ኮሮናቫይረስ፡ ሩሲያ የሰራችው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባት 92 በመቶ ውጤታማ መሆኑን ገለፀች

ክትባት የምትከተብ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሩስያ ኮሮናቫይረስን ይከላከላል ያለችውንና ስፑትኒክ 5 ስትል የሰየመችውን ክትባት 92 በመቶ ውጤታማ መሆኑን ገለፀች።

የአሜሪካ እና ጀርመን ተቀናቃኞቻቸው ውጤታማ የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባት ማግኘታቸውን መግለፃቸውን ተከትሎ ሩሲያ ስፑትኒክ 5 የተሰኘው ክትባት 92 በመቶ ውጤታማ መሆኑን ገልጻለች።

ፋይዘርና ባዮንቴክ የተባሉት የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኀን አበይት ርእስ ሆነው የከረሙ ሲሆን የሰሩት የኮሮናቫይረስ መከላከያ ክትባትም 90 በመቶ ውጤታማ መሆኑ ተገልጿል።

ሩሲያ በበኩሏ 16 ሺህ በጎ ፈቃደኞች ላይ ሙከራ መማድረጓን አስታውቃ 92 በመቶ ውጤታማ መሆኑን አስታውቃለች።

ይህ የሩሲያ ክትባት ግን በሌላ አካል ውጤታማነቱ አልተፈተሸም።

ሩሲያ ለበጎ ፈቃዶቹ ስፑትኒክ 5 የተሰኘውን ክትባት በ21 ቀናት ልዩነት በሁለት ዙር መስጠቷን ገልጻ 20ዎቹ ብቻ በቫይረሱ መያዛቸው ገልጻለች።

ሩሲያ በነሐሴ ወር የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ክትባት አገኘሁ በማለቷ ስትተች መቆየቷ ይታወሳል። በዚያ ወቅት የክትባቱ ሶስተኛ ዙር ሙከራ ገና አልተጀመረም ነበር ተብሏል።

ከዚያ ጊዜ ጀምሮ 36 ሺህ ሰዎች ቢያንስ ከሁለቱ ዙር ክትባት አንዱን የተወጉ ሲሆን ምንም ዓይነት የጎንዮሽ ጉዳት አልታየባቸውም ስትል አስታውቃለች።

በርካታ ሩስያውያን አሁንም በስፑትኒክ ክትባት ላይ ጥርጣሬ ቢኖራቸውም በርካታ በጎ ፈቃደኞች ግን ለሞስኮ የጤና ማዕከል እንደተናገሩት መድሃኒቱን ከወሰዱ በኋላ ጥሩ ጤንነት ተሰምቷቸዋል።

መድሃኒቱን የሰሩት ግለሰቦች ለመጀመሪያ ጊዜ እንደገለፁት ከሆን ለቫይረሱ የበለጠ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች፣ የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ፣ ከክሊኒካል ሙከራው ውጪ ስፑትኒክ 5 ክትባትን ተወግተዋል።

ሩሲያ የሰራችውን ክትባት ስፑትኒክ-5 (Sputnik-V) ስትል የሰየመችው ወደ ጨረቃ ባቀናችው በዓለም የመጀመሪያዋ የሩሲያ ሳተላይት ነው።

ስፑትኒክ በሩስኪ ቋንቋ ሳተላይት ማለት ነው።

ይህ ሩሲያ ተሳካ ያለችው ክትባት በዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዝርዝር ውስጥ ምዕራፍ ሦስት ከደረሱ ስድስት ተስፋ ሰጪ ክትባቶች አንዱ ሆኖ እንኳ አልተመዘገበም።

በዓለም የመጀመርያው የተባለው ይህ ስፑትኒክ-5 ክትባት ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲትዩት ነው ያመረተው።

ኢንስቲትዩቱ እንደሚለው ክትባቱ አስተማማኝ የመከላከል አቅም ይሰጣል።

ፑቲን በነሐሴ ወር ላይ ገና ቀደም ብሎ "ይህ ክትባት አስተማማኝ እንደነበር አውቅ ነበር" ብለዋል። "ሁሉንም ሳይንሳዊ ሂደቶችን በአስተማማኝ ሁኔታ ማለፍ ችሏል" ሲሉም አስረግጠው ተናግረዋል።

በወቅቱ ፑቲን ከልጆቻቸው ለአንዷ ክትባቱ ተሰጥቷት ትንሽ አተኮሳት እንጂ ምንም አልሆነችም ብለዋል።

ፑቲን የትኛዋ ልጃቸው ክትባቱን ወስዳ እንዳተኮሳት ግን በስም አልገለጹም።

የሩሲያ ሳይንቲስቶቹ ሰዎች ላይ ጉንፋንን የሚያመጣው አዲኖ ቫይረስ የተሰኘውን የተላመደ የተህዋስ ቅንጣት ተጠቅመው ነው ክትባት ሰራን ብለው ነበር።

ይህን ለማዳ ተህዋሲ አዳክመው ወደ ሰውነት በማስገባት ሕዋስ በማቀበል ክትባቱ ሰውነት ኮቪድ-19 ተህዋሲ ሲገባ ነቅቶ እንዲዋጋ ያደርገዋል ብለዋል።

ኮሮና