ሕዳሴ ግድብ፡ ኢትዮጵያ የውሃ ሙሌት ከመጀመሯ በፊት ግብጽና ሱዳን ባለሙያ እንዲሰይሙ ጠየቀች

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሳተላይት ምስል

የፎቶው ባለመብት, Maxar Technologies via Reuters

የምስሉ መግለጫ, በመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ወቅት ተነሳ የሳተላይት መስል

ሁለተኛው ዙር የታላቁ የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት መረጃ ለመለዋወጥ እንዲቻል ሱዳንና ግብጽ ባለሙያዎችን እንዲሰይሙ የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጠየቀ።

ሚኒስትሩ ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂ.) ለአገራቱ የውሃ ጉዳዮች ሚኒስቴሮች በጻፉት ደብዳቤ ላይ ቀጣይ ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራው በመጪው የክረምት ወራት ውስጥ እንደሚከናወንና ከዚህ በፊት በተደረሰው ስምምነት መሰረት አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት እንዲቻል ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ በታላቁ የሕዳሴው ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ ሂደት ላይ ለዓመታት ሲያካሂዱት የነበረው ድርድር ቀጣይ ዙር ተካሂዶ ያለውጤት ከተጠናቀቀ ከቀናት በኋላ ነው ኢትዮጵያ ግብዣውን ያቀረበችው።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ለሦስት ቀናት የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር በሆነችው በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሰብሳቢነት ኪንሻሳ ውስጥ የተካሄደው ድርድር ያለ ውጤት ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ ስለሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ሱዳንና ግብጽ መረጃ ለመለዋወጥ እንዲያመች ባለሙያዎቻቸውን እንዲያሳውቁ ጠይቃለች።

ከኢትዮጵያ በኩል የቀረበው ጥሪ የሦስቱ አገራት ገለልተኛ ብሔራዊ የሳይንስ ቡድን አማካይነት በተደረሰው ስምምነት በወጣው ግድቡን በውሃ የመሙላት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት መሆኑን ገልጾ፤ የውሃ ሙሌቱም በሐምሌና በነሐሴ ወር የሚከናወን ሲሆን የዝናቡን ሁኔታ ከግምት በማስገባትም የመስከረም ወርን ሊጨምር እንደሚችል አመልክቷል።

የሕዳሴ ግድብ የደረሰበትን ግንባታ ሂደትና የውሃ ሙሌቱ የሚካሄድበት የኢትዮጵያ ክረምት ወቅት መቃረቡን በመጥቀስ ተግባራዊ ጉዳዮች ዙሪያና በአስፈላጊ የግንኙነት መስኮች ላይ በጋራ የመሥራትን አስፈላጊነትን የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል።

ሱዳንና ግብጽ ለመረጃ ልውውጥ አስፈላጊ የሆኑ ባለሙያዎችን መሰየማቸው በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የሚካሄደው የሦስትዮሽ ድርድር መቋጫ አስኪያገኝ ድረስ አስፈላጊ የመረጃ ልውውጥ መስመርን ለማመቻቸትና መተማመንን ለመገንባት ይጠቅማልም ብሏል ሚኒስቴሩ።

ከዚህ ቀደም ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የግድቡን ውሃ ሙሌት ከማከናወኗ በፊት ሕጋዊና አሳሪ ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት ሲጠይቁ ቢቆዩም ይህ በኢትዮጵያ በኩል ተቀባይነትን አላገኘም።

ባለፈው ማክሰኞ ካለውጤት ከተጠናቀቀው የኪንሻሳው ድርድር በኋላ የኢትዮጵያ ውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የግድቡን አሞላል፣ ውሃ አያያዝ እንዲሁም አለቃቀቅን በተመለከተ ከስምምነት ለመድረስ ኢትዮጵያ ዝግጁ እንደሆነች ጠቅሶ ነበር።

ነገር ግን ግብጽና ሱዳን "ድርድሩ የኢትዮጵያን የውሃ ድርሻ የሚገድብና አለን የሚሉትን የውሃ ክፍፍል የሚያፀ አስገዳጅ ስምምነት ካልተደረሰ የሚል አቋም በመያዛቸው" ከውጤት አለመደረሱን ገልጿል።

ጨምሮም ግብጽና ሱዳን በተደጋጋሚ ሲሉት የነበረውን አስገዳጅ ስምምነት ሳይደረግ የግድቡ ሙሌት መከናወን የለበትም የሚለው ሃሳብ "የሕግ መሠረት የሌለውና ኢትዮጵያ የላትን የተፈጥሮ ሃብት የመጠቀም መብት የሚጋፋ በመሆኑ ተቀባይነት የለውም" በሚል ውድቅ አድርጋጎታል።

ግንባታው ከተጀመረ አስረኛ ዓመቱን የያዘው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና ቀጣይ የሥራ ሂደትን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብጽ መካከል ለዓመታት ሲካሄድ የቆየው ድርድር ውጤት ሳያስገኝ እስከአሁን ዘልቋል።

የአፍሪካ ሕብረት የሚያሸማግለው ይህ ድርድር ቀደም ሲል በአዲስ አበባ፣ በካርቱም፣ በካይሮና በዋሽንግተን ላይ የሦስቱ አገራት ልዑካን ተገናኝተው ሲካሄድ የቆየ ሲሆን በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መከሰት ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በበይነ መረብ አማካይነት ቀጥሎ ነበር።

ኢትዮጵያ አምስት ቢሊየን የሚጠጋ ዶላር አውጥታ እየገነባችው ያለው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሊጠናቀቅ 20 በመቶ ያህል የቀረው ሲሆን፤ የግድቡ ግንባታ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ካሉ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ሁሉ ቀዳሚው ይሆናል ተብሏል።

ግድቡ ተጠናቅቆ ሙሉ ለሙሉ ሥራውን ሲጀምር ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም አለው።

ግድቡ ባለፈው ዓመት የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ያደረገ ሲሆን ሁለተኛውን ዙር ደግሞ በመጪው ክረምት እንደሚከናወን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቋል።

ወደ 80 በመቶ የሚጠጋው የግድቡ የግንባታ ሥራ መከናወኑ የተነገረ ሲሆን በመጪው ዓመትም በተወሰነ ደረጃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይጀምራል።

ግብጽና ሱዳን ግድቡ የውሃ አቅርቦታችንን በከፍተኛ ደረጃ ይቀንሰዋል በሚል ከግንባታው መጀመር አንስቶ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቢቆዩም፤ ከግማሽ በላይ ለሚሆነው ሕዝቧና እያደገ ላለው የኢንዱስትሪ ዘርፏ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ዋነኛ ግቧ አድርጋ የተሳችው ኢትዮጵያ በግንባታውና ቀጥላ ወደ ማጠናቀቁ ተቃርባለች።

የግብጽና የሱዳን መንግሥታት ከፍተኛ ባለስልጣናት በተለያዩ አጋጣሚዎች ኢትዮጵያ እየገነባችው ባለው ግድብ ሳቢያ አገሮቻቸው ከወንዙ በሚያገኙት የውሃ መጠን ላይ የሚፈጠርን ማንኛውም ተጽእኖ እንደማይቀበሉት ሲገለጹ ቆይተዋል።

የግብጹ ፕሬዝዳንት አቡዱል ፋታህ አል ሲሲም በዚህ ሳቢያ 'የከፋ አካባቢያዊ ችግር' ሊፈጠር ይችላል ሲሉ መስጠንቅቃቸው ይታወሳል።

ፕሬዝዳንቱ "ማንም ከግብጽ ውሃ ላይ አንዲት ጠብታ መውሰድ አይችልም፤ ይህ ከሆነ ደግሞ ከሚታሰበው በላይ አደገኛ አለመረጋጋት በአካባቢው ይፈጠራል" ብለው ነበር።

ኢትዮጵያ ግድቡን የምትጠቀመው ውሃውን በግዛቷ ውስጥ ለሚያስቀሩ ፕሮጀክቶች እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ብታስረዳም ሱዳን በተለይም ግብጽ የትኛውም አይነት በውሃው ላይ የሚከናወን ሥራ የእነሱን ስምምነት ሳያገኝ መካሄድ እንደሌለበት ሲገልጹ ቆይተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ በአገሪቱ ምክር ቤት ላይ ባደረጉት ንግግር "ውሃ አሞላሉን በተመለከተ ተደራድረን ስናበቃ እንሙላ ካልን ክረምቱ ያልፍና በዓመት 1 ቢሊየን ዶላር እናጣለን" ሲሉ የውሃ ሙሌቱን ማዘግየት እንደማይቻል አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር የሆኑት ስለሺ በቀለ (ዶ/ር፣ ኢንጂ.) ኢትዮጵያ ወደ መጠናቀቁ የተቃረበውን የሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በምንም ዓይነት መልኩ እንደማታራዝመውና ለዚህም የሚያበቃ አሰራርና ምክንያትም እንደሌለ ተናግረዋል።