ቼልሲ ለፍጻሜ መድረሱን ተከትሎ የቻምፒንስ ሊግ ዋንጫ ከእንግሊዝ እንደማያልፍ እርግጥ ሆነ

ቲሞ ቨርነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቼልሲ በስታንፎርድ ብሪጅ ሪያል ማድሪድን በአሳማኝ ሁኔታ በማሸነፍ ለኢስታንቡሉ የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ማለፉን አረጋግጧል።

ቼልሲ በፍጻሜ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲን ይገጥማል። ይህም የእንግሊዝ ክለቦች ብቻ የሚሳቱፉበት የቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ጨዋታ ይሆናል።

ከአንድ ሳምንት በፊት ቼልሲ ወደ ሪያል ማድሪድ ተጉዞ ጨዋታው አንድ አቻ መጠናቀቁ አይዘነጋም።

የቶማስ ቱሄል ቡድን ምስጋና ለግብ ጠባቂው ኤድዋርድ ሜንዲ ይሁንና ሁለት የካሪም ቤንዜማ ጥሩ አጋጣሚዎችን አድኗል።

በጨዋታው ቲሞ ቨርነር በ28 እኛ ሜሰን ማውንት ደግሞ በጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች ቼልሲ 2 ለ 0 ማሸነፍ ችለዋል።

ቼልሲ በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ጨዋታውን በበላይነት አጠናቋል።

ቼልሲ በአዲሱ አሰልጣኝ ቱማስ ቱሄል ስር እያንሰራራ ይገኛል። በሃቨርት እና በቨርነር ፈጣን እንቅስቃሴ ዕድሜ የተጫነው የሚመስለው ማድሪድ ላይ የበላይነት አሳይተዋል።

ግብ ጠባቂው ሜንዲ ጎል ሊሆኑ የሚችሉ ኳሶችን ሲያድን አንቶንዮ ሩዲገርም በጨዋታው የኋላ ደጀንነቱን አስመስክሯል።

ጉዞ ወደ ኢንስታንቡል ፍጻሜ

ቼልሲዎች ከሲቲ ወቅታዊ አቋም አንጻር ዝቅተኛ ግምት ያገኘ ቡድን በመሆን ወደ ፍጻሜው ቢያቀኑም ዕድላቸውን ለመጠቀም ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠቃል።

ቼልሲዎች የኋላ መስመራቸው ጠንካራ ሲሆን መሐሉ ደግሞ ውጤተማ የሚባል ነው።

አሰልጣኙ ቱሄል እና አምበሉ ቲያጎ ሲልቫ ባለፈው ዓመት ከፒኤስጂ ጋር ለፍጻሜ ደርሰው የነበረ ሲሆን ዘንድሮም በሌላ ቡድን ውስጥ ሆነው ለፍጻሜ ደርሰዋል።

ቱሄል ባለፈው ዓመት በባየር ሙኒክ የደረሰባቸውን ሽንፈት ለማካካስ ወደ ቱርክ ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ዘንድሮ ዌምብሌይ ላይ በኤፍኤ ካፕ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ቼልሲ 1 ለ 0 ማንችስተር ሲቲን በማሸን ለፍጻሜ ደርሷል። በፍጻሜው ሌስተር ሲቲን በማሸነፍ ዋንጫውን አንስቷል።

አሰልጣኞቹ ምን አሉ?

የቼልሲው ቶማስ ቱሄል ለቢቲ ስፖርት "[ተጫዋቾቹ] ማሸነፍ ይገባቸዋል። ሪያል ኳስ ብዙ በመያዙ አስቸጋሪ ቢሆንም የነበረው የመልሶ ማጥቃት ጥሩ ነበርን። የመከላከል ፍላጎት ነበራቸው" ብለዋል።

"ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ነበር። ከመከላከል በተጨማሪ ጎል ማስቆጠር ችለናል። ይህ አስደናቂ ስኬት በመሆኑ ለቡድኑ ትልቅ ደስታ ነው" ብለዋል።

የሪያል ማድሪዱ አሰልጣኝ ዚነዲን ዚዳን ለሞቪስታር "ድሉ ይገባቸዋል። በልጆቼ እኮራባቸዋለሁ። ሞክረናል፣ ከፍጻሜውም በአንድ ጨዋታ ብቻ ርቀናል። ቼልሲዎች ጥሩ ተጫውተው በማለፋቸው ውጤቱ ይገባቸዋል" ብለዋል።