ዝነኛው ኤርትራዊ ድምጻዊ የማነ ባርያ ሲታወስ

የማነ ባርያ

የፎቶው ባለመብት, Ftisum

በኤርትራዊያን ዘንድ ተጠቃሽ ከሆኑት ድምፃዊያን መካከል አንዱ የሆነው የማነ ገብረሚካኤል (የማነ ባሪያ) ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ ሁለት አስርት ዓመታት አለፉ። የቢቢሲ ትግርኛዋ ኤደን ሃብተሚካኤል የድምጻዊውን ህይወትና ሥራዎች ቃኝታ ነበር።

የማነ ገብረሚካኤል (ባርያ) በ1949 ኤርትራ ውስጥ ተወለደ። ኪነ-ጥበብ አብራው እንደተወለደች የሚያሳብቅበት ገና የሰባተኛ ክፍል ተማሪ እያለ ወደ መድረክ መውጣቱ ነበር።

ታድያ የዚያን ጊዜ አባቱ አቶ ገብረሚካኤል ብስራት "እኔ አዝማሪ ሆኖ ከሚቀር ትምህርቱን ተከታተትሎ ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስልኝ በመመኘት፤ ላስቆመው ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር፤ ሆኖም ግን ሳይሳካልኝ ሲቀር እብድ ነው ብዬ ተውኩት" ብለው ነበር።

እናቱ ወይዘሮ አዜብም በእሱ የተነሳ ቤተሰቡ ውስጥ ብዙ አለመስማማት እንደነበር ያስታውሳሉ።

ዝነኛው ከያኒ የማነ ባርያ ብዙ ጊዜ ግጥሞቹን የሚጽፋቸው ካየው፣ ከሰማውና ወቅታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ተንተርሶ እንደሆነ በተለያዩ ጊዜያት ይናገር ነበር።

"በድንገት ሄደች፤ አላውቅም የት እንዳለች፤ ወሰዱብኝ ሉላየን፤ ምወዳትን" የተሰኘች ሙዚቃውን እንደለቀቀ ለእሥር ተዳረገ። ጉዳዩ በፖለቲካ ተመነዘረበት። በወቅቱ ጉዳዩን የያዙት ዳኛ ነገሩ ለሞት ሊያደርሰው እንደሚችል ቢናገሩም፤ በሚወዱትንና ጥበቡን በሚያፈቅሩ ሰዎች ጉትጎታ ከእሥር ሊፈታ ቻለ።

በጊዜው በነበረው የፖለቲካ ግለት ምክንያት እንደፍላጎቱ ማቀንቀን ባለመቻሉ ለኤርትራ ነጻነት የተጀመረውን ትግል ተቀላቀለ።

በስደት ወደ ሱዳን ከሄደም በኋላ፤ የተቸገሩ ስደተኞች በመርዳት ቤቱን መጠለያ እስከማድረግ ደርሶ ነበር። እርሱ እንደ ትልቅ ነገር ባይቆጥረውም በእርሱ እርዳታ ያን ጊዜ አልፈው ነብሳቸውን ማዳን፣ ኑሯቸውን ማስተካከል የቻሉ ስደተኞች ግን "የድሃ አባት" የሚል ስም እንደሰጡት ይናገራሉ።

የማነ ባርያ፤ የገጠማቸውና የተጫወታቸውን ዜማዎች ለአድማጭ ጆሮ ግቡ የሆኑ፤ ከእዝነ ሕሊና የማይጠፉ እና ጥልቅ መልዕክት ያዘሉ ናቸው። በሌሎች ተደግመው ሲሰሩ መስማት ባያስከፋ እንኳ፤ ለእሱ ብቻ የተፈጠሩ የሚመስሉ ዜማዎቹን ከሌሎች አንደበት መስማት ለጆሮ እንደሚከብድ አድናቂዎቹ ይናገራሉ።

የማነ ባርያ

የፎቶው ባለመብት, Fitsum

"ዘመን ተለወጥክብኝ፤ ከቤቴ አስወጣኽኝ፤

ስደተኛ ሆንኩኝ፤ አገር እንደሌለኝ፤

የልብ የማላደርስ ሰነፍ፤ አደረግከኝ መና፤ ህዋ ላይ ምንሳፈፍ፤

ክብሬን ገፈህ ለዚህ ዳረግከኝ፤ ምክንያቱ ምንድን ነው፤ ዘመን መልስልኝ'' ሲል ያቀነቀናት ዘፈኑ በብዙዎች ዘንድ አሁንም እንደ አዲስ ትነሳለች።

የማነ፤ የእኔ የሚለው ምንም ነገር ሳይኖረው ሌሎችን ለመርዳት ወደኋላ ያለማለቱን ምክንያት ሲጠየቅ፤ መልሱ አጭር ነበር "ሃብቴ ህዝቤ ነው" የሚል። ለዚህም የማነ፤ ከስደት መልስ አሥመራ ገብቶም በኪነ-ጥበብና በለጋስነቱ በሕዝብ ልብ ውስጥ መንገስ የቻለ የጥበብ ሰው ነበር።

ወርሃ ኅዳር፤ 1989 ከዚህች ዓለም በሞት የተለየው የማነ ባርያ ግብዓተ መሬቱ ሲፈፀም ቤቱ የቀረ የአሥመራ ነዋሪ ያለ አይመስልም ነበር። "አባቴ፤ ወንድሜ" ብሎ የሚያነባ እንጂ እንደ ባዳ ጥግ የቆመ ሰው አይታይም ነበር። ማነው የቅርብ ዘመድ? የቱስ ነው ቤተሰብ? ለማወቅ ያዳግት ነበር።

ዝነኛው ኤርትራዊ ድምጻዊ አብራር ዑስማን ሰለየማነ ሲያወሳ "ሳዑዲ አብረን ሳለን ለሰዎች ያደርግ የነበረውን ነገር ሳይ፤ ለእርሱ ያለኝ አክብሮት ይበልጥ ጨመረ" ይላል።

የጥበብ አጋሮቹ ስለየማነ አውርተው የሚጠግቡ አይመስሉም፤ ድምፃዊ ተስፋለም ቆርጫጭ "በዕድሜ ዘመኔ እሱን በአካል ለመተዋወቁ ዕድል ባላገኝም፤ በጥበብ በኩል ስለማገኘው እጽናናለሁ" ይላል።

ከሰባት በላይ አልበሞችና በመቶዎች የሚቆጠሩት የሙዚቃ ሥራዎቹን ያበረከተው የማነ ካረፈ እነሆ 21 ዓመታት አለፉ። ይሁን እንጂ ባምደ-ወርቅ የዘገበው ጥበቡ፤ የአድማጭን ጆሮ የገዛበት፤ ህዝቡን ሃብቱ ያደረገበት ሙዚቃ ሕያው ሆኖ ይኖራል።