አምባሳደር ፍጹም ምርጫው 'ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም' ላሉት ሴናተሮች ምላሽ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Eth News Agency
ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ አስፈጻሚው ምርጫ ቦርድ ገለልተኛ መሆኑን እና መንግሥት ምርጫው ዲሞክራሲያዊ እና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገለጹ።
አምባሳደሩ ይህንን የገለጹት ኢትዮጵያ ከሳምንታት በኋላ የምታካሂደው ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን አያሟላም ላሉት ሴናተሮች ምላሽ በሰጡበት ደብዳቤያቸው ነው።
አምስቱ ሴናተሮች ምን ነበር ያሉት
አምስት የአሜሪካ ሴናተሮች ከሳምንታት በኋላ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ አሁን ባለበት ሁኔታ ነጻ፣ ሚዛናዊ እና ግልጽ ሆኖ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎች አያሟላም ብለው ነበር።
ሴናተሮቹ ይህን ያሉት በቅርቡ የፕሬዝደንት ጆ ባይደን አስተዳደር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው ለተሾሙት አምባሳደር ጆፍሪ ፌልትማን በጻፉት ደብዳቤ ነው።
ሴናተሮቹ ቤንጃሚን ኤል ካርዲን፣ ቲም ኬይን፣ ጃኪ ሮስን፣ ኮርይ ኤ ቡከር እና ኤድዋርድ ጄ ማርኬይ ስለመጪው አገራዊ ምርጫ፣ ስለትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ስፍራዎች ስላሉ ግጭቶች ለተሿሚው ልዩ መልዕክተኛ መልዕከታቸውን አጋርተው ነበር።
አምባሳደር ፍጹም ለሴናተሮቹ በሰጡት ምላሽ፤ መጪው አገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሽግግር ውስጥ ታሪካዊ ነው ካሉ በኋላ፣ ምርጫውን የሚያስፈጽመው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገሪቱ ታሪክ ገለልተኛው ነው ብለዋል።
አክለውም መንግሥትም ምርጫው ነጻ እና ግልጽ እንዲሆን ያላሰለስ ጥረት አድርጓል እያደረገም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
አምባሳደሩ ለሴናተሮቹ በጻፉት ደብዳቤያቸው በቀጣዩ ምርጫ ለመሳተፍ 47 ፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከ8ሺህ በላይ እጩዎች መመዝገባቸውን አስታውሰው ከምርጫ ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመግባባቶችን የፍትሕ አካሉ በገለልተኛነት ይመለከታቸዋል ብለዋል።
ዓለም አቀፍ የምርጫ ታዛቢዎችም ምርጫውን እንዲታዘቡ ጥሪ እንደቀረበላቸውም ገልዋል።
በየትኛውም አገር የሚካሄድ ምርጫ ፍጹም ነው ተብሎ አይጠበቅም ያሉት አምባሳደር ፍጹም፤ ስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ መድበለ ፓርቲ ስርዓት ያሸጋግራታል ብለን እናምናለን ብለዋል።
አምባሳደሩ በደብዳቤያቸው ላይ ባነሷቸው ጉዳዮች ላይ ለመወያየት ዝግጁ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጽዋል።
ትግራይ
አምስቱ ሴናተሮች በትግራይ ክልል በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ የሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው በርካቶችም ተፈናቅለው እንደሚገኙ በደብዳቤያቸው አትተው፤ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲረጋገጥ፣ የኤርትራ ጦር ከትግራይ እንዲወጣ፣ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች በገለልተኛ አካል እንዲመረመሩ ዲፕሎማሲያዊ አማራጮችን እንዲጠቀሙ እናበረታታዎታለን ብለዋል።
አምባሳደር ፍጹም በበኩላቸው፤ በትግራይ ቀውስ የተከሰተው ሕወሓት በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ መሆኑን ጠቅሰው፤ መንግሥት ዓለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅቶች በመላው ትግራይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያቀርቡ ፈቅዷል ብለዋል።
አምባሳደሩ የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ፈተና ሆኖ የቆየው ተበታትነው የሚገኙት የህወሓት ታጣቂዎች ለራሳቸው ፖለቲካዊ ጥቅም ሲሉ የረድኤት ሠራተኞች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸው ነው ብለዋል።
የኤርትራ ሠራዊት የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ያለፈው የደህንነት ስጋት ስላለባቸው መሆኑን በመግለጽ ከኢትዮጵያ እንደሚወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መናገራቸው ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ የኤርትራ መንግሥትም ጦሩን ከኢትዮጵያ እንደሚያስወጣ ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች
አምባሳደር ፍጹም ተፈጽመው የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚመረመሩ እና ጥፋተኞችን ለሕግ ለማቅረብ መንግሥት ቁርጠኛ ነው ብለዋል። አምባሳደሩ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር አብረው እየሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።












