በ23 ዓመቱ የህክምና ትምህርቱን ያጠናቀቀው ዶ/ር አቤኔዘር ብርሃኑ

የፎቶው ባለመብት, Abenezer Birhanu
ጓደኞቹ 'ጢቆ' ይሉታል- ትንሽ እንደማለት። አንዳንዶች ደግሞ ያንግ [Young] የሚል ቅፅል አክለው 'ዶ/ር ያንግ' እያሉ ይጠሩታል። እናቱ በቤት ስሙ 'ቤቢ' ነው የሚሉት።
የህክምና ዶክትሬቱን ያጠናቀቀው በ23 ዓመቱ ነው። በተለመደው የእድሜ አሰላል እዚህ ማዕረግ ላይ ከሚደረስበት በሦስት ዓመታት ያንሳል።
ዶክተር አቤኔዘር ብርሃኑ።
እናቱ መምህር፤ አባቱ ደግሞ የህክምና ባለሙያ ናቸው። ወላጆቹ ሥራ ላይ ስለሚውሉ በርካቶች የሚፈተኑበት ሁነኛ የልጆች ሞግዚት እጦት የእነርሱንም ቤት አልዘለለም።
ይሁን እንጅ እናቱ ሥራቸውን ለመልቀቅም ሆነ፤ ልጃቸውን ለጎረቤት አደራ ብለው መተው አልተዋጠላቸውምና ከእርሳቸው ጋር ትምህርት ቤት ይዞ ለመሄድ መፍትሔ ሻቱ። ለቤተሰቡ ሦስተኛ ልጅ የሆነው አቤኔዘር ያኔ የ4 ዓመት ህፃን ነበር።
አቤኔዘርም ከእናቱ ጋር እየሄደ የፊደልን ገበታ በጠዋቱ መቁጠር ጀመረ።
በእርግጥ ታላላቆቹም እንደ እርሱ አይሁን እንጅ፤ አንደኛ ክፍልን የጀመሩት በ5 እና 6 ዓመት እድሜያቸው ነው። ታናናሾቹም እንዲሁ።
ታዲያ ቤተሰብ ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥር ያደርግላቸዋል።
በተለይ እናቱ መምህር በመሆናቸው ከእርሱ አስተማሪዎች ጋር በመነጋገር፤ ድክመቱን በመረዳት ለሚከብዱት የትምህርት ዓይነቶች አጋዥ መፅሐፍ በመግዛት፣ ከፍ ያሉ ጎበዝ ተማሪዎች እንዲያስተምሩት በማድረግ ይደግፉት ነበር።
ምክራቸውም አይለየውም። "የምትፈልጉትን ነገር መሆን ትችላላችሁ፤ ሁሉም ነገር ተሰጥቷችኋል" እያሉ ያበረታቷቸው ነበር። ይህ በሁሉም ልጆች ሕይወት ውስጥ ውጤት አሳይቷል።
አቤኔዘር የህልሙን ነው የሆነው። ፍላጎቱ በህክምና ሙያ ላይ መሰማራት ነበር።
አቤኔዜር ባደገባት ከሚሴ ከተማ በተለይ በወቅቱ የጤና መሠረተ ልማት የተሟላ አልነበረም። የህክምና ባለሙያዎችም እጥረት እንደዚያው። ታዲያ በዚያ የህክምና ባለሙያዎች ብርቅ በሆኑበት ወቅት፤ በአካባቢው የሚያያቸው ዶክተሮች ቀልቡን ይይዙት ነበር።
እኔም የእነርሱን ፈለግ መከተል አለብኝ አለ፤ ምሳሌዎቹም እነርሱ ሆኑ።
በእርግጥ ይህ ምኞት የእናቱም ይመስላል። አቤኔዘር እንዳጫወተን እናቱ ባለቤታቸው ሐኪም በመሆናቸውም ይመስላል ጥሎባቸው ሐኪም ይወዳሉ። እርሱም ዶክተር በመሆኑ እጅግ ደስተኛ ናቸው።
የፊዚክስና የሂሳብ ትምህርቶችን አብዝቶ የሚወደው አቤኔዘር፤ በህክምና ሙያ ላይ ባይሰማራ ራሱን መካኒካል መሀንዲስ ሆኖ ሊያገኘው እንደሚችል ይናገራል።
ግኝቶችን መፍጠር፣ ለሰዎች አስተዋፅኦ ማድረግን ይመኝ ነበር። ተግባር ለሚበዛባቸው ሙያዎች የተሰጠ ነው።
ይሁን እንጅ ህልሙ ተሳክቶለት ራሱን የህክምናው ሙያ ላይ አግኝቶታል።
"የልጅነት ጊዜ ጨዋታ. . ."
የልጅነት ጊዜ ጨዋታ አይጠገብም። እንኳንስ ልጅ ሆነውና አዋቂም ሆኖ ትዝታው አይለቅም። እድሉ ከተገኘ እርጅናም አያስቀረው። አቤኔዘር የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን የጀመረው በአራት ዓመቱ ነው- ጉልበቱ ሳይጠና፣ በመዋዕለ ህፃናት ትምህርትን ሳይለማመድ።
ታዲያ ልቡ ወደ ጨዋታው ያመዝን ነበር። በተለይ እግር ኳስን የሚያህልበት የለም። በሰፈራቸው ባቋቋሙት የእግር ኳስ ቡድን ጎል ጠባቂ ነበር። "ለቡድኑ እጅግ አስፈላጊ ሰው ነበርኩ" ይላል።
ቡድኑ በብቃቱ ስለሚተማመንበት፤ ከየትም ተፈልጎ ይመጣል እንጅ የእርሱን ምድብ የሚይዝ አልነበረም። በመሆኑም ራሳቸው ከቆርኪና ሽቦ የሰሩትን ዋንጫ በተደጋጋሚ አንስተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Dr Abenezer Birhanu
በእግር ኳስ ቡድናቸው ውስጥ የነበሩት ጓደኞቹ በትምህርታቸው ለስኬት የበቁ ናቸው። ትምህርቱን አቋርጦ አልባሌ የሕይወት መንገድ ላይ የቆመ እምብዛም የለም።
ይህ መሆኑም ለትምህርቱ ያለው ትኩረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብርታት ሆኖታል።
ከዚህም በተጨማሪ ከቤተሰብ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር ይደረግበት እንደነበር ያስታውሳል። "ጊዜህን በማይሆን ቦታ አታሳልፍ" የሚነገረው የዘወትር ምክር ነው። በትምህርቱ ጠንክሮ በ10ኛ ክፍል ትምህርቱ 4 ነጥብ ነበር ያስመዘገበው።
12ኛ ክፍልም ላይ ያስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ ነበር። ጂማ ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ሲገባ የ16 ዓመት ታዳጊ ነበር።
በዚህ እድሜው ከቤተሰብ ተነጥሎ ሲወጣ የመጀመሪያ ጊዜው በመሆኑ ውስጡን ፍርሃት ገብቶት ነበር። ይሁን እንጅ ቀደም ብሎ ታላቅ ወንድሙ እዚያው ዩኒቨርሲቲ ተመድቦ ስለነበር ጭንቀቱን አቅልሎለታል፤ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴው ከጎኑ አይጠፋም።
እንደ ህፃን ነበር የሚንከባከበው።
በተለይ ተማሪዎች፣ መምህራን እና የጥበቃ ሠራተኞቹ እንደ ተማሪ ስለማያምኑት በወጣ በገባ ቁጥር እነርሱን ማስረዳቱም ሌላ ጣጣ ነበር።
ይህ ብቻም ሳይሆን መንገዱን የሚያስቱ አሉታዊ የአቻ ግፊቶች እዚያም አልጠፉም፤ ነገር ግን ራሱን በመቆጠቡና ጓደኞቹን በመምረጡ መሰናክሎቹን አልፎ ከዓላማው እንደደረሰ ያስረዳል።
"ሰውን በገፁ መፅሐፍትን በሽፋናቸው. . ."
ሰዎችን በአለባበሳቸው፣ በሰውነት አቋማቸው፣ በመልካቸው፣ ባላቸው የሐብት መጠን፣ እንዲሁም በእድሜያቸው ማንነታቸውን የመለካት ግምታዊ አስተሳሰብ በማህበረሰብ ዘንድ ሰርጎ የገባ አጉል ልማድ ይመስላል።
በተለያዩ ጊዜያትም በተለይ ወጣት አመራሮች ከሚያነሱት ችግር አንዱ ለሥራ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ አመኔታ መነፈጋቸው ነው።
አቤኔዘርም የዚሁ አስተሳሰብ ዳፋ ከሚያርፍባቸው ወጣቶች አንዱ ነው። ለዚህ ማሳያ በርካታ ገጠመኞች ቢኖሩትም፤ ለአብነት አንዱን ያስታውሳል።
ነገሩ እንዲህ ነው። አንዲት ታማሚ ለሕክምና ክትትል ወደ ሐኪም ቤት ትሄዳለች። በወቅቱ አቤኔዘር ከአንድ ጓደኛው ጋር በመሆን ሥራው ላይ ተሰይሟል። ወደ ጤና ተቋሙ ለመጣችው ታማሚ ባልደረባው ምርመራውን ካደረገ በኋላ፤ መድሃኒት እንዲፅፍላት ለእርሱ ይነግረዋል።
ታማሚዋ ግን በእርሱ ላይ እምነት አልጣለችበትም ነበር። "ህፃን እኮ ነው! ሊሳሳት አይችልም ወይ?" ስትል አመነታች። ያኔ ሴትዮዋን ለማሳመን በርካታ ጥረቶች እንዳደረገ የሚዘነጋው ጉዳይ አይደለም።
እርሱ እንደሚለው የሰውን ማንነት መረዳት የሚቻለው በሚሰራው ሥራ፣ ባለው እውቀት እና በሙያው መሆን አለበት።
በተለይ እርሱ በተሰማራበት የሕክምና ሙያ ከህሙማን ጋር የሚኖራቸው ግንኙነት በመተማመን ላይ የተመሰረተ መሆን አለበት። ህክምናው የሚጀምረውም በመተማመን ላይ በመመስረት ነው።
አመኔታ ከሌለ ውጤቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚያሳድር ሰዎች በአካል፣ በቁመና እና በዕድሜ ሳይሆን በተሰጣቸው ሙያ፣ በሚሰሩት ሥራ ሰውን መመዘን እንደሚገባ ያስረዳል።
"ወደፊትም መሰል ፈተናዎች ሊገጥሙኝ ይችላሉ" የሚለው አቤኔዘር፤ ፈተናዎቹን ለመጋፈጥ ግን መዘጋጀቱን ያስረዳል።
ቀጣይ ጉዞ
ከአንድ ወር በኋላ በሕክምና ዶክትሬቱን የሚቀበለው የ23 ዓመቱ አቤኔዘር፤ ወደፊት በቀዶ ህክምና ስፔሻላይዝ የማድረግ ፍላጎት አለው። ቀዶ ህክምና የተለየ ክህሎት የሚጠይቅ በመሆኑና ክህሎትን የሚጠይቁ ሥራዎች ላይ ፍላጎት ስላለው ለዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ፍላጎት አለው።
ጅማ ዩኒቨርሲቲ በሚሰራበት ወቅትም በዘርፉ ላይ የሰዎች እጥረት መኖሩን በመረዳቱ፤ የበኩሉን ለማበርከት የተቻለውን እንደሚያደርግ ሃሳብ ሰንቋል።
















