ኢትዮጵያ፤ ግብጽ እና ሱዳን ወደ ድርድሩ እንዲመለሱ ግፊት እንዲያደርግ የጸጥታው ምክር ቤትን ጠየቀች

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጥላ ስር ሕብረት በሚካሄደው የሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ግብጽና እና ሱዳን እንዲመለሱ ግፊት እንዲያደርግ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤትን ጠይቃለች።
ኢትዮጵያ ይህንን በይፋ የጠየቀችው ለጸጥታው ምክር ቤት ባስገባችው ደብዳቤ እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ዲና ሙፍቲ በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች ባደረጉት መግለጫ አስታውቀዋል።
ግብጽና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ሙሌትና አጠቃላይ አሰራር ወደተጀመረው የሦስትዮሽ ድርድር እንዲመለሱና የአፍሪካ ሕብረትን ሂደት እንዲያከብሩ የጸጥታው ምክር ቤት ግፊት ሊያደርግ ይገባል ብላለች።
ከቀናት በፊት ባስገባችው ደብዳቤ ግብጽ እና ሱዳን በግድቡ ሁሉም ተጠቃሚ የሚሆንበትን ሳይሆን በአቋማቸው እንደጸኑና በሌላ መልኩ በተጣደፈ መልኩና በኢትዮጵያ ላይ ያልተገባ ተፅእኖ በመፍጠር ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው ለማድረግ አገራቱ እየሰሩ ነው ማለቷን ቃለ አቀባዩ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ደብዳቤውን ያስገባችው መጋቢት 8/2013 ዓ.ም ሲሆን ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላትን አቋም በተመለከተ በዝርዝር አስፍራለች።
ለዓመታት ሲካሄድ የነበረው የሦስትዮሽ ድርድር ፍሬ ሳያፈራ ቀርቶ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር እንዲካሄድ መደረጉ ይታወሳል።
በአፍሪካ ሕብረት መሪነት ሲካሄድ የነበረው ድርድርም የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ሙሉ ድጋፍ ያልተለየው መሆኑን ያስታወሰችው ኢትዮጵያ "ለአፍሪካዊ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሔን መሻት" በሚል መርህና መንፈስም መሆኑን ጠቅሳለች።
በአፍሪካ ሕብረት በሚደረገው በዚህ ድርድር ላይ ሙሉ እምነት እንዳላት የምትገልፀው ኢትዮጵያ የሕብረቱ የቀድሞ ሊቀመንበርነትን ስፍራ ይዛ የነበረችው ደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የአሁኑ ሊቀ መንበር ዲሞክራቲክ ኮንጎ "ለአህጉሪቷ ችግር አህጉራዊ መፍትሔ" መፈለግ በሚል መንገድ ያደረጉትን ጥረትም ያላትን ምስጋና ችራለች።
በመጪው ክረምት የውሃ ሙሌቷን ለማከናወን በዕቅድ ላይ ያለችው ኢትዮጵያ ከዚያ በፊት ግን በሕዳሴ ግድቡ ላይ መረጃ መለዋወጥ ያስችል ዘንድ ባለሙያዎች እንዲያቀርቡ ለሁለቱ አገራት ጥሪ ብታደርግም ውድቅ አድርገውታል ትላለች።
"ሁለቱ አገራት አሳሪ ስምምነት እስኪደረስ ድረስ በሚል ሽፋን" የላይኛው ተፋሰስ ኢትዮጵያን በግድቡ እንዳትጠቀም ለማድረግና ለዓመታት የቆየውን ኢ-ፍትሃዊ የውሃ አጠቃቀም ለማስፈን የሚደረግ ሩጫ ተቀባይነት እንደሌለውም አፅንኦት ሰጥታለች።
ኢትዮጵያ በሦስቱ አገራት የተፈረመውና በመርሆች ስምምነት መመሪያዎችና ሕጎች በዋናነት እየተመራች እንደሆነና ከዚያ ውጭ በሆነ ሁኔታ ግን ኢትዮጵያ ላይ የሚደረግ ጫናም ሆነ በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ስር የሚደረገውን የሦስትዮሽ ድርድር ወደ ጎን ለማድረግ የሚካሄድ ሂደት በሦስቱ አገራት ላይ መተማመንን ያጠፋል ትላለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃለ አቀባይ ከሕዳሴ ግድብ በተጨማሪ ጎረቤት አገር ሱዳን ጋር የተነሳውን የድንበር ውዝግብ አስመልክቶ ወቅታዊ ሁኔታዎችን ለጋዜጠኞቹ አስረድተዋል።
የሱዳን መንግሥት 61 የኢትዮጵያ ወታደሮችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለኢትዮጵያ ባለስልጣናት እንዳስረከበ ቢያስታውቅም ኢትዮጵያ በበኩሏ ሱዳን እንደምትለው ወታደሮች አይደሉም፤ በተቃራኒው ከነዚህ ውስጥ 59 አርሶ አደሮች እንደሆኑና ሁለቱ ደግሞ የአካባቢው ሚሊሺያ ናቸው ብለዋል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ወታደራዊ የአፀፋ ምላሽ በሌለበት ሁኔታ የሱዳን መንግሥት የኢትዮጵያ ወታደሮችን በቁጥጥር ስር አውያለሁ በማለት ኢትዮጵያ በድንበር ግጭቱ ላይ እየተሳተፈች ነው ለማለትና ዓለምን ለማሳሳት የሚደረግ ነው በማለት ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሬት ላይ ያለው እውነታ የሚለው በሁለቱ አገራት ጦርነት እንዳልተካሄደና በተፃራሪው የሱዳን ወታደሮች የኢትዮጵያ አርሶ አደሮችን ከቦታቸው አፈናቅለውና ንብረታቸውን ዘርፈዋል ብሏል።
ኢትዮጵያ ከሱዳን ጋር ምንም አይነት ወታደራዊ ግጭት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግ አፅንኦት የሰጠው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በአንፃሩ በሰላማዊ መንገድ ሁኔታዎች እንዲፈቱና ወደ 1972 የአገራቱ መግባባቶች እንዲመለሱ ትፈልጋለች በማለት የአገሪቷን አቋም አስታውቋል።












