ከበርካታ ወንዶች ጋር ተፎካክራ በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛ ነጥብ ያስመዘገበችው ሴት ተማሪ ማናት?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተናን ከ350 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተፈትነው ውጤታቸውን ማወቅ ችለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛው ውጤት የቅዱስ ዮሴፍ ተማሪ ብሩክ ባልካቸው 669 አስመዝግቧል። ሁለተኛ የወጣው ደግሞ የኤክዜል አዳማ ተማሪ የሆነው ናኦል በለጠ 665 አምጥቷል።
እንደ ኤጀንሲው መረጃ ከ1ኛ እስከ 14ኛ ደራጃ የሚይዘውን ከፍተኛ ውጤት ያመጡት በሙሉ ወንዶች ናቸው።
በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ 15ኛ የሆነቸው ሰዓዳ ጀማል ከሴት ተማሪዎች ቀዳሚዋ ናት። ሁለተኛ ደግሞ ቤዛዊት ብርሐኔ ስትሆን የክሩዝ ትምህርት ቤት ተማሪ መሆኗን የኤጀንሲው መረጃ ያሳያል።
ሰዓዳ ጀማል ማን ነች?
ሰዓዳ ጀማል ለቤተሰቦቿ የመጀመሪያ ልጅ ነች።
ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግራለች። ገና ታዳጊ እያለች ትምህርቷን ከተማው ላይ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች መማሯን ታስታውሳለች።
"እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ የተማርኩት አልቀለም የሚባል ትምህርት ቤት ነበር፤ ጎበዝ ተማሪ ነበርኩ" ትላች ሰዓዳ።
ከ5ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ወራቤ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ደግሞ በስልጤ ልማት ማኅበር የተቋቋመው ሃይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምራለች።
የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የሆነችው ሰዓዳ፣ ሃይረንዚ አዳሪ ትምህርት ቤት ተምራ ከፍተኛውን ውጤት ለማስመዝገብ በቅታለች።
በመጀመሪያ ደረጃም ሆነ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶቿ የደረጃ ተማሪ እንደነበረች የምታስታውሰው ሰዓዳ 10ኛ ክፍል 4 ነጥብ በማምጣት በክልል እና በትምህርት ቤቷ የገንዘብ እና የሜዳሊያ እንዲሁም የተለያዩ ስጦታዎች ተበርክተውላታል።
"10ኛ ክፍል 4 ነጥብ አምጥቼ ሳልፍ 2 ሺህ ብር ክልሉ ሸልሞኛል። ከትምህርት ቤቴ ደግሞ የተለያዩ ሽልማቶች እና ሜዳሊያ አግኝቻለሁ።"
ለእህት ወንድሞቿ ሁሌም መልካም አርዓያ መሆኗን የምትናገረው ሰዓዳ፤ 11ኛ ክፍል የሚማረው ወንድሟ ጥሩ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ትናገራለች።
የፈተና ውጤቷን የሰማች ዕለት
ሰዓዳ የምታውቀው ዘንድሮ በተሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃትን ጥሩ ውጤት ማምጣቷን እንጂ ብሔራዊ ፈተናው ከሴቶች አንደኛ መሆኗን የሰማችው ከቢቢሲ ነው።
የቢቢሲ ጋዜጠኛዋ የምትነግራትን ማመን አልቻለችም። ድምጿ ውስጥ የሚፍለቀለቅ ሳቅ ሞልቶ "በጣም ነው ደስ ያለኝ፤ ለመጀመሪያ ጊዚ ካንቺ መስማቴ ነው" ስትል መለሰች።
ሰዓዳ በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ካመጡ ተማሪዎች ስሟ በ15ኛ ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው፤ ከፊቷ የሚገኙ 14 ወንዶች ናቸው። እርሷ በአስራ አምስተኛነት ስትመጣ 650 ነጥብ አስመዝግባ ነው።
በዚህም ደስታዋን ስትገልጽ፤ "ከፍተኛ ውጤት አመጣለሁ ብዬ ጠብቄ ነበር ግን ከሴቶች ቀዳሚ እሆናለሁ አላልኩም" ብላለች።
ባለፈው ዓመት መሰጠት የነበረበት የ12ኛ ክፈል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተራዝሞ ነበር።
በኋላ ላይ ፈተናው በታብሌት ይሰጣል ተብሎ ሲጠበቅ ሌላ መዘግየት ተፈጠረ። በስተመጨረሻም ተማሪዎቹ በወረቀት እንዲፈተኑ ተወስኖ የካቲት መጨረሻ ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ 350 ሺህ ተማሪዎች ፈተናውን ወሰዱ።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው ተማሪዎች ዓመቱን ሙሉ አልተማሩም። ነገር ግን መምህሮቿ የተለያዩ አጋዥ ማስታወሻዎችን በቴሌግራም ይልኩላቸው እንደነበር ሰዓዳ ገልጻለች።
የሚያስፈልገኝ ነገር ሲኖር መምህራኖቼን ትምህርት ቤት ውስጥ በማንኛውም ሰዓት አገኛቸዋለሁ። ርዕሰ መምህራችንም በምክር ያበረታታኝ ነበር ብላለች።
ሰዓዳ "የፈተናው በተደጋጋሚ መራዘም ከባድ ነበር፤ ተስፋ ያስቆርጣል። በኋላ ላይ የሚመጣውን ውጤት እያሰብኩኝ ራሴን ሳዘጋጅ ነበር" ትላለች።
የፈተናው መራዘም ላይ በርካታ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች እንደነበሩ የምታስታውሰው ሰዓዳ፤ ሁሌም ግን ወደፊት ያለውን ብሩህ ተስፋ በማሰብ ንባቤን እቀጥል ነበር ብላለች።
መምህራኖቿ በተለያየ ጊዜ እርሷ እና ጓደኞቿን እንዲያጠኑ፣ ተስፋ እንዳይቆርጡ እና እንዳይዘናጉ ምክር እንደሰጧቸውም ትናገራለች።
የፈተናው ውጤት በተገለጸበት ጊዜ በአጋጣሚ አያቷ ጋር የነበረችው ሰዓዳ ማለፊያ ነጥብ ማስመዝገቧን ስታውቅ መጀመሪያ የተናገረችው ለአያቷ ነበር።
ከዚያ በኋላ ለእናትና ለአባቷ እንዲሁም ለጓደኞቿ ደውላ መናገሯን ትገልጻለች።
ወላጆቿም በውጤቷ ከመደሰት ባሻገር "ከዚህ በላይ እንጠብቃለን" ማለታቸውን ትናገራለች።
ሰዓዳ ቤት ውስጥ ጫና የለባትም። እናም ወላጆቿ ሁልጊዜም ከፍተኛ ውጤት እንድታመጣ ያበረታቷት፣ እንድታጠናም ሁኔታዎችን ያመቻቹላት እንደነበር ገልጻለች።
ትምህርቷን ዘወትር በክፍል ውስጥ በሚገባ መከታተሏ፣ ፈተና ሲደርስ ከማንበብ ይልቅ ከስር ከስር ማጥናት መምረጧ ጥሩ ውጤት እንድታመጣ አግዟታል።
"ፈተና ሲደርስ ማንበብ በሚገባ ሳይረዱ ወደ ፈተና መግባት ስለሚያስከትል ምርጫዬ አይደለም" በማለት ከፈተና በፊት ቀድሞ ማጥናት ልማዷ ማድረጓን ተናግራለች።
"ፈተና ኖረም አልኖረም ማንበብ እወዳለሁ፣ ለማወቅ በሚል ነው የማነበው።"
ከጓደኞች ጋር ስላነበበቻቸው ነገሮች መወያየት፣ መምህራኖቿንም በየጊዜው እንደምትጠይቅም ገልጻለች።
ሕክምና ማጥናት የምኞቷ የሆነው ሰዓዳ በዚሁ መስክም በከፍተኛ ውጤት ተመርቃ ማኅበረሰቧን እና አገሯን ማገልገል የወደፊት ምኞቷ ነው።













