ማንችስተር ሲቲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ አለፈ

በትናንት ምሽቱ ጨዋታው ድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ አገናኝቷል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በትናንት ምሽቱ ጨዋታው ድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ አገናኝቷል።

የእንግሊዙ የእግር ኳስ ክለብ ማንቸስተር ሲቲ የፈረንሳዩን ፒኤስጂ በመርታት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ለቻምፒየንስ ሊግ ለፍጻሜ ማለፉን አረጋግጧል።

ፓሪስ ላይ በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ማንችስተር ሲቲዎች 2 ለ 1 ማሸነፋቸው ይታወሳል። በትናንት ምሽቱ የሁለተኛ ዙር ጨዋታ ደግሞ ሲቲዎች በሜዳቸው 2 ለ 0 ፒኤስጂን በመርታት 4 ለ1 በሆነ ድምር ውጤት ነው ያሸነፉት።

በትናንት ምሽቱ ጨዋታው ድንቅ አቋም ላይ የሚገኘው አልጄሪያዊው ሪያድ ማህሬዝ ሁለቱንም ግቦች ከመረብ አገናኝቷል።

ፒኤስጂዎች ጨዋታው ከመካሄዱ በፊት የሚተማመኑበት ፈረንሳዊው የፊት መስመር ተጫዋች ኪሊያን ምባፔ በጉዳት ምክንያት እንደማይጫወት ይፋ አድርገው ነበር። በጨዋታው ፒኤስጂዎች የቀድሞ ፈጣን አጨዋወታቸውን መከተል አቅቷቸው የነበረ ሲሆን ማንችስተር ሲቲዎች ደግሞ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ነበር ያመሹት።

ልክ በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ የፒኤስጂው ኢድሪሳ ጌይ በቀይ እንደወጣው በሁለተኛው ዙር ደግሞ ከእረፍት መልስ አርጀንቲናዊው አንሄል ዲማሪያ ፈርናንዲንሆ ላይ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ዳኛው ወስነዋል።

ሲቲዎች በሜዳቸው ግብ ላለማስተናገድ በጥንቃቄ ሲጫወቱ የነበረ ሲሆን አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላም ልፋታችን መና አልቀረም ብሏል። ክለቡም በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ይጫወታል።

ዛሬ በሚደረገው ሌላኛው የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ ከቼልሲ እና ሪያል ማድሪድ ይገናኛሉ። የዚህ የደርሶ መልስ አሸናፊ በፍጻሜው ማንችሰተር ሲቲን የሚገጥም ይሆናል።

ቼልሲና ሪያል ማድሪድ ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ በማድሪድ ሜዳ አንድ አቻ ተለይየተዋል።

ማንረችሰተር ሲቲዎች በጋርዲዮላ እየተመሩ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ስኬትን እያስመዘገቡ ሲሆን ዘንድሮም ለሶስተኛ ጊዜ ዋነጫውን ለማንሳት ከጫፍ ደርሰዋል።

በመጪው ቅዳሜ በፕሪምየር ሊጉ ከቼልሲ የሚያደርጉትን ጨዋታ የሚያሸንፉ ከሆነ ደግሞ የዘንድሮው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ።

ማንችሰተር ሲቲ ለአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ በመድረስ ዘጠነኛው የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለብ መሆን የቻለ ሲሆን ዋንጫውን የሚያነሳ ከሆነ ደግሞ በክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል።