መከላከያ ‘ነብይ’ እዩ ጩፋ ላይ ክስ ልመሰርት ነው አለ

የአገር መከላከያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

የፎቶው ባለመብት, @fdredefense.official

የምስሉ መግለጫ, የአገር መከላከያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ

የአገረ መከላከያ ሠራዊት በ'ነብይ' እዩ ጩፋ ላይ ክስ ሊመሰርት መሆኑን አስታወቀ።

'ነብይ' እዩ ጩፋ የሠራዊቱን ስምና ታማኝነት በማሳጣት ለግል ፍላጎትና ጥቅም በማን አለብኝነትና ኃላፊነት በጎደለው አኳኋን ለፈፀመው ድርጊት በሕግ ይጠየቃል ሲሉ የአገር መከላከያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ተናግረዋል።

መከላከያ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ፤ "እዩ ጩፋ የተባለ በሐይማኖት ስም ፣ እየተከተሉኝ ነው ያላቸውን ግለሰቦች ክብር ባልጠበቀ መልኩ፣ ከነ ዩኒፎርማቸው፣ በቪዲዮና ፎቶ ቀርጾ በአደባባይ እንዲሰራጭ አድርጓል" ብሏል።

"ጥቂት የሠራዊታችን አባላትም ይህን ፍላጎት ለማሟላት የሁሉም ኢትዮጵያውያን መለያ የሆነውን ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ እንደነበሩ ተረጋግጧል" ብሏል።

ከሰሞኑ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ደንብ ልብስን የለበሱ ሰዎች 'ነብይ' እዩ ጩፋ በሚያገለግልበት መድረክ ላይ የደንብ ልብስ ለብሰው መገኘታቸውን የሚያሳይ ምስል በሰፊው ተሰራጭቶ ነበር።

አነጋጋሪው 'ነብይ' እዩ ጩፋ ከዚህ ቀደም ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ ብዙውን ጊዜ እግሩን በመሰንዘር የአጋንንት ማስወጣት ተግባራትን እንደሚፈጽም ተናግሮ ነበር።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ከዚህ ቀደምም በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሰጥቶ ነበር። እንደ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ከሆነ "የሠራዊታችን አባላት የፈለጉትን ዕምነት የመከተል መብት አላቸው። ይሁን እንጂ የተከበረውን የኢትዮጵያ ህዝቦች መመኪያ የሆነውን የደንብ ልብስ በመልበስ ማምለክ ፈጽሞ የተከለከለ ነው" ሲሉ ተናግረው ነበር።

መከላከያ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ "የደንብ ልብስ ለብሰው ተሳታፊ የሆኑ አባላት በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸውንም ወደ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ለማቅረብ የማጣራት ሥራ እየተሠራ ይገኛል" ብለዋል።

የሕዝብ ግነኙነት ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ ጥፋት በተለያዩ የእምነት ተቋማት የተገኙ አባላት ላይ የእርምት እርምጃ ተወስዶ እንደነበር አስታውሰው፤ "ወደፊትም ማንኛውም የሠራዊቱ አባል የየትኛውም እምነት ተከታይ ቢሆን በእንደዚህ አይነት ተግባር ውስጥ ተሳትፎ ከተገኘ ተጠያቂ ይሆናል" ብለዋል።

"ሠራዊታችን በጋብቻ፣ በቀብር ጊዜ እና በእምነት ቦታዎች ክብሩን በጠበቀ መልኩ የሚከወኑ ስርዓቶች አሉት። ሠራዊቱም ከህዝብ የወጣ በመሆኑ በየግሉ ሐይማኖት ያለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በኛ በኩል በህጋችን የተፈቀዱና የተከለከሉ ጉዳዮችን የማስረፅ ሥራም ይሠራል" ብለዋል።

line

እዩ ጩፋ በፈውስ ትዕይንቶች፣ 'አጋንንትን በካራቴ በመጣል'ና በሌሎችም በርካታ ምክንያቶች አነጋጋሪና አወዛጋቢ ስለመሆኑ ከሁለት ዓመታት በፊት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, እዩ ጩፋ

ከእዩ ጋር የተደረገውን ሙሉ ቃለ ምልልስ እዚህ ማንበብ ይችላሉ። እዩ ጩፋ፡ ማን ነው ነብይ ያለህ?