የእጮኝነት ቀለበት ሴቶችን እንዴት ይገልፃቸዋል?

Matilde Suescún

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ማቲልዴ ባታገባም ከሕይወት አጋሯ ጋር ነው የምትኖረው

ጥንዶች ወደ ትዳር ከመግባታቸው አስቀድሞ ለትዳር ይተጫጫሉ፤ መተጫጨታቸውን የሚያሳዩበት አንዱ መንገድ ደግሞ ለሴቷ ቀለበት ማድረግ ነው።

እዚህ ላይ ወንዱ በእጮኝነት ላይ እያለ ለምን ቀለበት አያደርግም? የሚል ጥያቄ ወደ እዕምሮዎ ይመጣ ይሆናል። በእርግጥ ወንዶች ፈርጥ ያለው፣ ያማረ፣ የእጮኝነት ቀለበት ለምን አያጠልቁም? ሴቶች ብቻ ለምን ያጠልቃሉ? የማቲልዴ ጥያቄ ነው።

የሚዲያ ባለሙያዋ ማቲልዴ ሱስከም ግን ይህ በባህላችን ለሴቶች የሚጠለቀው በጣም ውድ የሆነ የእጮኝነት ቀለበት ለሴቶች የውድቀትና የጥገኝነት ማሳያ ነው ትላለች።

እንዲህ ዓይነት ድርጊቶችም ሊያበቃላቸው ይገባል ስትልም በተደጋጋሚ ፅፋለች፤ መለወጥ ያለበት ልማድ ነው ስትል አበክራ ትሞግታለች።

ሁለት ጊዜ ትዳር መስርታ እንደነበርና ወደፊትም ልታገባ እንደምትችል የምትናገረው ማቲልዴ "መቼም ቢሆን ቀለበት አልፈልግምም፤ አላደርግምም" ትላለች።

ቀለበት ፀረ ሴቶች እንደሆነ ታምናለች፤ ጥገኛ ያልሆነች ሴት ላይ ያለውን አመለካከት የሚቃረን ነው፤ ይህም ማለት ቀለበቱን ያደረገችው ሴት የሌላ ናት ፤ተይዛለች የሚል መልዕክት አለው።

ከዚህም ባሻገር አቅምንና የኑሮ ደረጃን የምናሳይበት እየሆነ ነው፤ በአሜሪካ ሃገር ቀለበቱን ለመግዛት በአማካይ 6351 ዶላር ( 172 ሺህ ብር ገደማ) ያወጣሉ።

የአልማዝ ፈርጥ ያለው ትልቅ ቀለበት፤ ቀለበቱ ምን ያህል ውድ እንደሆነ ያመላክታል። በውስጠ ታዋቂ በምን ያህል እንደተሸጠች ያሳብቃል የምትለው ማቲልዴ በምትኖርበት አሜሪካ የሚኖሩት ጓደኞቿ በሙሉ ያላቸው አመለካከት ከእርሷ በተቃራኒ እንደሆነ ትናገራለች።

"አብዛኞቹ በእጮኝነት የተደረገላቸው የአልማዝ ቀለበት አላቸው፤ የአንዳንዶቹ ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት ትልቅ ነው። በኩራት ፎቶ እየተነሱ በየማህበራዊ ሚዲያው ይለጥፉታል፣ ይኩራሩበታል፤ ከእኔም ጋር ስንገናኝ ያሳዩኛል፤ ሰው እንዲያይላቸው ይፈልጋሉ" ትላለች።

ለእርሷ ግን የሚያስገርምና የሚያስቅ ጉዳይ እንጂ ምንም ደስታን የሚሰጥ አይደለም።

በእርግጥ ይህንን ሃሳቧን የሚቃወሙት በርሷ ዕድሜ የሚገኙ ጓደኞቿ ብቻ ሳይሆኑ ልጇም በአስተሳሰቧ ታሾፍባታለች። ምክንያቱ ደግሞ ወደ ፍቅር ዓለም ስትገባ እርሷም በጣም ውድ የሆነና አብረቅራቂ ቀለበት እንዲደረግላት ስለምትፈልግ ነው።

ድርጊቱ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣና ያደገችበት ባህል በመሆኑ የልጇን ሕልምና ሃሳብ ትረዳለች፤ ቢሆንም ግን በእዚህ አስተሳሰብ መቼም እንደማትስማማ ጠንካራ አቋሟ አላት።

ለጋብቻ አንድን ሰው እጩ የሚደረግበት የተለመደ ሥርዓት ያሰለቻታል፤ ባልየው በጉልበቱ ተንበርክኮ፣ የሚያጫትን ሴት እጅ ይዞ፤ 'ታገቢኛለሽ ?' የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ያስገርማታል።

ይህን ድርጊት የሚፈፅሙት ደግሞ ሰዎች በተሰበሰቡበት፣ ባልታሰበ አጋጣሚ፣ እርሷ ምንም መናገር በማትችልበትና እድል በማይሰጥበት ቦታ አሊያም በካሜራ ፊት በመሆኑ ሴቷን ተጋላጭ ማድረግ ለማቲልዴ ተቀባይነት የለውም።

ጋብቻ አንዱ ለአንዱ የሚያሳያው ሳይሆን የሁለቱ የጋራ ስምምነት መሆኑን እንደ ምክንያት ታስቀምጣለች።

"የቀድሞው ባለቤቴ የጋብቻ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ በተለመደው መልኩ ነበር፤ በወቅቱ ጣም ነበር ያሳቀኝ፤ ግን ያሰብነው አልሆነም፤ ጋብቻችን አልሰመረም፤ ምክንያቱም ዋናው ነገር ተግባቦት ነው " በማለት በቀለበት ሳይሆን የጥንዶቹ ውሳኔ ነው መሆን ያለበት ስትል ታክላለች።

ምንም እንኳን ብዙም ያልተለመደና ቁጥራቸው አናሳ ቢሆንም ተንብርክከው የጋብቻ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሴቶችም አሉ።

ቢሆንም ግን ማህበረሰቡም ሆነ ሚዲያ ሴቶች ህልም እንዲኖራቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ማስተማር እንዳለባቸው ታምናለች፤ ቀለበቱን አድርግላት (Put a ring on it) የሚለውን የቢዮንሴን ዘፈን እየሰሙ ያድጉና ጋብቻ ሁሉንም የሕይወታቸውን ችግር እንደሚፈታላቸው ያስባሉ።

ይሁንና ሴቶች ጋብቻንና ቀለበትን ከማለም ይልቅ ጥገኛ ላለመሆን፤ በትምህርት የተሻለ ስለመሆን፣ ስለ እድገት፣ እንዴት ደስተኛ ሊሆኑ እንደሚችሉ ቢያስቡ ይበጃል ስትል ታስረዳለች።

"አንዳንዴ ይሄን የሕይወት ፍልስፍናዬን በጋዜጣዎች አሊያም በድረ ገፆች ላይ ስፅፍ ሰዎች ቀንደኛ የሴቶች መብት ተሟጋች አድርገው ያስቡኛል" የምትለው ማቲልዴ አንዳንዶቹ እንደውም 'የፍቅር ጠር' እያሉ እንደሚጠሯት ትናገራለች። እርሷ ግን እንደ እኔ የፍቅር ሰው የለም ትላለች። የማትስማማበት ጉዳይ ቢኖር ቀለበት ይዞ ሊያጠልቅላት የሚመጣን ወንድ መጠበቁ ላይ ነው።

ጋብቻ አንድን ሰው ማፍቀርና ለፍቅሩም ተገዥ መሆን እንጂ ቀለበት ማጥለቁ ላይ አይደለም ትላለች።