የ'ሸኔ' እና ሕወሓት በሽብር መፈረጅ አንድምታው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, ROBERTO SCHMIDT
ቅዳሜ ዕለት የሚንስትሮች ምክር ቤት ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) እና 'ሸኔ' በሽብርተኛነት እንዲሰየሙ የውሳኔ ሐሳብ ማስተላለፉን ይታወሳል።
በቀጣይ የሚንስትሮች ምክር ቤት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 77 በተሰጠው ስልጣን መሠረት፤ "ህወሓት" እና "ሸኔ" ቡድኖችን በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ የውሳኔ ሃሳቡን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይልካል።
ፓርላማውም የሚንስትሮች ምክር ቤት ሃሳብን ተቀብሎ ቡድኖቹን 'አሸባሪ' ብሎ ለመፈረጅ ሁለት ሶስተኛ ድምጽ መሰጠት አለበት።
ለመሆኑ አንድን ቡድን አሸባሪ ብሎ መፈረጅ ለምን ያስፈልጋል?
ለዚህ ጥያቄ ምላሽ እንዲሰጡን ከዓመት በፊት ተሻሽሎ የፀደቀውን የሽብር ሕግ የማርቀቅ ተግባር ላይ የተሳተፉት እና የዐቃቤ ሕጉን የአማካሪ ጉባኤ ጽህፈት ቤት የሚመሩትን አባድር ኢብራሂምን (ዶ/ር) ጠይቀናል።
አባድር (ዶ/ር) መንግሥት የተለያዩ የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል ዝርዝር ክትትል ማድረግ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር አንድን ቡድን አሸባሪ በማለት ሊፈርጅ እንደሚችል ያብራራሉ።
አባድር (ዶ/ር) አንድን ተግባር 'ሽብር' ለማለት "የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ ህዝብን ወይም የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ለማሸበር አስቦ የተፈፀመ ተግባር ሲሆን"
አክለውም "መንግሥትን፣ የውጭ አገር መንግሥትን ወይም ዓለም አቀፍ ድርጅትን ለማስገደድ ህይወትን ለአደጋ ማጋለጥ፣ የአካል ጉዳት ማድረስ፣ ማገት ወይም መጥለፍ፣ ንብረትን እንዲሁም የማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስተጓጎል" የሚሉትን ጨምሮ የተቀመጡ አምስት ክልከላዎች ተጥሰው ሲገኙ የሽብር ወንጀልን ያቋቁማሉ ሲሉም ይገልፃሉ።
በተጨማሪም አባድር (ዶ/ር) አንድ ድርጅት እነዚህን ተግባራት አላማው ካደረገ፣ የድርጀቱ አመራር ወንጀሉን በአሰራር ወይም በግልጽ የተቀበለው ከሆነ፣ በአሰራር ወይም በአፈፃፀም ወንጀሉ የድርጅቱ መገለጫ ከሆነ፣ አንድ ቡድን አሸባሪ ተብሎ ሊሰየም እንደሚችል ለቢቢሲ አስረድተዋል።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት አንድ ድርጅት 'አሸባሪ' ተብሎ እንዲፈረጅለት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርብ፤ ድርጅቱን አሸባሪ ያስባሉ ተግባራት እና ድርጅቱ በዚያ ውስጥ ያለውን ተሳትፎ በግልጽ ማሳየት ይገባል ሲሉም አባድር ያብራራሉ።
ይህንን ማስረጃ ይፋ ማድረግ የደህንነት ስጋት ያለው ነው ተብሎ ሲታመን ግን ዝርዝር ጉዳዮች ላይቀርቡ እንደሚችሉ ሕጉ ደንግጓል።
ድርጅቱ ከላይ በተጠቀሱት ሶስት ተግባራት ቢያንስ በአንዱ መሳተፉ መረጋገጥ እንደሚገባውም ባለሞያው ያስረዳሉ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ድርጅቱ ወይም ሌላ አካል አስተያየቱን የሚያቀርብበትን በቂ ጊዜ በመስጠትና የጊዜ ገደብ በመግለጽ አግባብ ባለው መገናኛ ዘዴ ጥሪ ማስተላለፍ አለበት ሲል አዋጁ ይደነግጋል።
በአሸባሪነት ሊፈረጅ ሃሳብ የቀረበበት ድርጅትም ለምክር ቤቱ አስተያየት ለማቅረብ የማያስችሉ እና ሚስጥራዊ ከሚባሉ ጉዳዮች በስተቀር ማስረጃዎችን የማወቅና የማግኘት መብት አለው። እንዲሁም የውሳኔ ሀሳቡን ለመቃወም ለምክር ቤቱ ማንኛውንም ማስረጃ ለማቅረብ መብት እንዳለው አዋጁ ይደነግጋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት [ሰኞ] ይህንን ጥሪ በመገናኛ ብዙሃን አቅርቧል።
ይህ የውሳኔ ሃሳብ ሲፀድቅም በአዋጁ መሠረት የመጀመሪያው ውጤት ድርጅቱ ካልፈረሰ እና ህጋዊ ሰውነት ካለው፤ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ድርጅቱ እንዲፈርስ ስልጣን ላለው ፍርድ ቤት በማመልከት እንዲፈርስ ያደርጋል። እንዲሁም የድርጅቱን ንብረት መንግሥት እንዲወርሰው ይደረጋል ሲል አዋጁ ይደነግጋል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ስህተቱ ምን ይማር?
መንግሥት እነዚህ ሁለት ድርጅቶችን በአንድ ግዜ ሽብርተኛ ለማለት ያስብ እንጂ በሁለቱ ድርጅቶች ላይ የሚኖረው ውጤት ተለያይቶ መታየት አለበት ሲሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሕግ ባለሙያ ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም መንግሥትን የሚቃወም አሸባሪ እየተባለ በዚህ ትርጉም ስር ወድቆ ነበር የሚሉት ባለሙያው መንግሥትን መቃወም ሽብር ሆኖ መታየት የለበትም ሲሉም ያስረዳሉ።
"ሲቪል መሆን የሚጠበቀው የፖለቲካ ግንኙነት፤ በህግ፣ በወታደር እና በፖሊስ መተዳደር የለበትም። በተለይ አተገባበር ላይ እንዳይኖር መደረግ አለበት" በማለት ገልፀዋል።
"ከዚህ ቀደም የተሻረውን የፀረ-ሽብር ሕግ መንግሥት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለውን ግንኙነት ወደ የፀጥታ ግንኙነት የሚወስድበት ነበር። ይህ አሁን ላይ መደገም የለበትም" ብለዋል።
"በተለይም በመንግሥት እና በእነዚህ ሁለት ተቋማት መካከል ከዚህ በኋላ ድርድር፣ እርቅ ወይም ምንም አይነት ስምምነት ማድረግ የማይታሰብ ያደርገዋል" ሲሉም አክለዋል።
በተለይም በትግራይ ክልል ያለውን ችግር መሰረቱን ከመፍታት ይልቅ አንድ በአንድ የሚታዩ የፍርድ ቤት ጉዳይ ያደርገዋል። ይህም ህጋዊ የወንጀል ድርጊት እና በጥቃቶች ላይ መልስ የመስጠት ሂደት ይሆናል።
በተጨማሪም በአገር ውስጥ ያሉ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የውጪ አካል ለማስታረቅ ወይም ለመደራደር የሚያደርገውን ጥረት ወንጀል እንደሚያደርገውም ያስረዳሉ። በተለይም አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የውጪ መንግሥታት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት በስምምነት እንዲቋጭ ሲቀርቡ የነበሩ ጥያቄዎችን ለመዝጋት የታሰበ ይመስላልም ሲሉ አስረድተዋል።
በአሸባሪነት እንዲፈረጁ የውሳኔ ሃሳብ የተላለፈባቸው 'ሸኔ' እና ህወሓት ማን ናቸው?
ሸኔ
የሚንስትሮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብሎ እንዲፈረጅ ሃሳብ ያቀረበው "ሸኔ" ቡድንን ነው።
በአሁኑ ወቅት በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ በስፋት ስለሚንቀሳቀሰው እና የመንግሥት ባለስልጣናት፤ 'ኦነግ ሸኔ' ብለው ስለሚጠሩት ታጣቂ ቡድን የሚታወቀው የሚከተለውን ነው።
መንግሥት በተለይ የኦሮሚያ ክልል ባለስልጣናት 'ኦነግ ሸኔ' በሚል የሚጠሩት ታጣቂ ኃይል ራሱን "የኦሮሞ ነጻነት ጦር" በማለት ይጠራል።
'የኦሮሞ ነጻነት ጦር' ለበርካታ አስርት ዓመታት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ የጦር ክንፍ ሆኖ ቆይቷል።
የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህምድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የኦነግ አመራሮች ወደ አገር ከገቡ በኋላ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (መንግሥት ኦነግ ሸኔ የሚለው ቡድን) ከፓርቲው ተገንጥሎ በትጥቅ ትግሉ እንደሚቀጥል ይፋ አደረገ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ-መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ የኦሮሞ ነጻነት ጦር (ኦነግ ሸኔ) በእርሳቸው እንደማይታዘዝ ይፋ አድርገው ነበር።
ሸኔ የምትለዋ መጠሪያ ከየት መጣች?
ሸኔ- ማለት 'ሸን' ከሚለው የኦሮምኛ ቃል የመጣ ነው። 'ሸን' ማለት አምስት ማለት ነው። 'ሸኔ' ማለት ደግሞ አምስቱ እንደማለት ነው።
በኦሮሞ ነጻነት ግንባር ፓርቲ አደረጃጀት ውስጥ አምስት አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ 'ጉሚ ሸኔ' ተብሎ ይጠራል። ጉሚ ሸኔ ማለት 'አምስት አባላት ያሉት ጉባኤ' እንደማለት ነው። ፓርቲው ግን ከ5 በላይ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አባላት ሊኖረው ይችላል።
ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው ቡድን መሪ እንደሆነ የሚታመነው ኩምሳ ድሪባ በትግል ስሙ በስፋት የሚታወቀው ጃል [ጓድ] መሮ፤ ለኦሮሞ ነጻነት እንታገላለን ይላል።
በተለያዩ ወቅቶች መንግሥት በዚህ ቡድን ላይ በሳምንታት ውስጥ 'እርምጃ' እወስዳለሁ ቢልም፤ በቡድኑ አባላት ተፈጽመዋል በሚባሉ ጥቃቶች በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ተገድለዋል በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተፈናቅለዋል።
መንግሥት ኦነግ ሸኔ ብሎ የሚጠራው ቡድን በርካታ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የፖሊስ አባላት ላይ ግድያ እና የባንክ ዝርፊያ መፈጸሙን ይገልጻል።
መንግሥት ከዚህ ቀደም ይህ ቡድን በህወሓት ድጋፍ እንደሚደረግለት እና በትግራዩ ግጭትም ለህወሓት ወግነው ሲዋጉ ነበሩ ያላቸውን 'የኦነግ ሸኔ' ታጣቂዎችን መማረኩን አስታውቆ ነበር።
ኦነግ-ሸኔ የሕዝብ 'ጠላት ነው'
የቦረና አባ ገዳ የሆኑት ኩራ ጃርሶ ኦነግ-ሸኔን የሕዝብ ጠላት ነው ሲሉ ቡድኑን ማውገዛቸው ይታወሳል።
አባ ገዳ ኩራ በታጣቂ ቡድኑ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ሠላማዊ ሰዎች በመገደላቸው ቡድኑን ጠላት ብሎ መፈረጁ እንዳስፈለጋቸው ተናግረዋል።
የቦረና አባ ገዳ በማኅበረሰባቸው ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸው ሲሆኑ የሚያስተላልፉትም መልዕክት ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው።
ህወሓት
ህወሓት በሽምቅ ውጊያ ወደ አገር መሪነት ከዛም ወደ የክልል አስተዳዳሪነት በመጨረሻም ወደ ሽምቅ ወጊያ ተመልሷል።
ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ በአገሪቱ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛው ተዋናይ ሆኖ የቆየው ህወሓት ባለፈው ጥቅምት ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱን አጥቶ እንዲሰረዝ ተደርጓል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የንጉሡ አስተዳደር ወድቆ ወታደራዊው መንግሥት ወደሥልጣን መውጣቱን ተከትሎ ነበር የካቲት 11/1967 ዓ.ም የትጥቅ ትግል መጀመሩን ያስታወቀው።
ለህወሓት የትጥቅ ትግል መነሻ የሆነው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቋቋሙት ማገብት (ማህበረ ገስገስቲ ብሔረ ትግራይ) የተባለው መደበኛ ያልሆነ ቡድን ነበር።
ማገብት በስምንት አባላት የተመሠረተ ሲሆን ከእነዚህም መካከል በሪሁ በርሀ (አረጋዊ በርሄ ዶ/ር)፣ አምባዬ መስፍን (ስዩም መስፍን) እና አመሃ ፀሃዬ (አባይ ፀሃዬ) ተጠቃሽ ናቸው።
ከደርግ ጋር የሚደረገው ጦርነት ወደ ሌሎቹ የአገሪቱ ክፍሎች ሲሸጋገር በየአካባቢዎቹ ያሉትን ሕዝቦች ይወክላሉ የተባሉ ድርጅቶችን ማቀፍ እንዲሁም ሊወክሉ ይችላሉ የሚባሉ እንዲቋቋሙ ህወሓት ጉልህ ሚና ተጫውቷል።
ይህንንም ተከትሎ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን)፣ ከኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ጋር በመጣመር ኢሕአዴግ የተባለውን ግንባር ፈጠረ።
በህወሓት የበላይነት ይመራ የነበረው ኢሕአዴግ የደርግ መንግሥትን ከሥልጣን ካስወገደ በኋላ ለ27 ዓመታት አገር መምራት ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስተር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ግን በግንባሩ ውስጥ ለዓመታት የቆየው ቅሬታ ስር እየሰደደና እየጎላ መጣ።
በመጨረሻም ኢህአዴግ ከስሞ የብልጽግና ፓርቲ ሲተካው ህወሓት በአዲሱ ስብስብ ውስጥ ላለመግባት ከመወሰኑ ባሻገር "ውህደቱ ሕጋዊ አደለም'' በማለት ተቃውሞውን አስምቶ ነበር።
ህወሓት ከፍተኛ አመራሮቹን ይዞ ወደ ትግራይ ካቀና በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረው ግንኙነት ከመሻከር አልፎ ወደ ግጭት አምርቷል።
ከ6 ወራት በፊት በተጀመረው ጦርነት የፌደራሉ መንግሥት 'ህወሓት አብቅቶለታል' ሲል አውጇል።
የቡድኑ ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በተለያዩ ከፍተኛ ወንጀሎች ተጠርጥረው የእስር ማዘዣ ከወጣባቸው ወራት ተቆጥረዋል።
በርካታ የህወሓት አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውና ሌሎች ደግሞ መገደላቸው የአገሪቱ ሠራዊት መገለጹ ይታወሳል።












