ትዳራቸውን ያፈረሱ አምስት ቢሊየነሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ ከ27 ዓመታት በኋላ ከሚሊንዳ ጌትስ ጋር መስርተውት የነበረውን ትዳር ለማፍረስ መስማማታችውን ገልጸዋል።
ሁለቱ ጥንዶች የተገናኙት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1980ዎቹ ውስጥ ሚሊንዳ የቢል ጌትስን ማይክሮሶፍት ተቋም በተቀላቀለችበት ወቅት ነበር።
''ከብዙ ማሰብና ግንኙነታችንን ለማሻሻል ከሰራን በኋላ ትዳራችንን ማፍረሱ የተሻለ አማራጭ አድርገን ወስደናል'' ብለዋል በትዊተር ገጻቸው ላይ ባስቀመጡት መልዕክት።
ቢሊየነሮቹ ጥንዶች በ27 ዓመታት የትዳር ዘመናቸው ሦስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፤ በተለያዩ ዘርፎች ድጋፍ የሚያደርገውን 'ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን' አቋቁመዋል።
ድርጅታቸውም የተለያዩ አይነት ተላላፊ በሽታዎችን ለመዋጋትና ለህጻናት ክትባቶችን ለማድረስ በቢሊየኖች የሚቆጠር ዶላር ፈሰስ አድርጓል።
ቢል ጌትስ በፎርብስ መጽሄት መረጃ መሠረት የዓለማችን አራተኛው ቢሊየነር ሲሆን የተጣራ ሀብቱም 124 ቢሊየን እንደሆነ ተነግሯል።
የጥንዶቹ ትዳር ማፍረስ ዓለምን ያነጋገር ትልቅ ዜና ቢሆንም ያልተለመደ ነገር ግን አይደለም። ከዚህ በፊትም በርካታ ቢሊየነር ጥንዶች ትዳራቸውን አፍርሰው ሀብት ንብረታቸውን ተካፍለዋል። እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ጄፍ ቤዞስ እና ማኬንዚ ቤዞስ
የአለማችን ቀንደኛ ሃብታም ጄፍ ቤዞስ እና ባለቤቱ ማክኬንዚ ትዳራቸውን ለማፍረስ የተስማሙት እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ሚያዝያ 2019 ላይ ነበር። ።
ጄፍ ቤዞስ ፍቺውን ለህዝብ ይፋ ያደረገው በቲውተር ገፁ ላይ ሲሆን ጉዳዩም በመስማማት መከናወኑን ጠቅሷል። ፍቺው ግን እንዲሁ በቀላሉ የሚወጡበት አልሆነም። ባለቤቱ የድርሻዋ ነው የተባለውን 35 ቢሊየን ዶላር ተካፍላለች።
35 ቢሊዮን ዶላር ድርሻዋን የምትቀበለው ማክኬንዚን ከዓለማችን ሃብታም ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ያካትታታል።
ይህ ብቻ ሳይሆን ባለቤቷ ከዛሬ 25 አመት በፊት ከመሰረትውና በአለማችን ቁጥር አንድ ከሆነው የኢንተርኔት የችርቻሮ ግብይት ድርጅት አማዞን የአራት በመቶ ድርሻ ይኖራታል።
ቢሊየነሯ ማኬንዚ በአሁኑ ሰአት ልጆቿ በሚማሩበት ትምህርት ቤት ሳይንስ የሚያስተምር ግለሰብ አግብታለች። ቢሊየነሯ የሳይንስ አስተማሪው ዳን ጄዌትን ማግባቷ ይፋ የሆነው 'ጊቪንግ ፕሌጅ' በተሰኘው የእርዳታ ድረ-ገፅ ላይ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሌክ ዊልደንስቲን እና ጆሰሊን ዊልደርስቲን
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 1999 እነዚህ ጥንዶች ትዳራቸውን ለማፍረስ ሲስማሙ ዓለም ጉድ ብሎ ነበር። በወቅቱ ከፍቺ በኋላ ከፍተኛ ወጪ ያስከተለ ትዳር ሆኖ ተመዝግቦ ነበር።
በንግድ ስራውና የጥበብ ስራዎችን በመሰብሰብ የሚታወቀው አሜሪካ ፈረንሳያዊው አሌክ ዊልደንስቲን ከ21 ዓመታት በኋላ ትዳራቸውን እንደሚያፈርሱ ገልጾ ነበር። ባለቤቱ ጆሰሊን ዊልደርስቲን ደግሞ ከፍቺው በኋላ መጀመሪያ ላይ 2.5 ቢሊየን ዶላር እንደምታገኝ ተገልጾ ነበር።
በወቅቱም በየዓመቱ ለሚቀጥሉት 13 ዓመታት ተጨማሪ 100 ሚሊየን ዶላር እንደሚሰጣት ተገልጿል። በዚህም በአጠቃላይ ያገኘችው ገንዘብ ወደ 3.8 ቢሊየን ዶላር ይደርሳል።

የፎቶው ባለመብት, Forbes
ቢል እና ሱ ግሮስ
ቢል ግሮስ እና ሱ ግሮስ በአውሮፓውያኑ 2016 ትዳራቸውን ሲያፈርሱ ክፍያው በኋላ በርካታ ያልተጠበቁ ነገሮች ተከስተው ነበር።
ቢል በዓለማችን ታዋቂ አሜሪካዊ ቢሊየነር ሲሆን የመንግሥት ቦንድ በመግዛት ከፍተኛ ትርፍ በማግኘት ይታወቃል።
የጥንዶቹ የፍቺ ሂደት ደግሞ ሁለት ዓመታትን የፈጀ ነበር። ፍቺያቸውን ሳይጠናቀቅ በፊት ቢል ግሮስ 31 ሚሊየን የሚያወጣውን የባለቤቱን መኖሪያ ቤት ከጥቅም ውጪ አድርጎት መውጣቱን እና ተክሎችን ጭምር ገድሎ እንደሄደ ባለቤቱ ለፍርድ ቤት ተናግራ ነበር።
ከፍቺው መጠናቀቅ በኋላ ደግሞ ሱ ግሮስ 1.3 ቢሊየን ዶላር እንዲሁም 31 ሚሊየን የሚያወጣውን መኖሪያ ቤት እንዲሰጣት ፍርድ ቤት ወስኗል።
በተጨማሪም ጥንዶቹ የገዟቸው በሚሊየኖች የሚያወጡ የጥበብ ስራዎችን እኩል እንዲካፈሉም ተወስኗል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሩፐርት መርዶክ እና አና ቶርቭ
በሚዲያ ቢዝነስ የሚታወቀው ቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ እና አና ቶርቭ ለ31 ዓመታት የቆየ ትዳር የነበራቸው ሲሆን ሶስት ልጆችንም ማፍራት ችለዋል።
ነገር ግን ቢሊየነሩ ሩፐርት መርዶክ ከሁሉም ነገር ራሱን ለማግለል ሲያቅድ በአውሮፓውያኑ 1998 ላይ አብረው ትዳራቸውንም ለማፍረስ ተስማምተዋል። ከፍቺው ጋር ተያይዞም አና ቶርቭ እስከ 1.7 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ እንደተሰጣት ተገልጿል።
ፍቺያቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ጥንዶቹ ወደ ሌላ ትዳር ለመሄድ ብዙም አልፈጀባቸውም ነበር። ሩፐርት መርዶክ ትዳሩን ባፈረስ በ17ኛው ቀን ዌንዲ ዴንግ የተባለች ሴት አግብቶ ትዳር መስርቷል።
አና ቶርቭ ደግሞ ከስድስት ወራት በኋላ ዊሊያም ማን የተባለ ግለሰብ አግብታለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሀሮልድ ሀም እና ሱ አን አርኖል
በነዳጅ እና ጋዝ ንግድ ላይ የተሰማራው አሜሪካዊው ቢሊየነር ሀሮልድ ሀም እስከ 14 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ሀብት እንዳለው ይነገር ነበር። ከባለቤቱ ሱ አን አርኖል ጋር በአውሮፓውያኑ 2015 ትዳራቸውን ለማፍረስ ሲስማሙ 1 ቢሊየን ዶላር ለባለቤቱ እንዲሰጥ ፍርድ ቤት ወስኗል።
በአሁኑ ሰአት ሀሮልድ ሀም የተጣራ ሀብቱ 9 ቢሊየን ዶላር እንደሆነ ተገልጿል።












