የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ

የሙዚቃ ህክምና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሙዚቃ ጥበብ ነው፤ ስሜት ያድሳል፤ ሕመምን ይሽራል። እንኳን ሰው እንስሳትና እፅዋት በሙዚቃ ይደሰታሉ። ለዚህም ነው ያደጉት አገራት ሙዚቃን አንደ አንድ የሕመም መፈወሻ መድሃኒት እየተጠቀሙበት ያለው።

ታዲያ ይህ የሕክምና ጥበብ ወደ እኛ አገርም ተሻግሯል። አሻጋሪው ደግሞ ዶክተር መልካሙ መዓዛ ናቸው።

በቅዱስ ያሬድ ዘመን ሰዎች ሙዚቃና ቅዳሴን በመጠቀም የታመመ ሰውን ስቃይ በመቀነስ ለታማሚው ምድራዊ ገነትን ለመፍጠር ሲጠቀሙበት ነበር።

በህዳሴ ዘመን ደግሞ የሙዚቃ ሐኪሞች የስሜታችንና የሰውነታችን ተፈጥሯዊ ለውጦችን ለማምጣት ሙዚቃን ለሳይንሳዊ ጥናት እንደተጠቀሙበት ዶ/ር መልካሙ ያስረዳሉ።

አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ ሙዚቃና ሕክምና እጅግ ተሳስረዋል። በተለይ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ የጤና ተቋማት ሙዚቃን እንደ ደጋፊ የሕክምና ግብዓት እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።

ዶ/ር መልካሙ "ሙዚቃ ጤናን አስቀድሞ ለመጠበቅ እና ከህመም ለመዳን አስተዋፅኦው ከፍተኛ ነው" ይላሉ።

ዶ/ር መልካሙ የሙዚቃ አድናቂ ናቸው። ክራር፣ ጊታር፣ ፒያኖና ቶም የተባሉ የሙዚቃ መሳሪያዎችን ይጫዎታሉ። ድፕ አቢሲኒያ (ትራይባል ማጂክ) የተሰኘ የሙዚቃ አልበምም አሳትመዋል።

የቀዶ ሕክምና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር መልካሙ፣ የሙዚቃ ዝንባሌ ያደረባቸው ከዛሬ ስድስት ዓመት በፊት በግላቸው ባጋጠማቸው ችግር ምክንያት እንደሆነ ይናገራሉ።

በሥራቸውና በቤተሰባቸው አካባቢ ችግር ገጥሟቸው ለጭንቀት ተዳርገው ነበር። ከዚህ ለመሸሽ ወደ ሙዚቃ ቀረቡ። የሚነጋገሩትም፣ የሚያዋዩትም ሙዚቃን ሆነ። በጊዜ ሒደትም ከገቡበት ስሜት እየተላቀቁ መጡ።

የሙዚቃን ኃያልነት ከራሳቸው ተሞክሮ የተረዱት ዶ/ር መልካሙ፣ ለሌላው ሰው ለመትረፍ አብዝተው ማሰብ ጀመሩ።

በምዕራቡ ዓለም የተለመደውን የሙዚቃ ሕክምና ሳይንስን ለማጥናትና ዘርፉ ላይ ለመስራት ወሰኑ፤ ያሳቡትም ተሳካ።

ለመሆኑ የሙዚቃ ሕክምና እንዴት ይሰጣል?

ዶ/ር መልካሙ የሙዚቃ ሕክምና የሚሰጥባቸውን ሁለት መንገዶች ያብራራሉ።

አንደኛው በተቋማት ያሉ ባለሙያዎች ሙዚቃን በመጠቀም ደጋፊ ወይም አማራጭ ሕክምና የሚሰጡበት ዘዴ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በማሕበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የሙዚቃ ሕክምና ነው።

በማሕበረሰብ ውስጥ የሚደረግ የሙዚቃ ሕክምና ግን በማከም ሳይሆን በመከላከል ደረጃ የሚሰጥ ነው።

የሕክምናው ዓይነትም በየቤቱ ታመው የተቀመጡና ማሕበረሰቡ ጋር የማይቀላቀሉ ሰዎች በሕይወታቸው ላይ ተስፋ እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚሰጥ የሕክምና ዓይነት እንደሆነ ዶ/ር መልካሙ ያብራራሉ።

አሁን ግን የጥናት ውጤቶችን መሠረት በማድረግ ሕክምናው ከሌሎች የሕክምና ሙያ ዓይነቶች ጋር ተቀናጅቶ እየተሰጠ ይገኛል።

የሙዚቃ ሕክምና የእድሜ ገደብ የለውም። ለሕፃናትም ሆነ ለአዋቂዎች ይሰጣል።

በተለይ የአዕምሮ ዕድገት ውስንነት፣ የባህሪ ችግር፣ የአካል ጉዳት፣ የስሜት መረበሽ፣ መናገር፣ ማየትና መስማት ለተሳናቸው፣ የነርቭ እክል ላጋጠማቸው፣ ቀዶ ሕክምና ላደረጉ፣ ለካንሰር ህሙማን፣ የአልኮልና አደንዛዥ ዕፅ ተጠቂ ለሆኑ፣ ወሲባዊ ጥቃት ለደረሰባቸው እንዲሁም የአመጋገብ ችግር ላለባቸው ይሰጣል።

በተጨማሪም ለእናቶች በቅድመ ወሊድ፣ በወሊድ ወቅት እና ከወሊድ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ሕክምናው ሊሰጥ ይችላል ።

ዶ/ር መልካሙ እንደሚሉት ሙዚቃ በአንጎል ውስጥ የሚገኙ ዶፓሚንና ሴሮቶኒን የተባሉ ሆርሞኖች በተለያየ ሁኔታ እንዲመነጩ ስለሚያደርግ በሰው ልጆች ተግባቦት፣ ማሕበራዊ መስተጋብር፣ የሰውነት እንቅስቃሴ፣ የስሜት ህዋሳት፣ የሥነ-ልቦና እና የስሜት ለውጥ ላይ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋል።

ሕክምናው በዋናነት በግል ወይም በቡድን የተቀዳን ሙዚቃ አሊያም የሙዚቃ ሐኪሞች የሚጫወቱትን ማዳመጥ፣ ማንጎራጎር፣ በግል ወይም በቡድን ሐኪም በሚያዘው መሰረት ሙዚቃን መጫወት እና የምት (ሪትም) እንቅስቃሴ ማድረግን ያካትታል።

የሚያክሙን ሙዚቃዎች ዓይነት

ዶ/ር መልካሙ እንደገለጹት ለሙዚቃ ሕክምና የትኛውም ዓይነት ሙዚቃ ጥቅም ላይ አይዉልም። ታካሚው ላጋጠመው የህመም ዓይነት የተዘጋጁ የሙዚቃ ዓይነቶች ያስፈልጋሉ።

ከእነዚህም መካከል ቀደም ብለው የተቀዱ ሙዚቃዎች አሊያም ሐኪሙ በቀጥታ ለታካሚው የሚጫወታቸው ሙዚቃዎች ሊሆኑ ይችላሉ።

''እነዚህ ሙዚቃዎች ታካሚው እንዳለበት የህመም ዓይነትና እንደሚያስፈልገው ሕክምና በምት፣ በቅጥነት፣ በውፍረት፣ በፍጥነት፣ በድምፅ ከፍታና ዝቅታ በተለያየ መልኩ ሊዘጋጁ ይችላሉ።

"በአብዛኛው ክላሲካል የሚባሉት ሙዚቃዎች ለሕክምና ይውላሉ" ይላሉ ዶ/ር መልካሙ።

የሞዛርትንና የቤትሆቨንን ሙዚቃዎች በመጥቀስም ቆየት ባለው ጊዜ የነበሩት እነዚህ ረቂቅ (ክላሲካል) ሙዚቃዎች በሰው ልጆች ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ሙዚቃዎች መሆናቸውን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ ጤና ላይ አዎንታዊ ጠቃሜታ ያላቸው ሙዚቃዎች እንዳሉ ሁሉ ጤናን የሚያውኩ ሙዚቃዎችም አሉ።

"በአጠቃላይ ጠንካራ ምት፣ ንዝረትና ፍጥነት ያላቸው እንደ ሮክ፥ ድራም፥ ባዝና ትራንስ ያሉ የሙዚቃ ዓይነቶች ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጥናቶች አመልክተዋል" ይላሉ።

በሰው ልጆች ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ እነዚህ ያሉ ሙዚቃዎች የሚሰሙበት አካባቢ ያሉ እፅዋቶች ሳይቀሩ እድገታቸው እንደሚቀጭጭ ዶ/ር መልካሙ ጥናቶችን አጣቅሰዋል።

የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ

ሳይንሳዊ የሆነው የሙዚቃ ሕክምና በኢትዮጵያ ገና በጅማሮ ላይ ያለ ነው።

ከቅርብ ዓመታት በፊት ከጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የሙዚቃ ሕክምናን የሚመለከት አንድ የሥራ ሂደት ተቋቁሞ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለጹት ዶ/ር መልካሙ፣ በገፈርሳ የአዕምሮ ህሙማን ማገገሚያና ማከሚያ ማዕከል ውስጥ በሳምንት ለሦስት ቀናት የሙዚቃ ሕክምና በተለይ የምት እንቅስቃሴ ሕክምና መሰጠት መጀመሩን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ እንደ ሌሎች ሕክምናዎች ሁሉ የሙዚቃ ሕክምና ባለሙያ ቢያስፈልገውም በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ባለመኖራቸውና በሌሎች ወቅታዊ ምክንያቶች ውጤቱ አርኪ እንዳልነበር ይገልጻሉ።

ሆኖም የተጀመረው እንቅስቃሴ ሕክምናውን ለማስጀመርና በሰዎች ዘንድ ግንዛቤ ለመፍጠር የተደረገ ጥረት እንደሆነ ያምናሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት እንቅስቃሴው የሙዚቃ ሕክምና ባለሙያን ከውጭ አገር በማስመጣት ድጋፍ እንዲገኝም መንገድን አመቻችቷል።

እንግሊዝ አገር ከሚገኝ 'ሚዩዚክ አዝ ቴራፒ' ከተሰኘ ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በተፈጠረ ግንኙነት የሙዚቃ ሕክምና በባለሙያ የሚታገዝበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዝግጅት እያደረጉ እንደሆነም ዶ/ር መልካሙ ተናግረዋል።