አርሰናል ለአውሮፓ ሊግ ፍጻሜ ማለፍ ሳይችል ቀረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አርሰናል በአውሮፓ ሊግ የፍጻሜ ተፎካካሪ ለመሆን ሲያደርገው የነበረው ግስጋሴ ትናንት ምሽት ተቋጭቷል።
ከቪላሪያል ያደረገው የግማሽ ፍጻሜ ያለምንም ግብ አቻ ተጠናቆ ቪላሪያል 2 ለ 1 በሆነ የደርሶ መልስ ውጤት አርሰናልን ማሸነፍ ችሏል።
ሊጠናቀቅ ጥቂት ጨዋታዎች በቀሩት የፕሪሚየር ሊግ ሰንጠረዥ ላይ 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርሰናል፤ አርሰናል ከ25 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በየትኛውም የአውሮፓ ውድድሮች ላይ ላይሳተፍ የሚችልበትን እድል ከፍ አድርጎታል።
ስፔን ተካሂዶ በነበረው የዚህ ጨዋታ የመጀመሪያ ዙር ቪላሪያል ሁለት ለአንድ አሸንፎ የነበረ ሲሆን በመልሱ ጨዋታ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ያስቆጠረውን ግብ ይዞ በሜዳው ጥሩ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ተገምቶ ነበር።
በአርቴታ የሚመሩት አርሰናሎች ግን በትናንቱ ጨዋታ ጥሩ ቢንቀሳቀሱም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ጋቦናዊው የፊት መስመር ተጫዋች ፒዬር ኤምሪክ ኦባምያንግ ሁለት ጊዜ የጎሉን አግዳሚ ያገኘባቸው አጋጣሚዎች ለአርሰናል አስቆጪ አጋጣሚዎች ሆነው አልፈዋል።
በቀድሞው የአርሰናል አሰልጣኝ ኡናይ ኤምሪ የሚመሩት ቪላሪያሎች ጨዋታውን አሸንፈው ወደ ፍጻሜ ማለፋቸው ደግሞ ትለቅ ድል እንደሆነ ገልጸዋል። ኤምሪ በአውሮፓውያኑ 2019 ላይ ነበር ከ18 ወራት ቆይታ በኋላ ከአርሰናል አሰልጣኝነታቸው የተባረሩት።
ሌላኛው የእንግሊዝ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ደግሞ በመጀሪያው ዙር በሜዳው ኦልድትራፎርድ ሮማን 6 ለ2 ማሸነፉን ተከትሎ በሮማ የተካሄደው የመልሱ ጨዋታ ብዙም አልከበደውም ነበር።
ዩናይትዶች በጨዋታው ሶስት ለሁለት ቢሸነፉም በድምር ውጤት ግን ለአውሮፓ ሊግ የፍጻሜ ጨዋታ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል።
የፍጻሜው ጨዋታ ግንቦት 18 በፖላንድ ዳስክ ስታዲየም ይከናወናል።
ለማንችስተር ዩናይትድ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረው ኡራጋያዊው ኤዲሰን ካቫኒ ሲሆን አሰልጣኝ ሶልሻየር አጥቂው በዚህ አቋሙ የሚቀጥል ከሆነ ዋንጫውን የማናናነሳበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።
በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ሁለቱ የእንግሊዝ ክለቦች ማንቸስተር ሲቲና ቼልሲ ለፍጻሜ ማለፋቸውን ተከትሎ በአውሮፓ ሊግም ሁለቱ እንግሊዝ ክለቦች አርሰናልና ዩናይትድ ለፍጻሜ እንደሚደርሱ ተገምቶ ነበር። ነገር ግን የአርሰናል ከውድድሩ ውጪ መሆንን ተከትሎ ሁለቱም ዋንጫዎች እንግሊዝ መግባታቸው እንዲረጋገጥ ማንችስተር ዩናይትድ የፍጻሜውን ጨዋታ ማሸነፍ አለበት።
አርሰናል ከአውሮፓውያኑ 1996/97 የውድድር ዓመት ጀምሮ ከአውሮፓ ውድድሮች ውጪ ሆኖ አያውቅም። በቀድሞው አሰልጣኝ አርሰን ዌንገር እየተመራ በርካታ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድሮችን አድርጓል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በአውሮፓ ሊግ መሳተፍ ጀምሯል።
ነገር ግን ከትናንቱ ውጤት በኋላ በሚቀጥለው የውድድር ዓመት በአውሮፓ መድረክ የመሳተፍ እድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጠቧል። አራት ጨዋታዎች በቀሩት የውድድር ዓመት ሁሉንም ጨዋታዎች ቢያሸንፍ እንኳን በአውሮፓ ሊግ ላይሳተፍ ይችላል። ምከንያቱም ከላይ ያሉት እነ ሊቨርፑል፣ ዌስትሀም፣ ቶተንሃምና ኤቨርተን በቀላሉ ነጥብ ይጥላሉ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው።













