ሩሲያ ሠራሹ ክትባት 'ልክ እንደ ክላሽንኮቭ አስተማማኝ ነው'-ፑቲን

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ስፑትኒክ የተሰኘው ሩሲያ ሠራሹ የኮቪድ-19 ክትባት ልክ እንደ ጦር መሳሪያው ክላሽንኮቭ አስተማማኝ ነው ሲሉ ተደመጡ።
ፑቲን ይህን ያሉት ከአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ጋር በነበራቸው የቪዲዮ ኮንፍረንስ ነው።
ትናንት የአገሪቱ ጤና ተመራማሪዎች በአንድ ዙር ብቻ የሚሰጠውን እና 'ስፑትኒክ ላይት' የሚል መጠሪያ ስላገኘው ክትባት ውጤታማነት መግለጫ ሰጥተዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን ከክትባቱ ጋር ያነጻጸሩት ክላሽንኮቭ የተሰኘው መሳሪያ የተፈበረከው በሩሲያ ሲሆን በመላው ዓለም ዝነኛ የጦር መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል።
የሩሲያው 'ስፑትኒክ ቪ' የኮቪድ ክትባት ከአስትራዜኔካ እና በጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባቶች ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ ነው የሚሰራው። ክትባቶቹ አቅሙ የተዳከመ ጉዳት የማያስከትል ቫይረስ ወደ ሰውነት እንዲገባ በማድረግ የሰውነት የበሽታውን መከላከል አቅምን ያዳብራሉ።
ባሳለፍነው ዓመት የሩሲያ መንግሥት በስፑትኒክ ቪ ክትባት ላይ በቂ ምዘና ሳያደርግ ክትባቱ ለሰዎች እንዲሰጥ ፈቅዷል በማለት በርካቶች ሲቃወሙ ነበር። ይሁን እንጂ በከትባቱ ላይ የተካሄዱ የመጨረሻ ደረጃ የምርምር ?ሥራዎች ቫይረሱ ውጤታማ እንደሆነ ያረጋገጡ ነበር።
ሩሲያ ሰራሹ ስፑትኒክ ቪ ክትባት በሁለት ዙር እንዲሰጥ በበርካታ አገራት ፍቃድ አግኝቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሩሲያ በአንድ ዙር ብቻ የሚሰጠውን ስፑትኒክ ላይት ውጤታማነት ስትመረምር ቆይታለች። የክትባት አምራቹ በሰጠው መግለጫ በአንድ ዙር የሚሰጠው ክትባት 79.4 በመቶ ውጤታማ ነው ብሏል።
በአንድ ዙር ሰዎችን መከተብ በርካቶችን በቀላሉ እና በአጭር ጊዜ ለመድረስ ስለሚያስችል ተመራማሪዎች በአንድ ዙር የሚሰጡ ክትባቶችን ለማበልጸግ ጥረት እያደረጉ ነው።














