የአረብ ሊግ በግድቡ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን በመቃወም ኢትዮጵያ ለጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጻፈች

ሕዳሴ

የፎቶው ባለመብት, @seleshi_b_a

የአረብ ሊግ በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን በመቃወም ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ጻፈች።

የውጪ ጉዳይ ሚንስትር በማኅበራዊ ድረ ገጾቹ ይፋ እንዳደረገው፤ ኢትዮጵያ የአረብ ሊግ አገራት በግድቡ ጉዳይ ጣልቃ መግባታቸውን ትቃወማለች።

ሊጉ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ አስገብቶ የግድቡን ግንባታ በተመለከተ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቋል። ይህንን የአረብ ሊግ ጥያቄ ተከትሎ ኢትዮጵያ ጥያቄውን በመቃወም ለጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ ማስገባቷ ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትርና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንን ትላንት ሰኔ 28/2013 ዓ. ም. ለጸጥታው ምክር ቤት በጻፉት ደብዳቤ፤ የአረብ ሊግ የሕዳሴ ግድቡን በተመለከተ የጣልቃ ገብነት መብት ሳይኖረው ለተባበሩት መንግሥታት ደብዳቤ በመጻፉ ኢትዮጵያ ተቆጥታለች ብለዋል።

"የአረብ ሊግ አገራት አባይን በተመለከተ ግብፅ የምትለውን ማንኛውንም ነገር ሳያመዛዝኑ ሲቀበሉ የመጀመሪያቸው አይደለም" ይላል የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ያወጣው መግለጫ።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን የታላቁ ሕዳሴ ግብድ ግንባታን በተመለከተ በአፍሪካ ሕብረት አማካይነት የሦስትዮሽ ውይይት እያደረጉ ባሉበት ወቅት የአረብ ሊግ ጣልቃ ገብነት ተገቢ አለመሆኑ ለጸጥታው ምክር ቤት በተጻፈው ደብዳቤ ተጠቁሟል።

የአረብ ሊግ የሚከተለው መንገድ በአፍሪካ ሕብረት እና በሊጉ መካከል ያለውን ወዳጅነት እንዲሁም ትብብር አደጋ ውስጥ የሚጥል እንደሆነም ተመልክቷል።

"የአፍሪካ ሕብረት የኢትዮጵያ፣ የግብፅ እንዲሁም የሱዳንም ነው። ሁሉም አካል ተጠቃሚ መሆን በሚችልበት መንገድ ላይ የሦስትዮሽ የድርድር መድረክ ዘርግቷል። ይህም ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የሚለውን ብሂል የተከተለ ነው" ይላል ደብዳቤው።

ኢትዮጵያ በዚህ የሦስትዮሽ ድርድር ውስጥ የአፍሪካ ሕብረትን አሸማጋይነት በመከተል እንዲሁም በበጎ ምልከታ ድርድሩ ውጤት እንዲያመጣ ቁርጠኛ መሆኗን ያተተው ደብዳቤው፤ ግብፅ እና ሱዳንም ሂደቱን እንዲያከብሩ አሳስቧል።

ግብፅ እና ሱዳን የድንበር ዘለል ውሃ ሀብት አጠቃቀምን በተመለከተ ዓለም አቀፍ ሕግጋትን እንዲያከብሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊገፋፋቸው እንደሚገባም ኢትዮጵያ ጠይቃለች።

ከዚህ ቀደም ሱዳን እና ግብፅም የአረብ ሊግ አገራት ግድቡን በሚመለከት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ግብፅ እና ሱዳን የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስለ ግድቡ ጉዳይ እንዲወያይ ቢጠይቁም፤ ምክር ቤቱ ሦስቱን አገራት በመጥራት ስጋታቸውን እንዲገልጹና ወደ ስምምነት ሊያደርሳቸው ወደሚችለው ድርድር እንዲመለሱ ከማበረታታት ውጪ ሊያደረግ የሚችለው ነገር እንደሌለ ከቀናት በፊት መገለጹ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት መጀመሯን ተከትሎ ግብፅ የቀጠናውን መረጋጋት አደጋ ላይ የሚጥል እርምጃ ነው ብላ ተቃውማለች።

የግብፅ የመስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብደል አቲ፤ የውሃ ሙሌቱ እንደተጀመረ የሚገልጽ ይፋዊ ደብዳቤ ከኢትዮጵያ እንደደረሳቸው አመልክተው ውሳኔውን ግን አንቀበለውም ብለዋል።

ሚኒስትሩ ለተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ እንደጻፉም ተዘግቧል።