ነብይ እዩ ጩፋ “ልብሱን [የደንብ ልብስ] ለብሳችሁ ኑ አላልንም” ሲል ምላሽ ሰጠ

'ነብይ' እዩ ጩፋ የአገር መከላከያ ሠራዊት ክስ እንደሚመሰርትበት መግለፁን ተከትሎ ወታደራዊ የደንብ ልብሱን ለብሳችሁ ኑ አላልንም ሲል ምላሽ ሰጠ።
የአገረ መከላከያ የሠራዊት አባላቱን የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ክብር ባልጠበቀ መልኩ፣ በቪዲዮና ፎቶ ቀርጾ በአደባባይ እንዲሰራጭ በማድረኩ 'ነብይ' እዩ ጩፋ ላይ ክስ እመሰርታለሁ ማለቱ ይታወሳል።
ነብይ እዩ ጩፋ የአገር መከላከያ ሠራዊት ስላወጣው መግለጫ በቪዲዮ በሰጠው ምላሽ፣ ወታደራዊ ልብስ ለብሰው በቤተ እምነቱ የተገኙ ሰዎች የሰሩት ወንጀል የለም ያለው ነብይ እዩ ጩፋ አለ ከተባለም በወታደራዊ ሕግ ሊጠየቁ ይችላሉ ሲል ተናግሯል።
እርሱ ይከሰሳል ስለመባሉ ሲመልስም " ነብይ እዩ ይከሰሳል የሚለው ደግሞ ለአንዳንድ ሰው የተለየ ሕግ ካለ ሊሆን ይችላል፤ የተለየሕግ ከሌለ ግን የሚያስከስስ አይደለም" ሲል ተናግሯል።
መከላከያ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫው "ጥቂት የሠራዊታችን አባላት ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል" ብሏል።
የደንብ ልብሱን ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ አባላቱም በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸውን ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ሥራ እየተሠራ ይገኛል ብሎ ነበር።
'ነብይ' እዩ ጩፋ ለቀረበበት ክስ ምላሽ ሲሰጥ የመከላከያ አባላቱ የተሳተፉበት ፕሮግራም ከአንድ ወር በፊት ገደማ የተካሄደ መሆኑን ጠቅሶ፤ የደንብ ልብስ የለበሱና የጦሩ አባል የሆኑ ወታደሮች ልክ እንደማንኛውም ሰው በአዲስ አበባ በሚገኘው 'ክራይስት አርሚ ቤተ-ክርስቲያን' ተገኝተው የዕለቱን ፕሮግራም መካፈላቸውን አስረድቷል።
አክሎም ማንኛውም በቤተ እምነቱ የሚገኝ ሰው ፕሮግራሙ እንደሚቀረጽና እንደሚተላለፍ እንደሚያውቅ ገልጿል።
'ነብይ' እዩ "ልብሱን ለብሳችሁ ኑ አላልንም። እንደማንኛውም ምዕመን ለመታደም ነው የመጡት" በማለት ከዚህ ቀደምም የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎች ወደ ቤተ ክርስቲያኑ እንደሚመጡ እና እርሱ በሚመራው አገልግሎት እንደሚካፈሉ ባስተላለፈው የቪዲዮ መልዕክት ላይ ተናግሯል።
"እኛ ይሄ ሰው ይምጣ፤ ይሄኛው አይምጣ አንልም። እኛ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለሁሉም ሰው ክፍት አድርጎ መጠበቅ ብቻ ነው" ብሏል።
"በእለቱ እኛ ጋር መጥተው ከአጋንንት እስራት ነጻ የሆኑ ሰዎች የሰሩት ወንጀል የለም። በወቅቱ የመጡት ወታደሮችም ልክ እንደ ማንኛውም አጋንንት ለቅቋቸው ሲሄድ ወድቀው ነበር። ይሄ ለሁሉም ሰው የሚሆን ነው። የተደበቀ ነገር አይደለም" ብሏል 'ነብይ' እዩ ጩፋ።
የቤተ-ክርስቲያኗ አገልግሎት በቴሌቪዥን እና በማህበራዊ ድረ-ገጾች ከዚህ ቀደምም እንደሚለቀቅ አስታውሶ፤ "ይሄም የተለየ ጉዳይ አይደለም" በማለት ተናግሯል።
"የመከላከያ ወታደሮች እንዲገኙ ኑ ብለን አልደወልንላቸውም። እኔ አገልግሎት የሰጠሁት የመከላከያ ካምፕ ሄጄ አይደለም። በቤተክርስቲያናችን ተገኝተው ነው የተገለገሉት። ዩኒፎርማቸውን ለብሰው ለምን ተገኙ የሚለው ሌላ ጥያቄ ነው። የተገኙ ሰዎች ግን የሰሩት ወንጀል የለም"
'ነብይ' እዩ፤ "ብዙ አይነት ሰው ወደ እኛ ይመጣል" ካለ በኋላ፤ "እኛ ጋር ሲመጡ ግን አለባበሳችሁን አስተካክሉ አልያም ልብሳችሁን ቀይሩ የማለት ስልጣን የለንም። ቤተክርስትያን ለሁለም ናት፤ የሁሉም ናት" ሲል ተናግሯል።

እዩ ጩፋ ከሁለት ዓመት በፊት ለቢቢሲ ሲናገር "አጋንንትን በካራቴ ሆነ በቴስታ ብመታ ምን ችግር አለው?" ብሎ ጠይቆ ነበር።
እዩ ጩፋ ነብይና ሐዋርያ ተብለው ከተነሱ ብዙዎች አንዱ ነው። እዩ በፈውስ ትዕይንቶች፣ 'አጋንንትን በካራቴ በመጣል'ና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች አነጋጋሪና አወዛጋቢ ስለመሆኑ ጠይቀነው ምላሽ ሰጥቷል።
ከእዩ ጨፋ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ እዚህ ማንበብ ይችላሉ።













