የዩቲዩብ ከፍተኛ ተከፋይ፡ 22ሚሊዮን ዶላር የሚያገኘው የሰባት ዓመቱ ህፃን

የአሻንጉሊት ገምጋሚው ራያን

የፎቶው ባለመብት, YouTube

አሻንጉሊትን በመገምገም የሚታወቀው አሜሪካዊው የሰባት ዓመቱ ህፃን ራያን 22 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት የዩቲዩብን አንደኛ ክፍያ ስፍራ ተቆናጧል።

በፎርብስ መፅሔት ግምት መሰረት የራያን አሻንጉሊት ግምገማ ታዋቂውን ጄክ ፓውልን በ500 ሺ ዶላር በመብለጥ አንደኛ ሆኗል።

ይህም ከሰኔ ጀምሮ ባሉት አስራሁለት ወራት ውስጥ ነው።

የራያን ቪዲዮዎች በየቀኑ በዩቲዩብ ላይ የሚለቀቁ ሲሆን ትልቅና ሚስጥራዊ እንቁላልን ሲመረምር የሚያሳየው ቪዲዮ ከሚሊዮን በላይ ሰዎች ከእሁድ ጀምሮ ባለው ጊዜ ተመልክተውታል።

ዱድ ፐርፌክት የተባለው የዩቲዩብ ቻናል 20 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት ሶስተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱን የፎርብስ መረጃ ያሳያል።

ይህን ያህል መወደድና አድናቆትን ማግኘትን በቅርቡ ስምንት አመት የሞላው ህፃን እንዴት ያየዋል?

"አዝናኝና አስቂኝ ስለሆንኩ" ነው በሚል ለኤን ቢሲ ለተባለው ሚዲያ ምላሽ ሰጥቷል።

የራያን በዩቲዩብ ቪዲዮ የማሳየት ጉዞ የተጀመረው ከሶስት ዓመት በፊት በቤተሰቦቹ አማካኝነት ሲሆን፤ ቪዲዮዎቹ ከ26 ቢሊዮን በላይ ተመልካች ማግኘት የቻሉ ሲሆን 17.3 ሚሊዮን ተከታዮችንም አፍርቷል።

ፎርብስ በበኩሉ እንደተናገረው ከ22 ሚሊዮን ዶላሩ ላይ 1ሚሊዮን ዶላሩ ከቪዲዮው በፊት ከሚታዩ ማስታወቂያዎች የተገኘ ሲሆን ሌላው ቀሪው ደግሞ ከስፖንሰር ነው።

ምንም እንኳን ከስፖንሰር የተገኘው ገንዘብ ብዙ ቢመስልም ከሌሎች ዩ ቲዩብ ቻናሎች ጋር ሲወዳደር እምብዛም እንደሆነ ፎርብስ ፅፏል።

በራያን የዩቲዩብ ቪዲዮዎች ላይ የሚቀርቡት አሻንጉሊቶች ገበያ ላይ በፍጥነት ተሽጠው እንደሚያልቁም ተዘግቧል።

ከፍተኛ የዩቲዩብ ተከፋዮች

በነሐሴ ወር ዎልማርት የተባለው ትልቁ የገበያ ማዕከል የራያን አለም የሚል አሻንጉሊትና ልብሶች፣ ራያንና ቤተሰቦቹ በዎልማርት ውስጥ አሻንጉሊት ሲፈልጉ የሚያሳየው ቪዲዮ 14 ሚሊዮን ተመልካቾችን በሶስት ወራት ውስጥ አግኝቷል።

ከዎልማርት የሚገኘው ይህ ገቢም የራያንን የሚቀጥለው ዓመት ገቢውን ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ታዳጊ እንደመሆኑ መጠን ከአጠቃላይ ገቢው 15 % በባንክ ውስጥ የተቀመጠ ሲሆን የአዋቂነት ደረጃ ላይ ሲደርስ ገንዘቡን በፈለገው መንገድ መጠቀም ይችላል።

የራያን መንትያ እህት በአንዳንድ ቪዲዮዎች ላይ ትቀርባለች።

ሶስት ህፃናትን ያሳተፈውና "በቤት ውስጥ ለህፃናት መደረግ የሚችሉ አስር ሳይንሳዊ ምርምሮች" የሚል ርዕስ የተሰጠው ቪዲዮ 26 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።

በባለፈው ዓመት 16.5 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት አንደኛ የነበረው የቪዲዮ ጌም (ጨዋታ) ፈጣሪው ዳንኤል ሚድልቶን በዘንድሮው አራተኛ ደረጃን ይዟል።

ጄክ ፓውል ከስድስተኛ ወደ ሁለተኛ ሲመነጠቅ ወንድሙ ሎጋን ፓውል በ14.5 ሚሊዮን ዶላር ወደ አስረኛ ቦታ አሽቆልቁሏል።

ምንም እንኳን ይህ ገንዘብ ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር በሶስት ሚሊዮን ዶላር ቢበልጥም።

ሎጋን ፓውል በጥር ወር ላይ በሰራው የጃፓን ቪዲዮ ላይ ራሱን የገደለ ግለሰብ ቪዲዮ በማሳየቱ ይቅርታን ጠይቋል።

የዩቲዩብ ባለቤት ቪዲዮ ጉግል ውዝግቡን ተከትሎ ኩባንያዎች ማስታወቂያ ከሚሸጥበት ስፍራ ላይ ቪዲዮውን አስወግደውታል።