ኢሰመኮ፡ በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ እንደሚያሳስበው ገለፀ

የኢሰመኮ አርማ

የፎቶው ባለመብት, EHRC

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን [ኢሰመኮ] በኦሮሚያ ክልል ያለው የእስረኞች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ ያሳስበኛል ብሏል።

ኮሚሽኑ ክትትል ባደረገባቸው ፖሊስ ጣብያዎች ዕድሜያቸው ከ 9 እስከ 18 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት አካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ጋር ተቀላቅለው በእስር ላይ እንደሚገኙ አመልክቷል።

በፖሊስ ጣቢያዎቹ ብዙ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ “በወቅታዊ ሁኔታ” የተጠረጠሩ ናቸው በሚል መታሰራቸውን፣ ከእነዚህም አብዛኛዎቹ ምርመራ ሳይጀመርባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሕግ ከተቀመጠው ጊዜ በላይ ታስረው እንደቆዩ የሚያመላክቱ አሳማኝ መረጃዎች ቀርበዋል ይላል መግለጫው።

በተጨማሪም በብዙ ፖሊስ ጣቢያዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ ባለመገኘቱ ምክንያት “የአያስከስስም ውሳኔ” የሰጠባቸው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መለቀቅ የነበረባቸው ተጠርጣሪዎች ዋና ተሳታፊ (ኮር) ናቸው ወይም በሌላ ወንጀል ይፈለጋሉ በሚል ያለ አግባብ ታስረው እንዲቆዩ የሚደረጉ መሆኑን ተረድቻለሁ ብሏል።

በ21 ፖሊስ ጣብያዎች የተደረገ ክትትል

የሰብአዊ መብት ተቋርቋሪው ኮሚሽን ከህዳር11 ቀን 2013 ዓ.ም. እስከ ጥር 04 ቀን 2013 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሉ ያለውን የእስረኞችን አያያዝ ሁኔታ በተመለከተ በ21 ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል ማድረጉን በመግለጫው አትቷል።

ኮሚሽኑ፤ በተለይም የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በቁጥጥር የዋሉ ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ ሌሎችም “በወቅታዊ ሁኔታ” የተያዙ የሚባሉ ብዛት ያላቸው እስረኞች የሚገኙባቸውና ተደጋጋሚ ቅሬታዎች ከሚቀርቡባቸው መካከል የተመረጡ ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ክትትል አድርጊያለሁ ብሏል።

በክትትሉም ከእስረኞች እና የፖሊስ ጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ጋር መወያየቱን፣እንዲሁም የክትትሉን ግኝቶች ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የክልሉ የሕግ አስከባሪ እና የአስተዳደር አካላት በማሳወቅ ምላሽ እንዲሰጥባቸው መጠየቁን ኮሚሽኑ አሳውቋል።

ኢሰመኮ፤ በጎበኛቸው የፖሊስ ጣቢያዎች በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢና በአፋጣኝ ሊሻሻል የሚገባው ነው ይላል።

በፖሊስ ጣቢያዎቹ ብዙ ሰዎች ያለ ፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ተይዘው የታሰሩ፣፣ ከነዚህም አብዛኛዎቹ ምርመራ ሳይጀመርባቸው እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በሕግ ከተቀመጠው ጊዜ በላይ የታሰሩ ስለመኖራቸው አሳማን ማስረጃ ማግኘቱን በመግለጫው ላእ አመልክቷል።

በተጨማሪም በበርካታ ፖሊስ ጣቢያዎች ዐቃቤ ሕግ በቂ መረጃ ባለመገኘቱ ምክንያት “የአያስከስስም ውሳኔ” የሰጠባቸው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት መለቀቅ የነበረባቸው ተጠርጣሪዎች በሌላ ወንጀል ይፈለጋሉ በሚል ያለ አግባብ ታስረው እንዲቆዩ መደረጋቸውን መረዳቱንም በመግለጫው ላይ አስፍሯል።

የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎች ኃላፊዎች “በወቅታዊ ሁኔታ” ተጠርጥረው የታሰሩ እስረኞች ጉዳያቸው የሚታየው በዞን እና በወረዳ ደረጃ በተቋቋሙ “የፀጥታ ምክር ቤቶች” መሆኑን ይገልጻሉ ይላል።

ይህ አሰራር ብዛት ያላቸው ተጠርጣሪዎችን በሕግ ከመዳኘት ይልቅ የፖለቲካ (የአስተዳደራዊ) ውሳኔዎች ሰለባ እንዲሆኑ አድርጓል ሲል የኢሰመኮ መግለጫ ያትታል።

ኢሰመኮ በጎበኛው ፖሊስ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ እስረኞች ድብደባ እንደተፈፀመባቸው እና ጉዳት እንደደረሰባቸው አይቻለሁ ብሏል።

በተወሰኑ ቦታዎች “የኦነግ ሸኔ” አባል ወይም ደጋፊ ናቸው በሚል የሚፈለጉ “ልጆቻችሁን አቅርቡ” በማለት አባት ወይም እናትን የማሰር፤ “ባልሽን አቅርቢ” በማለት ሚስትን የማሰር ተግባር እንደሚፈጸም ከተለያዩ ታሳሪዎች አሳማኝ ምስክርነቶችን መቀበሉን በመግለጫው ገልጿል።

ክትትሉ በተደረገባቸው በሁሉም ፖሊስ ጣቢያዎች ሴት እስረኞች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የተወሰኑት እድሜያቸው ከ 5 ወር አስከ 10 ዓመት የሚሆናቸው ሕጻናት ልጆቻቸውን ይዘው የታሰሩ ናቸው ይላል የኮሚሽኑ ሪፖርት።

አብዛኛዎቹ ፖሊስ ጣቢያዎች ንፅህናቸው ያልተጠበቀ፣ በጣም የተጨናነቁ እንዲሁም የምግብ፣ ውሃና መፀዳጃ አቅርቦት የሌላቸው መሆኑን ታዝቢያለሁ ብሏል ኮሚሽኑ።

የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተጠቀሱትን የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በተመለከተ ከኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር የምርመራ ቡድን በማዋቀር የማጣራት ሥራ መሥራቱን ጠቅሶ ግኝቶቹን በማስተባበል ዝርዝር ምላሽ ሰጥቷል ይላል የኢሰመኮ መለግጫ።