ታፍኖ የተወሰደው አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል የት እንዳለ አለመታወቁን በመቃወም ኢትዮጵያውያን በናይሮቢ ሰልፍ አካሄዱ

የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶችም በናይሮቢ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል
የምስሉ መግለጫ, የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶችም በናይሮቢ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል

በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከወራት በፊት ታፍኖ የተወሰደው አቶ ሳምሶን ተክለሚካኤል የት እንዳለ እስካሁን ድረስ አለመታወቁን በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ።

ከሦስት ወራት በፊት ከናይሮቢ ጎዳና ላይ ባልታወቁ ሰዎች ከመኪናው እንዲወርድ ተደርጎ ከተወሰደ በኋላ እስካሁን ያለበት ያልታወቀው በንግድ ሥራ የሚተዳደረው አቶ ሳምሶን ጉዳይ ያሳሰባቸው ቤተሰቦቹ፣ ጓደኞቹ እንዲሁም ሌሎችም በናይኖቢ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ናቸው ሰልፉን ያካሄዱት።

'ፍትሕ ለሳሚ'፣ 'ሳሚ የት ነው?'፣ 'ባለቤቴ ሳሚ የት ነው?'፣ 'ጓደኛዬ ሳሚ የት ነው?' እና 'አጎቴ ሳሚ የት ነው?' የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን ይዘው ኢትዮጵያውያኑ ሰልፍ ወጥተዋል።

የአቶ ሳምሶን ባለቤት ወ/ሮ ሚለን ሃለፎምን ጨምሮ የሃይማኖት አባቶች እና ወጣቶችም በናይሮቢ አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን አሰምተዋል።

አቶ ሳምሶን በዚህ ዓመት ኅዳር መጀመሪያ ላይ ነበር በናይሮቢ ከተማ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከመንገድ ላይ በኃይል ከተወሰደ በኋላ እስካሁን ድረስ ያለበት አልታወቀም።

በወቅቱ በመንገደኞች ተቀርጾ በማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት በተሰራጨ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ የትራፊክ ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሰ ግለሰብ ባለበት ሲቪል የለበሱ ሰዎች አቶ ሳምሶን ሲያሸከረክረው ከነበረው መኪና በኃይል ጎትተው ወደ ሌላ መኪና ሲወስዱት ታይቷል።

ኬንያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኬንያ መንግሥት አቶ ሳምሶን ያለበትን ቦታ በግልጽ እንዲያሳውቅ ከዚህ ቀደም በይፋ ጠይቋል።

የአቶ ሳምሶን ባለቤት ወ/ሮ ሚለን ሃለፎም ሰልፉ ላይ ተገኝታለች
የምስሉ መግለጫ, የአቶ ሳምሶን ባለቤት ወ/ሮ ሚለን ሃለፎም ሰልፉ ላይ ተገኝታለች

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ መለስ ዓለም "የኬንያ መንግሥት እና የሕግ አካላት ሳምሶን የት እንዳለ እንዲያሳውቁን ጠይቀናል" ሲሉ ለኬንያ መገናኛ ብዙኃን መግለጫ መስጠታቸው አይዘነጋም።

ጨምረውም "ኅዳር ላይ የተፈጠረው ክስተት ኢትዮጵያን አስደንግጧታል። በጠራራ ፀሐይ፣ ፖሊስ ባለበት፣ ኪሌሌሽዋ በተባለው ሰፈር ውስጥ ነው የተፈጠረው። ከዚያን ጊዜ አንስቶ የኢትዮጵያ ዜጋ የሆነውን ሳምሶን ተክለሚካኤል አላየለነውም" ብለዋል።

"በማኅበረሰቡ ዘንድ በብዙዎች የሚከበር ሰው እንደመሆኑ ድንገት መጥፋቱ አገሩ ኢትዮጵያን ጎድቷል" ሲሉም አምባሳደሩ ለኬንያ መንግሥት ተናግረዋል።

'ፍትሕ ለሳሚ'፣ 'ሳሚ የት ነው?'፣ 'ባለቤቴ ሳሚ የት ነው?'፣ 'ጓደኛዬ ሳሚ የት ነው?' እና 'አጎቴ ሳሚ የት ነው?' የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን ይዘው ኢትዮጵያውያኑ ሰልፍ ወጥተዋል
የምስሉ መግለጫ, 'ፍትሕ ለሳሚ'፣ 'ሳሚ የት ነው?'፣ 'ባለቤቴ ሳሚ የት ነው?'፣ 'ጓደኛዬ ሳሚ የት ነው?' እና 'አጎቴ ሳሚ የት ነው?' የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን ይዘው ኢትዮጵያውያኑ ሰልፍ ወጥተዋል

አቶ ሳምሶን ታፍኖ የተወሰደ ሰሞን የኬንያ ፖሊስ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለው እንደሆነ የገለጸ ቢሆንም፤ እስከ ዛሬ ድረስ ግን ከኬንያ ፖሊስም ሆነ ከኬንያ መንግሥት በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።

ከወራት በፊት ከቢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረገችው ወ/ሮ ሚለን ባለቤቷ በጋዝ ሽያጭ የንግድ ሥራ ላይ ተሰማርቶ እንደሚገኝ እና ታፍኖ ከመወሰዱ ቀደሞ ዛቻም ሆነ ማስፈራሪያ ደርሷቸው እንደማያውቅ ተናግራለች።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, ከቀናት በፊት በኬንያ ናይሮቢ የታገተው የሳምሶን ተ/ሚካኤል ጉዳይ እጅጉን እንዳሳሰባት ባለቤቱ ሚለን ሃለፎም ለቢቢሲ ተናግራለች።