ኤርትራዊያን በጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት ጉዳይ ለምን ይቋሰላሉ?

የፎቶው ባለመብት, Martin Plaut
ማርቲን ፕላውት ጋዜጠኛ ነው።
ደቡብ አፍሪካ የተወለደ እንግሊዛዊ ይሁን እንጂ በሚያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ለኤርትራዊያን ይቀርባል።
ሁልጊዜም ታዲያ በኤርትራዊያን ፖለቲካ ውስጥ የውዝግብ ምንጭ እንደሆነ አለ። ጀግናችን የሚሉት እንዳሉ ሁሉ ደመኛችን የሚሉትም ጥቂት አይደሉም። ከነዚህ 'ጥቂት አይደሉም' ከሚባሉት ውስጥ ያዕቆብ ገብረመድኅን ይገኝበታል።
ባለፈው ዓርብ 8፡00 ሰዓት ስለሆነው ነገር ማርቲን ለቢቢሲ ሲያስረዳ እንዲህ የይላል "ያዕቆብ ነኝ ከሚል ሰው ጥሪ ደረሰኝ፤ ከኤርትራ የወጡ ጠቃሚ መረጃዎች አሉ፣ ላቀብልህ አለኝ። መረጃዎቹ ይጠቅሙኛል ብዬ ስላሰብኩ ቀጠሮ አደረግን። ብሪቲሽ ላይብረሪ እንድንገናኝ ተነጋገርን። መልሶ ደወለና ከላይብረሪው ውጭ ብንገናኝ ይሻላል አለኝ። ከአቅራቢያ ባለች ካፌ ተገናኘን። ቡና አዘዘ። ትንሽ ቆይቶ ተነሳና በቅርብ ርቀት አስቀምጦት የነበረን አንድ ባልዲ አንስቶ እላዬ ላይ ደፋብኝ..."
ማርቲን ለቢቢሲ ጨምሮ እንዳስረዳው ጥቃት አድራሹ ኤርትራዊ ድርጊቱን በሚፈጽምበት ወቅት "አንተ ከሃዲ፣ በእንግሊዝና በአሜሪካ የተገዛህ! የኤርትራ ጠላት..." እያለ ይጮኸ ነበር።
ይህ ኤርትራዊ ወጣት ለዚህ ድርጊት ምን አነሳሳው? አቅዶ፤ እንቁላል በወተት ሊጥ አቡኪቶ፣ በባልዲ ጭኖ እንዲህ ዓይነት ድርጊት ለመፈጸም ያበቃው ቁጣ ከየት መጣ?
የማርቲንና የኤርትራ ዕውቂያ
ማርቲን ፕላውት አምስት መጻሕፍትን አበርክቷል። ከእነዚህ ውስጥ ምዕራቡ ዓለም "የአፍሪካ ሰሜን ኮሪያ" ስለሚላት ኤርትራ የጻፈው 'Understanding Eritrea' ይጠቀሳል። በምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች የእንግሊዝ ውጭ ጉዳይና የኮመንዌልዝ ቢሮ አማካሪም ነበር።
ለግዙፍ መገናኛ ብዙኃን በደቡብና በምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ ጉዳዮች እንደ ተቀዳሚ ተንታኝ የሚታየው ማርቲን ከኤርትራ ጋር ያለው ዕውቂያ ሩብ ክፍለ ዘመንን የሚሻገር ነው።
እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1984 ለቢቢሲ ይዘግብ ነበር። ከዚያ በፊት ግን በብሪታኒያ ሌበር ፓርቲ ውስጥ የአፍሪካ ተመራማሪና ጸሐፊ ኾኖ አገልግሏል። ከኤርትራና ከኤርትራዊያን ጋር ያስተዋወቀውም ያ ዘመን ነው።
በፈረንጅ በ70ዎቹ መጨረሻና በ80ዎቹ መባቻ ሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ ቅልጥ ያለ ትግል ላይ ነበር። ያን ጊዜ የግንባሩ የአውሮፓ ተወካይ ኤርሚያስ ደበሳይ (ፓፓዮ) ማርቲንን አፈላልጎ ያገኘዋል። ማግኘት ብቻም ሳይሆን የኤርትራ በረሃን እንዲጎበኝ ይጋብዘዋል። የሌበር ፓርቲው ማርቲን ፈራ ተባ እያለ ግብዣውን ተቀበለ።
በሱዳን በኩል አሳብሮ ኤርትራ ገባ፤ ሻዕቢያ በረሃ ይዞት ወረደ። በረሃ ብዙ ተመለከተ። የመጀመርያውን የኤርትራ የሴቶችና የሠራተኞች ጉባኤን ጭምር ሌበር ፓርቲን በመወከል ተሳተፈ።
ከ1984 ወዲህ ለቢቢሲ መሥራት የጀመረው ማርቲን ኤርትራን በድጋሚ የመጎብኘት ዕድሎች አጋጥመውታል። ነጻ የወጡ የሻዕቢያ የሚቆጣጠራቸውን ግዛቶችን ቃኝቷል። የከረን ምሽጎችን ተሽሎክሉኮባቸዋል። ኤርትራ ቤቱ ሆነች።
ያኔ በዚያ ዘመን ታዲያ ማርቲን ከሻዕቢያ የላዕላይ አመራር ጋር የቅርብ ወዳጅነት እንደፈጠረ ይገመታል። እሱም ቢሆን በቆይታዬ "በርካታ ወዳጆችን አፍርቻለሁ' ይላል።
ፓፓዮና ማርቲን
በትግል ስሙ ፓፓዮ (ኤርሚያስ ደበሳይ) ከሕዝባዊ ኤርትራ ሓርነት ግንባር ጎምቱ አመራሮች አንዱ ነበር። በትግሉ ወቅት የግንባሩ የአውሮፓ ተወካይ ሆኖ ሠርቷል። ከትግሉ በኋላም የማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና በድኅረ ነጻነት ኤርትራ በመወከል በኡጋንዳና በቻይና አምባሳደር በመሆን ለአጭር ጊዜ አገልግሏል።
ፓፓዮ ከዕለታት በአንዱ ቀን ወደ አገረ ኤርትራ ተጠራ። ታሰሮ ለአጭር ጊዜ ከእስር ተፈታ። በድጋሚ ከእህቱ ከሰናይት ደበሳይ ጋር ወደ እስር ቤት ተወረወረ። ከዚያ ወዲያ አልተመለሰም። ይሙት ይኑር አይታወቅም።
ፓፓዮ የፕሬዚዳንት ኢሳያስ የቅርብ ወዳጅና ምስጢረኛ እንደነበረ በስፋት ይነገራል።
ማርቲን ፕላውት ታዲያ የዚህ ኤርትራዊ ወዳጁ ለሁለት ዐሥርታት መታሰር በኤርትራ ጉዳይ ዝም እንዳይል ጉልበት ሳይሰጠው አልቀረም።
'ከአርብ ዕለቱ ጥቃት ወዲህ የኤርትራን ጉዳይ ታነሳለህ ወይ?' ተብሎ ከቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ፣ "... ፓፓዮ እስኪፈታ፣ የኤርትራ ሕዝብ የሚናፍቀውን ነጻነቱን እስኪቀዳጅ ድረስ በፍጹም ዝም አልልም" ሲል መልሷል።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
ጥቃት አድራሹ ማን ነው?
ያዕቆብ ድርጊቱን ሲፈጽም የሚያሳየው የተንቀሳቃሽ ምስል ባለፉት ቀናት በከፍተኛ ሁኔታ በማኅበራዊ ሚዲያ ተዛምቷል። ፖለቲካ ግድ የሚላቸው ኤርትራዊያንም እንደተለመደው በሁለት ጎራ ተሰልፈው ሲቆራቆሱ ታይተዋል። አበጀህ ያሉትን ያህል ዐይንህን ላፈር የሚሉትም በርካታ ናቸው።
ያዕቆብ ለዚህ ጥቃት ምን እንዳነሳሳው ለማወቅ ቢቢሲ እርሱን አግኝቶ ለማናገር ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ኾኖም ማርቲን በትዊተር ገጹ በኔዘርላንድስ የኤርትራ ኤምባሲ በጉዳዩ እጁ እንዳለበት የሚጠቁም መረጃ መስማቱን ጠቁሟል።
በኤርትራ ጉዳዮች ሐሰተኛ ዜናዎችን ያሰራጫል የሚል ተደጋጋሚ ክስ የሚቀርብበት ማርቲን "በመጀመሪያ ደረጃ ይህን ክስ የሚያቀርቡት የትኞቹ ኤርትራዊያን ናቸው?" ሲል ጥያቄውን በጥያቄ ይመልሳል።
የሆነስ ሆኖ ዲሞክራሲ ባለባት እንግሊዝ ጥገኝነት የጠየቀ አንድ ኤርትራዊ ይህንን ጥቃት በአገሬው ዜጋ፣ ለያውም በጋዜጠኛ ላይ ማድረሱ ምን ስሜት ሰጥቶት ይሆን?
"እኔ ጋዜጠኛ ነኝ፣ ሰው ነኝ፤ ልሳሳት እችላለሁ፤ በቻልኩት አቅም ሁሉ ግን መረጃን አቀርባለሁ። ሰዎች እኔ በማቀርበው መረጃ ላይስማሙ ይችላሉ፤ የመተቸት መብት አላቸው። ጥቃት የማድረስ መብት ግን የላቸውም" ይላል ማርቲን።
ጥቃት አድራሹ ወጣት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ በኋላ በዋስ ተለቋል። በዚህ የፈረንጆች ወር መጨረሻ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብም ይጠበቃል።












