አሜሪካ በኮቪድ ክትባቶች ላይ የአእምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲነሳ ድጋፍ ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አሜሪካ በዓለም ንግድ ድርጅት መድረክ ላይ በኮቪድ-19 ክትባቶች ላይ የአእምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲነሳ ድጋፍ ሰጠች።
የዓለም ንግድ ድርጅት አባል አገራት ለኮቪድ-19 ክትባቶች የባለቤትነት ጥበቃ እንዳይደረግ ቢስማሙ፤ ደሃ አገራትን ጨምሮ በርካቶች ክትባቶቹን ማምረት እና በዝቅተኛ ዋጋ ለተጠቃሚ ማድረስ ይችላሉ ተብሏል።
ከዚህ ቀደም ሕንድ እና ደቡብ አፍሪካ የክትባት አበልጻጊዎቹ የያዙት የአእምሯዊ መብት ጥበቃ እንዲነሳ አጥብቀው ሲወተውቱ ቆይተዋል።
ይሁን የእንጂ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝደንት አስተዳደር፣ የአውሮፓ ሕብረት እና ዩናይትድ ኪንግደም የክትባቶቹ የአእምሯዊ መብት መጠበቅ አለበት ሲሉ ቆይተዋል።
መድሃኒት አምራች ኩባንያዎችም የአእምሯዊ መብት እንዲነሳ መደረጉ የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልም በሚል የጆ ባይደንን አስተዳደር ትችተዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የፕሬዝደንት ጆ ባይደንን ውሳኔ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመዋጋት ቁልፍ እርምጃ ነው ብለዋል።
የዚህ ሃሳብ ደጋፊዎች እንደሚሉት፤ በክትባቱ ዙሪያ ያሉ የአእምሯዊ መብት ጥበቃዎች እንዲነሱ ቢደረግ ክትባቱን በበርካታ ቦታዎች በብዛት ማምረት እና ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል። አገራት ክትባቱን በአገራቸው እንዳያመርቱ ከመብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች እንቅፋት እንደሆኑባቸው ሲገልጹ ነበር።
የአሜሪካ የንግድ ተወካይ በዓለም አቀፍ የንግድ ድርጅት መድረክ ላይ አገራቸው በክትባቶቹ ዙሪያ ያለውን የመብት ጥበቃዎች እንዲነሱ ተወተውታለች ብለዋል።
በክትባቶቹ ዙሪያ ያሉት የመብት ጥበቃዎች የሚነሱት 164 የድርጅቱ አባል አገራት በሙሉ ሲስማሙ ነው ተብሏል። የክትባት ባለቤት የሆኑ ድርጅቶችን የአእምሯዊ መብት ለማንሳት ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተገልጿል።
የፕሬዝደንት ጆ ባይደን ውሳኔን "አሳዛኝ" ያለው ሲል የዓለም የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ማህበር ገልጾታል። ማህበሩ "የአምራቾችን መብት ማንሳት ውስብስብ ለሆነ ችግር ትክክል ያልሆነ መልስ መስጠት ነው" ብሏል።












