የማይክል ጃክሰን "የአፍጢም ዳንስ" ምሥጢር

የፎቶው ባለመብት, MANJUL TRIPATHI
የአከርካሪና ህብለ-ሰረሰር ቀዶ ጥገና ጠበብት የማይክል ጃክሰንን የምትሀት ዳንስ ለመተንተን በአያሌው ሞክረዋል።
በተለይም "ስሙዝ ክሪሚናል" በሚለው ሙዚቃው ላይ የሚያሳየው ሰዋዊ ያልሆነ መጥመልመል እንዴት ሊያሳካው ቻለ የሚለው ጥያቄ ሳይንሳዊ ምላሽ ሳያገኝ ከርሞ ነበር።
በ1987 (እአአ) በለቀቀው የሙዚቃ ሥራው ማይክል በ45 ዲግሪ ወደፊት በማዘንበል የማይቻል የሚመስል እንቅስቃሴ አድርጎ ዓለምን አስደምሞ ነበር።
እርግጥ ነው "ኢሉዥን" በተሰኘው ሙዚቃው የሚያሳየውን እንቅስቃሴ ብዙዎች ደግመውታል። እንዲያውም እሱኑ ለማስመሰል እምብዛምም አልተቸገሩም።
የ"ስሙዝ ክሪሚናል" ዳንስ ግን እስከዛሬም የሚሞከር አልሆነም።
የህብለ-ሰረሰር ጠበብት የማይክልን አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ተራ ሰዎች እንዳይደፍሯቸው ጭምር ያሳስባሉ።
በሕንድ የድኅረ ምረቃ ሕክምና ትምህርት ቤት ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ማንጁል ትሪፓቲ ባሳተሙት የጥናት ጆርናል እንደጠቆሙት፤ አብዛኞቹ ሥልጡን ተወዛዋዦች ወደፊት ማዘንብል የሚችሉት ከ20-30 ዲግሪ ብቻ ነው።
ማይክል ግን ጀርባው ሳይተጣጠፍ በ45 ዲግሪ ለጥ ብሎ ፊት ለፊት ሳይወድቅ ማዘንበል ይችላል። ይህ ሳይንሳዊ አልሆን ብሏቸዋል፤ ተመራማሪዎቹን።
ማይክል ታዲያ እንዴት ተሳካለት?
እነዚህ ተመራማሪዎች እንዳረጋገጡት ከሆነ የማይክልን "ስሙዝ ክሪሚናል" የተሰኘ የዳንስ ስልት ሌላ ማንኛውም ሰው ቢሞክረው በአፍጢሙ ሊደፋ ይችላል።
በማይክል ቁመናና ሰውነትን የማዘዝ ክህሎት ላይ የሚገኙ ቀልጣፋ ሰዎች እንኳን 45 ዲግሪ ወደፊት ማዘንበልን ሊያሳኩት አይችሉም። ምክንያቱም ነገርዬው ከመሬት ስበት ሕግ የሚቃረን ተግባር ነውና።
ማይክል ከ30 ዲግሪ በላይ ማዘንበል ያስቻለው ለዚሁ የተዘጋጀ ቅንጡ ጫማ በማጥለቁ ብቻ ነው ይላሉ ተመራማሪዎች።
በእንግሊዝኛዋ የ"ቪ" ፊደል ቅርጽ የተሰነጣጠቁት የጫማው የውስጠኛው ክፍል ማይክልን በአፍጢሙ ከመደፋት ያድኑታል። ልክ ለመንሸራተት በሚችል ቁልቁለት ላይ ያለ መኪና የፊት ታኮ እንደሚገባለት ሁሉ ማለት ነው።
ይህንን ጫማ የሚያቀርብ ሁነኛ ኩባንያ ከመምጣቱ በፊት ማይክል ወገቡ ላይ በሚታሰርና ከካሜራ ዕይታ በሚሰወር ገመድ ላይ ጥገኛ ሆኖ ቆይቷል።
እሱና ሁለት የሆሊውድ ወዳጆቹ ይህንን የጫማ ሐሳብ ያገኙት የሥነ-ከዋክብት ተመራማሪዎች ከሚያጠልቁት ልዩ መጫሚያ እንደሆነ ይነገራል።
ይህ ጫማ ከተጣበቀና ለዚሁ ተብሎ ከተዘጋጀ የጫማ ሀዲድ ጋር በመሆን የመሬት ስበት ዜሮ በሚሆንበት ሁኔታ ዘንበል ብሎ ላለመውደቅ የሚረዳ ነበር ተብሏል፤ በወቅቱ።
ያም ሆኖ ይላሉ ተመራማሪዎች፤ ይህንንም ልዩ ጫማ ተጫምቶ 45 ዲግሪ ማዘንበል ጠንካራ የጀርባ አጥንት፣ ተጣጣፊ ሰውነትና በአግባቡ የጎለበተ ጡናቻን መታደል ያሻል።
በርካታ የማይክል አድናቂዎች እና ይህንን ጥናት በጆርናል ያሳተሙ ሐኪሞች ጭምር ይህንን እንቅስቃሴ "የማይቻል" ሲሉ ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል።
ሌሎችም እንዳይሞክሩት በማሳሰብ ጭምር።
ዶክተር ትሪፓቲ እንደሚሉት ይህንን "የአፍጢም ዳንስ" የሚሞክሩ ደፋሮች መጀመርያ የሚያጋጥማቸው የቁርጭምጭሚት ወለምታ ነው፤ ከፍ ሲልም በአፍጢማቸው የመደፋት።












