አብዛኛውን ጊዜ በተደራራቢ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ፍርድ የተሰጠው ግለሰብ ቅጣቱን በተመሳሳይ ጊዜ እንዲጨርስ ይደረጋል።
ይህም ማለት አንድ ግለሰብ በአምስት የተለያዩ ክሶች ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቶ እያንዳንዱ ጥፋት ሃያ ዓመት ካስፈረደበት ሁሉንም ቅጣቶች በአንድ ጊዜ የሚፈጽም ይሆናል።
ይህም ማለት የእስር ቅጣቱ የአምስቱ ጥፋቶች 20 ዓመታት እስር ተደምሮ አንድ መቶ ዓመት ሳይሆን፤ የሁሉም የእስር ቅጣቶች በአንድ ጊዜ ስለሚፈጸሙ በሃያ ዓመት የእስር ቅጣት ብቻ ፍርዱን ሊፈጽም ይችላል።
"የሚተላለፉ የፍርድ ውሳኔዎች አንድ ሰው እስር ቤት ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንዳለበት ብቻ አይደለም፤ ውሳኔው ለማስተማሪያነት ነው"ይላሉ በካሊፎርኒያ ዩኒቨርስቲ የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ፍራንክሊን ዚም ሪንግ።
በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ የሆኑት አቶ አዲ ደቀቦ በበኩላቸው አገራት እንደዚህ ዓይነት የእስር ቅጣቶችን የሚያስተላልፉት ከተፈጸመው ወንጀል አንጻር የቅጣት ወሰን የሌላቸው ሲሆኑ ነው ይላል።
"የቅጣት ጣርያ ስላልተቀመጠ ሰዎች መኖር ከሚችሉበት እድሜ በላይ ይፈረድባቸዋል" በማለት የሚከተለውን አስረጅ ይጠቅሳሉ።
ከአስራ አምስት ዓመታት በፊት የ191 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው እና በስፔን በተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ላይ የተሳተፉ ወንጀለኞችን 43000 በሚደርስ ዓመት እስር እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል ሲል ይጠቅሳል።
ከዚህ በተቃራኒ ሌሎች አገራት ደግሞ በጣም አጭር የሆነ የእስር ቅጣት አላቸው።
ለምሳሌ በኖርዌይ 77 ሰዎችን ሆን ብሎ የገደለው አንደሬስ ብሬቪክ የተባለው ግለሰብ 21 ዓመት ብቻ ነው የተፈረደበት።
የኢትዮጵያ ሕግስ ምን ይላል?
አቶ አዲ ደቀቦ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ሕግ መሰረት ከፍተኛው የእስር ቅጣት 25 ዓመት ነው። ስለዚህ አንድ ሰው ከ25 ዓመት በላይ በእስራት አይቀጣም።
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ሰው በስድስት የተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥሮ ጥፋተኛ ሆኖ ቢገኝ ለፈጸማቸው ወንጀሎች እያንዳንዱ ተደምሮ ቅጣቱ ውሳኔ እንደሚሰጥ ይናገራል።
ቢሆንም ግን የእነዚህ ወንጀሎች ድምር ከ25 ዓመት እስካልበለጠ ድረስ ነው።
ድምሩ ከ25 ዓመት በልጦ ሃምሳ ወይም ስድሳ ዓመት ቢደርስ ግን ታራሚው ግለሰብ የእስር ጊዜውን እንዲፈጽም የሚደረገው ለ25 ዓመታት ብቻ መሆኑን የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ።
ሌሎች አገሮች ግን ድምሩ የቱንም ያክል ቢሆን እና ከግለሰቡ እድሜ ቢበልጥ እንኳ ቅጣቱን እንዲፈጽም ሊፈረድበት ይችላል።
እንደ ሕግ ባለሙያው ገለጻ አንድ ግለሰብ ይህን ያክል ረዥም ዓመት ሊፈረድበት የሚችለው ሌላኛው ምክንያት ይህ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ታራሚ ከእስር ቤት በይቅርታ ወጥቶ ወደ ኅብረተሰቡ እንዳይቀላቀል ለማድረግ ነው።














