በኢትዮጵያ በሐሰት ተመስክሮባቸው 20 ዓመት የተፈረደባቸው ሴት ነጻ ሊወጡ ነው

ማረሚያ ቤት

የፎቶው ባለመብት, CLASSICSTOCK

በሰሜን ሸዋ ዞን የሙጃና ወደራ ወረዳ የእንጀራ ልጃቸውን ገድለዋል በሚል 20 ዓመት የተፈረደባቸው ሴት ነጻ ሊወጡ መሆኑን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን የማረሚያ ቤቶች መምሪያ ገለፀ።

የመምሪያው ኮምዩኒኬሽን ባለሙያ ኮማንደር ደበበ መኩሪያ ለቢቢሲ እንደገለፁት ወ/ሮ አዛለች ቤታ የእንጀራ ልጃቸውን ገድለሻል በሚል የሀሰት ማስረጃ ቀርቦባቸው 20 ዓመት ተፈርዶባቸው ላለፉት 5 ዓመታት በእስር ላይ ነበሩ።

ነገር ግን ተገድላለች የተባለችው ወጣት ሴት በሕይወት በመገኘቷ ከአምስት ዓመት በላይ በእስር የቆዩት ወ/ሮ አዛለች ከወንጀል ነጻ መሆናቸው ተረጋግጧል ብለዋል።

ከአምስት ዓመት በፊት በ2007 ዓ.ም በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የሙጃና ወደራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ አዛለች "በ2006 የእንጀራ ልጅሽን ገድለሻል" በማለት ነበር በፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት።

ኮማንደር ደበበ መኩሪያ አክለውም የሰሜን ሸዋ ዞን የማረሚያ ቤቶች መምሪያ ወ/ሮ አዛለች ቤታ ያለምንም ወንጀል እስር ላይ እንደቆዩ እና እንዲለቀቁ ለክልሉ የይቅርታ ቦርድ ማመልከቻ መጻፉን ገልፀዋል።

ይሁን እንጂ ወ/ሮ አዛለች እንዲፈቱ ከክልሉ የይቅርታ ቦርድ የደብዳቤው ምላሽ እስካሁን አለመምጣቱ አስረድተዋል።

የይቅርታ ቦርድ "ለእርሷ ብቻ መሰብሰብ አይችልም።" በማላቸውን የሚናገሩት ኮማንደሩ፣ አስፈላጊው ሰነድ ለመስከረም ዝግጁ የሚሆን ከሆነ እንጂ "አሁን ላይ የምንፈታው ነገር አይደለም" በማለት የይቅርታ ቦርድ ምላሽ እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

ያልተፈፀመ ወንጀል እና የሐሰት ምስክሮች

ወ/ሮ አዛለች ቤታ ባለቤታቸው እና ከባለቤታቸው ሦስት ልጆች ጋር እየኖሩ ነበር።

ነገር ግን ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ከሶስት የእንጀራ ልጆቻቸው ጋር ያላቸው ግንኙነት እየሻከረ መጣ።

በ2006 ዓ.ም ግድያ ተፈጽሟል በተባለበት ቀንም ወ/ሮ አዛለች እና በእንጀራ ልጃቸው መካከል አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር።

ከአለመግባባቱ በኋላ ልጅቷ ቤት ጥላ ወጣች። ወ/ሮ አዛለችም ልጅቷ መጥፋቷንና እንዲፈልጓት ለአጎቶቿ ቢነግሩም እነርሱ ግን አለመፈለጋቸውን ኮማንደር ደበበ ይናገራሉ።

በኋላም የእንጀራ ልጇ ጠፍታለች ከተባለ ከአንድ ዓመት በኋላ በ2007 የወረዳው ፖሊስ ወ/ሮ አዛለች ቤታን በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ ማድረግ ጀመረ።

የነበረውን ሁኔታም ሲያስረዱ "ወ/ሮ አዛለች፣ የባለቤታቸውን ልጅ ገድላ ሽንት ቤት ውስጥ ጨምራለች፤ በሚል ተጠርጥረው ምርመራ ተካሄደባቸው" ይላሉ።

በዚህም መሰረት ፖሊስ በወ/ሮ አዛለች ግቢ በሚገኘው መፀዳጃ ቤት ባደረገው አሰሳ ተገድላለች የተባለችው ወጣት የትምህርት ቤት ደንብ ልብስ እና የሰው ፀጉር ተገኝቷል።

ወ/ሮ አዛለች በሰው ግድያ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር በሚውሉበት ጊዜ የሞጃ እና ወደራ ሕዝብ ሰልፍ በመውጣት 'እንዲገደሉ' ጠይቆ ነበር ሲሉም ሁኔታውን ያስታውሳሉ።

"በቁጥጥር ስር ውላ ለምርመራ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በምትወሰድበት ወቅት ሕብረተሰቡ 'ትገደልልን፤ ይህች ልጇን የገደለች ኃጥያተኛ ናት፤ ልቀቋት እኛ እንገድላታለን' እያለ ነበር ይህ በሚዲያም ተላልፏል።"

ነገር ግን ወ/ሮ አዛለች ድርጊቱን እንዳልፈፀሙ እያለቀሱ ይናገሩ አንደነበር ኮማንደር ደበበ ገልፀዋል።

በሰሜን ሸዋ ዞን ፍርድ ቤት በተደረገው የክርክር ሂደት ወ/ሮ አዛለች እንጀራ ልጃቸውን መግደላቸው ሰዎች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።

የዞኑ ፍርድ ቤትም የሰዎች እና የፖሊስ ማስረጃን ከመረመረ በኋላ ወ/ሮ አዛለች ግድያ ፈጽመዋል በማለት በዚያው በ2007 ዓ.ም የ20 ዓመታት እስር ፈርዶባቸዋል።

'የሞተችው ልጅ' በሕይወት ተገኘች

ወ/ሮ አዛለች ከአምሰት ዓመት በላይ በእስር ከቆዩ በኋላ ከአንድ ወር በፊት የካቲት 2013 ዓ.ም በ2006 ወ/ሮ አዛለች ቤታ ተገድላለች የተባለችው ሴት በዘመዶቿ ቤት ታየች።

በወቅቱ ይህች ከስድስት ዓመት በፊት ተገድላለች የተባለችው ሴት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ስትኖር ቆይታ መምጣቷ ተነግሯል።

ይህንን መረጃ እንደሰሙ ለአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና የፍትህ ጽህፈት ቤት ደብዳቤ መጻፋቸውን የሚናገሩት ኮማንደር ደበበ መኩሪያ፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ሞታለች የተባለችውን ወጣት በሕይወት መኖር የማረጋገጥ ስራ መሰራቱን ይናገራሉ።

"ይህች ሴት በሕይወት መኖሯ የ19 ሰዎችን ቃል በመውሰድ እንዲሁም ቤተሰቦቿ ልጃችንን አግኝተናል በማለት አረጋግጠዋል።"

የዞኑ አቃቤ ሕግ ሞታለች የተባለች ልጅ በሕይወት በመገኘቷ ያለ ጥፋታቸው የታሰሩት ወ/ሮ አዛለች ቤታ የእስረኞች ይቅርታ መመሪያ መሰረት በማድረግ እንድትፈታ ማመልከቻ ለማረሚያቤቱ መጻፋቸውን ኮማንደር ደበበ እናገራል።

ሌላ ፈተና

ኮማንደር ደበበ በሐሰት ማስረጃ በሰው ግድያ ተከስሰው ከአምስት ዓመታት በላይ በእስር ቤት ያሉት ወ/ሮ አዛለች በአሁኑ ወቅት ከወንጀሉ ነጻ መሆናቸው መታወቁ የተደበላለቀ ስሜት እንደፈጠረባቸው "አሁንም እያነባች ነው ያለችው" በማለት ይናገራሉ።

የሰሜን ሸዋ ዞን የማረሚያ ቤቶች መምሪያ ወ/ሮ አዛለች ቤታ ያለምንም ወንጀል እስር ላይ እንደቆዩ እና እንዲለቀቁ ለክልሉ የይቅርታ ቦርድ ማመልከቻ መጻፉን ኮማንደር ደበበ ለቢቢሲ ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ወ/ሮ አዛለች እንዲፈቱ ከክልሉ የይቅርታ ቦርድ የደብዳቤው ምላሽ እስካሁን አለመምጣቱ ገልፀዋል።

በዚህ መካከል ፍትህ እየታዛባ መሆኑን የሚናገሩት ኮማንደር ደበበ "እርሷም ያለ ጥፋቷ እስር ላይ ነች። ጉዳዩ በጣም ነው የሚያሳዝነው" ብለዋል።

በሐሰት ማስረጃ ተፈርዶባቸው እስር ቤት ያሉ ሰዎች ከሌሎች እስረኞች እኩል በይቅርታ ይወጣሉ ወይንስ ጥፋት እንደሌለባቸው በተረጋገጠበት ቅጽበት ይፈታሉ የሚለው በአዋጅ ላይ ምንም የተቀመጠ ነገር አለመኖሩን በመጥቀስም ይህም ችግር መሆኑን ገልፀዋል።

የሌሎች አገራት ልምድ ምን ይመስላል?

ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ሰዎች በተሳሳተ ክስ ተከስሰው ተፈርዶባቸው ለረዥም ዓመታት በእስር ላይ ቆይተው መፈታታቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም።

በአሜሪካ እኤአ በ2019 በካሊፎርኒያ በሐሰት ክስ ለ38 ዓመት ታስሮ የተፈታው ሰው የ21 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተከፍሎታል።

የ71 ዓመቱ አዛውንት ክሬግ ኮሊ በአሜሪካዋ የካሊፎርኒያ ግዛት በአውሮጳውያን አቆጣጠር በ1978 ዓ.ም የቀድሞ ጓደኛውንና ልጁን ገድሏል በሚል ነበር የተፈረደበት።

በ2017 የዲኤን ኤ ምርመራ ከተደረገ ምርመራ ከእስር ተፈትቷል።

በዚሁ በተመሳሳይ ወቅት በአውስትራሊያ ውስጥ አንድ ሰው የፖሊስ ኃላፊ ገድለሃል በሚል ለ19 ዓመት በእስር ከቆየ በኋላ የ7 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ተከፍሎታል።

ዴቪድ ኢስት ማን የተባሉት እኚህ የአውስትራሊያ ዜጋ እኤአ በ1995 ዓ.ም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር የሆኑት ኮሊን ዊንችስተር የተባሉትን ሰው በመግደል ተጠርጥረው ነበር የእድሜ ልክ እስር የተፈረደባቸው።