የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አበረ አዳሙ ሕይወታቸው አለፈ

Abere Adamu

የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር የነበሩት አቶ አበሩ አዳሙ ከዚህ ዓለም በሞት መለያታቸው ተሰምቷል።

ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ዛሬ ጠዋት የህመም ስሜት ተሰማኝ ብለው ወደ ሆስፒታል ከሄዱ በኋላ ማረፋቸው ታውቋል ሲል የዘገበው የሃገሪቱ ቴሌቪዥን ጣቢያ ኢቢሲ ነው።

አቶ አበረ አዳሙ፣ በድንገተኛ ህክምና ላይ እንዳሉ በልብ ህመም ችግር ህይወታቸው ማለፉን የሆስፒታል ምንጮች ገልፀዋል ሲል አክሏል ብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ።

የቀድሞው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አበረ አዳሙ ከሁለት ዓመታት በላይ በኃላፊነቱ ሲሰሩ ቆይተዋል።

አቶ አበረ ‘የሕግ የበላይነት ለአገራዊ ልማት’ የሚል መጽሐፍ አሳትመው ለንባብ አብቅተዋል።

አቶ አበረ የመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በስዊድን አገር ተከታትለዋል።

መጽሐፉ ጥናታዊ ጽሁፎችን መሠረት በማድረግ ተተርጉሞ የቀረበ መሆኑ በመፅሐፉ ምርቃት ወቅት ተገልጿል።

ይህ መጽሐፍ የፌደራል ቋንቋ ይሆናሉ በተባሉት አምስት ቋንቋዎች ተተርጉሞ መነበብ አለበት ሲሉም ተናግረው ነበር።

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር የነበሩት ተኮላ አይፎክሩ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽንን እንዲመሩ መሾማቸው ይታወሳል።

አዲሱ ኮሚሽነር አቶ ተኮላ ከሦስት ዓመት በፊት በፌደራል ፖሊስ ውስጥ በኃላፊነት ከመመደባቸው አስቀድሞ በአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በተለያዩ ቦታዎች አገልግለዋል።

በቅርቡ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና በተፈፀሙ ጥቃቶች የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱንና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ተከትሎ ነው አቶ ተኮላ ወደ ኃላፊነት የመጡት።