በ12ኛ ክፍል ፈተና ከፍተኛውን ውጤት ያመጣው ተማሪ "ምን እንደምማር ግራ ገብቶኛል" ይላል

የፎቶው ባለመብት, FAMILY
ከክፍል 1ኛ መውጣት ያለ ነው። ከ"ሴክሽን" 1ኛ መውጣትም ያለ ነው። ከትምህርት ቤት 1ኛ መውጣትም ይኖራል። ከ350ሺህ ተማሪ መካከል 1ኛ መውጣት ግን. . . ።
ብሩክ ባልካቸው ይባላል።
ብዙም ማውራት የሚወድ ዓይነት ልጅ አይመስልም።
ለቢቢሲ የስልክ ጥያቄዎችን አሁን ለጊዜው ከሚገኝበት ሩዋንዳ፣ ኪጋሊ አጠር አጠር ያሉ መልሶችን ነበር የሚሰጠው።
ቁጥሩም፣ ውጤቱም፣ ክስተቱም፣ ታሪኩም፣ ወደፊቱም ብዙ የገረመው ልጅ አይመስልም። የስክነት ምንጣፍ ላይ የሚራመድ ብስልና ብልህ ነው ብሩክ። ወይም እንደዚያ ይመስላል።
ከብዙ ተማሪዎች ለየት የሚያደርጉት ባህሪዎች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።
ለምሳሌ ብዙዎችን የሚፈታተነው ሒሳብ ትምህርት "የሚያዝናናኝ የትምህርት ዓይነት እሱ ነው" ሲል ይገልጸዋል።
አንድ ተማሪ ከኳስ ቀጥሎ በሒሳብ ከተዝናና ያ ተማሪ የዋዛ እንዳልሆ መገመት ይቻላል።
ብሩክ የአዲስ አበባ ወጣት ግልብጥ ብሎ ኳስ ከሚጫወትበት መስቀል አደባባይ ጀርባ በሚገኘው የቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ተማሪ ነው።
ይሁን እንጂ ሰፈሩ ቤቴል ነው። እሱም እሑድ እሑድ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ሜዳ ይወጣል። ሜዳ ሲጠፋ አስፋልት ይወጣል። ኳስ ሊራገጥ።
ኳስ መጫወት ብቻም ሳይሆን አዘውትሮ ይመለከታል። ከትልልቆቹ ቡድኖች የአርሴናል ደጋፊ ነው። እንዴት ሊሆን ቻለ?
"አባቴ የአርሴናል ደጋፊ ስለሆነ እሱን ላግዘው ብዬ በዚያው የአርሴናል ደጋፊ ሆንኩ" ይላል።
አባቱ ዶ/ር ባልካቸው ንጋቱ የማህፀን ስፔሻሊስት ናቸው። "በማተርናል ፌታል ሚዲስን" ደግሞ ሰብ ሰፔሻሊስት ናቸው።
እናቱ ዶ/ር ሔለን ይፍጠርም ሐኪም ናቸው። የውስጥ ደዌ ሐኪም። የእርሳቸው ሰብ ስፔሻሊቲ ደግሞ ኢንዶክሪኖሎጂ ነው። ከእሳቸው ጋር ቆየት ብለን እናወጋለን። አሁን ወደ ብሩክ እንመለስ።
ብሩክ መጀመሪያ ውጤቱን የሰማበትን ቅጽበት ለቢቢሲ ሲያስታውስ "አባቴ ነው እስኪ ውጤት ከወጣ እንይ ብሎ…" በማለት ይጀምራል።
ረቡዕ ቀን ነበር።
ከአባቱ ከዶ/ር ባልካቸው ጋር ሶፋ ላይ ሆነው እየተጫወቱ በየመሀሉ ኢንተርኔት ይሞክራሉ። ውጤት ለማየት። ኢንተርኔቱም ሲስተሙም አስቸገራቸው። ደጋግመው ሲሞክሩት ግን ሠራ።
የውጤት ማወጂያ ድረገጹ የሁሉንም ትምህርት ጨምቆ ድምር ውጤት አይናገርም። ስለዚህ በተናጥል የየትምህርት ዓይነቶቹን ብቻ ነበር ማየት የቻሉት።
ብሩክ በዚያ ማለዳ ምናልባትም የአባቱን የዶ/ር ባልካቸውን ያህል አልጓጓ ይሆናል። ሆኖም 7ቱን የትምህርት ዓይነቶች በቃል ደመሯቸው። 669 መጣ።
ቁጥሩ በዝቶባቸው ይሆን? ወይም እርግጠኛ ለመሆን ብቻ ካልኩሌተር አስፈለጋቸው። የተለወጠ ነገር አልነበረም። 669!
ይህ ቁጥር ለብሩክ አዲስ ቁጥር አይደለም። ለምን? ከዚያ ቀደም ብሎ ይህን ቁጥር ያውቀዋላ። የአገሪቱ ከፍተኛው ውጤት 669 ነው ተብሎ ሲወራ ሰምቷላ!
የሚገርመው ግን ገና ውጤቱን ከማየቱም ቀደም ብሎ ይህ ትንግርቴ ቁጥር (magic number) የእሱ እንደሚሆንም ጠርጥሮ ነበር።
እንዴት ሊሆን ይችላል? ቢቢሲ የብሩክ ልበ ሙሉነት እንደዋዛ ሊስማማ አልቻለም። ሞግቶታል።
"ተው እንጂ ብሩክ! እንዴት ከ350ሺህ ተማሪ በላይ በተፈተነበት የአንድ አገር ብሔራዊ ፈተና ትልቁ ውጤት የእኔ ሊሆን ይችላል ብለህ ቀድመህ ልትገምት ትችላለህ?"
ብሩክ ነገሩን ለማስረዳት ሞከረ።
"አንደኛ ከዚያ በፊትም 'ውጤት ሳላይ ገና ጓደኞቼ ይሄ ትልቁ ውጤት ያንተ ሊሆን ይችላል' እያሉኝ ነበር"። ሁለተኛ ደግሞ ፈተናውን ስፈተን የከበደኝ አንድ የኬሚስትሪ ጥያቄ ብቻ ነበረች፤ ስለዚህ…" ይላል።
"እውነት ለመናገር ፈተናው ቀሎኝ ነበር።"
የሆነስ ሆኖ ብሩክን የፈተነችው የኬሚስትሪ ጥያቄ የቷ ትሆን? የቷስ ብትሆን ምን ትሰራልናለች? ብሩክ እንደሁ ዝሆኑን ውጤት ኪጋሊ ይዞት ገብቷል።

የፎቶው ባለመብት, FAMILY
"ጥያቄዋን ታስታውሳታለህ ብሩክ?"
"የቷን?"
"የከበደችህን!"
"የሆነ ስለ ሳሙና አሰራር የቀረበ ጥያቄ ነው…"
እንደ ሳሙና የተሙለጨለጨችበትን ጥያቄ አልረሳትም። ከእሷ ጥያቄ ሌላ ግን የከበደው አንድም ጥያቄ ትዝ አይለውም፤ ብሩክ።
"እኛ አንድም ቀን አጥና ብለነው አናውቅም" እናቱ ዶ/ር ሔለን
"ፈተናውን በደንብ ሠርቼ ስለነበር የአገሪቱ ከፍተኛ ውጤት የእኔ እንደሚሆን ገምቼ ነበር" የሚለው ልበ ሙሉ ተማሪ እናት ዶ/ር ሔለን ይፍጠር በልጃቸው ልበ ሙሉነት እሳቸውም ልበ ሙሉ ናቸው።
"ብሩክ ከልጅነቱ ጀምሮ ትምህርት የሚወድ ልጅ ሆኖ ነው ያደገው፤ እንዲህ አድርግ፣ በዚህ ውጣ-በዚህ ግባ ብለነው ግን አናውቅም" ይላሉ።
ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?
"እውነቱን ንገሪኝ ካልከኝ ድሮ በልጅነቱ ካልሆነ እኔ አጥና፣ ፊልም አትይ፣ መሽቷል ኳስ አትመልከት፣ እንዲህ ሁን እንዲያ ሁን ስለው ትዝ አይለኝም። እኔም አባቱም።"
ቆይ ግን! ወላጅ ልጁን እንዴት አጥና እያለ አይቆነጥጥም? አንድም ቀን አጥና ያልተባለ ልጅ እንዴት በአገሪቱ ትልቁን ብሔራዊ ውጤት ሊያመጣ ይችላል?
ለዶ/ር ሔለን "ምስጢሩን ካልነገሩን አንላቀቅም" አልናቸው።
ነገሩ አሳቃቸው። ከልብ አሳቃቸው…። "'ብሩክ ጎበዝ ልጅ ስለሆነ ነው' የሚለው መልስ አይሆንም ማለት ነው?" ብለው በድጋሚ ሳቁ።
በአስጠኚ መምህራን ባይደገፍ እንኳ ላቅ ባለ ደረጃ የተማሩት ወላጆች እጁን ይዘው እንዴት አያስጠኑትም?
"ዕድለኛ ሳንሆን አንቀርም" የሚሉት ዶ/ር ሔለን የልጃቸው ከትምህርት ጋር በፍቅር መውደቅ ምናልባት ብሩክ ልጅ እያለ እሳቸውና ባለቤታቸው የነበሩበት ሁኔታ ጋር ሊተሳሰር እንደሚችል ይገምታሉ።
"ብሩክ የተወለደው እኔም አባቱም የሕክምና ተማሪ እያለን ነው። እኛ ስናጠና እያየ ስላደገ በዚያው ትምህርት ወዶ ሊሆን ይችላል።"
ብሩክ የተፈተናቸውን ሰባት የትምህርት ዓይነቶች በሙሉ በአንጸባራቂ ውጤት ነው ያለፋቸው።
ለምሳሌ ሲቪክ 98፣ ባዮሎጂ 97፣ ፊዚክስ 96፣ ሦስት ትምህርቶች ማለትም እንግሊዘኛ፣ ሒሳብና ኬሚስትሪን 95 እንዲሁም አፕቲቲዩድ 93 ከመቶ አስመዝግቧል።
"ፌስቡክ ነበረኝ፣ ግን ብዙም ትዝ አይለኝም።"
ተማሪ ብሩክ የትምህርት ዓይነቶችን መሠረት ያደረገ የአጠናን ዘዴን ይከተላል። ከሽምደዳ ይልቅ መረዳትን ያስቀድማል።
የሚሸመደድ ነገር እምብዛምም አይማርከውም። ትምህርት እንደ ሒሳብ ሁሌ አዲስ ነገርን መፈለግ ሲሆን የበለጠ ዘለግ ላለ ሰዓት ለማንበብ ይበረታታል።
"ካልገባኝ ዩቲዩብ ላይ ቪዲዮዎችን እመለከታለሁ። የመምህራንንም መምሪያንም እመለከታለው።"
ማኅበራዊ ሚዲያውስ? ዩትዩብን ከፍቶ መዝጋት እንዲህ መጽሐፍ ገልጦ እንደ መክደን ነው እንዴ? ዩትዩብ ውቅያኖስ ነው። ኢንተርኔት ባሕር ነው። ጎርፍ ነው። ብሩክን እያሳሳቀ አይወስደውም?
አንድ በርሱ ዕድሜ ያለ ተማሪ ቀርቶ…
የማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ ዓለም አቀፍ "ፈተና" የሆነው ዝም ብሎ አይደለም። ብሩክ ብሔራዊ ፈተናውንስ አጥንቶ አለፈው። ይህን የፌስቡክ ሱስ ፈተና እንዴት አለፈው?
ደግሞም ኢንተርኔት እያሳሳቀ ይዞ የሚሄድ ወራጅ ውሃ የሆነው ለወጣቶች ብቻ አይደለም። በወጣቶች ቢብስም 3ኛ ዲግሪ ለሚሠሩም ፈተና ነው።
ብሩክ በዚህ ጎርፍ እንዴት ሳትወሰድ ቀረህ ሲባል ጥያቄው ራሱ የገረመው በሚመስል ድምጽ፣ "ምንም አይመስለኝም" ይላል።
ለምሳሌ "ፌስቡክ አለህ ወይ" ተብሎ ሲጠየቅ ብዙም እርግጠኛ ባልሆነ ድምጽ "አዎ፣ ነበረኝ፣ አለኝ፣ መሰለኝ…" ሲል ነው የመለሰው። "…ግን ብዙም ተጠቅሜበት አላውቅም፤ ከጓደኞቼ ጋር ለማውራት ቴሌግራም አለኝ።"

የፎቶው ባለመብት, FAMILY
በኢትዮጵያ ደረጃ ትልቁ ውጤት ያንተ ነው፤ ሌሎች ተማሪዎች የሌላቸው አንተ ያለህ ነገር ምንድነው ተብሎ ሲጠየቅ ደግሞ፣
"…እኔ ሌሎች የሌላቸውን እንዴት አውቃለሁ?" የሚል አጭር አፍ የሚያሲዝ መልስ ከሰጠ በኋላ፣ "እኔንጃ ብቻ፣ ዋናው ፍላጎት መሰለኝ…ፍላጎት ካለ በቃ…" ሲል ምስጢር የማይመስል የጉብዝና ምስጢርን ያጋራናል።
"ሕይወት በትምህርት 1ኛ መውጣት ብቻ አይደለም" ዶ/ር ሔለን
የብሩክ እናት ዶ/ር ሔለን ዕድለኝነታቸውንም ሳይሸሽጉ፣ የልጃቸውን ስክነት፣ ለትምህርት መሰጠትና በራሱ ምርጫ ነገሮችን እንዲያደርግ መፍቀድ፣ ጥሩ የአስተዳደግ መስመር እንደሆነ ፈራ ተባ እያሉ ለመምከር ባለመሻት ውስጥ ሆነው ይመክራሉ።
"ልጅሽ ጎበዝ ስለሆነ መከረች አትበሉኝና በሚል ዓይነት ትሁት አንደበት ሲቀጥሉ፣ "ልጆችን እኛ ወደምንፈልገው፣ ወደእኛ፣ ወደ ወላጆች ፍላጎት መጎተት ልክ አይመስለኝም" ሲሉ ይሞግታሉ።
ልጆችን በእኛ መንገድ ስንጎትታቸው አሉታዊ ስሜትም እናጋባባቸዋለን። ያ ጥሩ አይመጣም፤ አልህም አለ፤ ብዙ ጊዜ ልጆቹ ማድረግ፣ መሄድ የሚፈልጉበትን ዝንባሌ አይተን ማበረታታ፣ ማገዝ ነው የሚሻለው መሰለኝ። እኔንጃ ብቻ ወላጅ ሁሉም የራሱ አስተዳደግ ዘዴ ስላለው፤ ይሄ የግሌ አረዳድ ነው ብቻ…፡፡"
ሁሉንም ተማሪ በትምህርቱ ጎበዝ ካልሆነ፣ 1ኛ ካልወጣ ብሎ ትንፋሽ ማሳጠርም ከዶ/ር ሔለን የአስተዳደግ ፍልስፍና የሚስማማ አይመስልም።
ስፖርትም፣ ሙዚቃም ሥነ ጥበብን፣ የፈጠራ ሰው መሆንም ሌላ የሕይወት አማራጭ መንገዶች መሆናቸውን መዘንጋት አያሻም ባይ ናቸው።
"በጣም ብዙ ዓይነት ሕይወት ነው ያለው እኮ፤ ምርጫችን ሰፊ ነው። ምንም ካለመማር ጀምሮ ምርጫ ነው። እርግጥ ነው ከዓለም ጋር ለመግባባት ፊደል መቁጠር አለብን። የግድ ነው፤ ከዚያ ግን ዓለም ላይ በጣም ብዙ ዓይነት ሙያ፣ ክህሎት አለ፤ ልጆች ራሳቸውን ፍላጎታቸውን ሊከተሉ ልንፈቅድ ይገባል" ሲሉ የሚያምኑበትን ይናገራሉ።
ለዚህ ፍልስፍናቸው ተገዢ ለመሆን ይመስላል ዶ/ር ሔለን ልጃቸውን "ይህን ነው መማር ያለብህ፣ ያ ሙያ ይቅርብህ ተው" ብለውት አያውቁም። ማስረጃ?
ይኸው ዩኒቨርስቲ ለመግባት ደጅ-ታዛ ሥር የቆመው ብሩክ ምን እንደሚማር አልወሰነም። እንዲያውም ግራ ገብቶታል።
በዚህ ጊዜ ማንኛውም ወላጅ ልጁን በራሱ ጊዜ ይወስን ብሎ ይተዋል ተብሎ አይገመትም። በአንድም በሌላም መንገድ ወደ ወላጅ ምርጫ ለማምጣት ይሞከራል። ይመክራል፣ ያስመክራል።
እነ ዶ/ር ሔለን ግን ሌላው ቀርቶ ወደ ሙያቸው ወደ ሕክምናው እንኳ ሊጎትቱት እየሞከሩ አይመስልም።
"ዌል፣ ሙያችንን ቢወድልን አንጠላም ግን ይሄ የራሱ ውሳኔ ነው መሆን ያለበት" ይላሉ።
ዶ/ር ሔለን አሁንም ያሰምሩበታል፤ የልጆችን ምርጫ ስለማክበር…።
"እንደ ወላጅ ልጄ ተምሮ ይህን ካልሆነልኝ የምንለው ነገር አለ፤ ብዙውን ጊዜ ተምሮ ጥሩ ገቢ የሚያገኝበትን ነው የምናስበው። ልጄ ምን ፍላጎት አለው ብለን ማሰብ መቅደም አለበት።" ካሉ በኋላ "በማንኛውም ሙያ ፍላጎት ካለና ጥረት ካለ ለኑሯችን የሚሆን ነገር አይጠፋም። ስኬትም በዚያ መንገድ ቢሆን ነው ጥሩ። ደስተኛም የሚሆኑት ልጆች በፍላጎታቸው ሲሄዱና ሲኖሩ ነው" ብለው ይደመድማሉ።
"ኪጋሊ ንጹሕ ከተማ ናት"
ዶ/ር ሔለንና ዶ/ር ባልካቸው ርዋንዳ ለሥራ ነው የሄዱት። በቅርብ ነው የሄዱት። ብሩክም አብሯቸው ነው ያለው።
ብሩክ ከዚህ የሚያኮራ ውጤት በኋላ ጓደኞቹንና መምህራኖቹን አላገኛቸውም።
ምን ተሸለምክ ሲባል፣" ምንም!" ይላል፣ ብዙም ሳይከፋው።
"ዘመዶቼ ግን በርታ ጎበዝ ብለው መርቀውኛል" ይላል።
"ከቤተሰብ እስከሁን ምንም ዓይነት ሽልማት አልተሰጠውም።"
እናት ዶ/ር ሔለን በልጃቸው ምላሽ ይስቃሉ።
"ሽልማት አልለመድንም ይሆናል። አሁን እየተነጋገርን ነው። ሩዋንዳ የመጣነው በቅርቡ ነው። እዚህ የተዋወቅናቸው ኢትዮጵያዊያን ግን ኬክ ገዝተው እንኳን ደስ ያለህ ብለውታል" ካሉ በኋላ ድምጻቸውን ቀነስ አድርገው፣ "እኛም እያስብንበት ነው" ብለዋል።
በልጃቸው ውጤት የተደሰቱት እናት ዶ/ር ሔለን ልጅዎ ስለራሱ ያልነገረን ነገር ካለ እርስዎ ቢነግሩን አልናቸው።
"ብሩክ ልቡ ትልቅ ነው። ከትምህር ውጪም ልቡ ትልቅ ነው።"
"የምን ልማር" ውልውል
አጥና ተብሎ ታዞ የማያውቀው ብሩክ ከልጅነቱ ጀምሮ ከ1ኛ አስከ 3ኛ ነው እየወጣ ከስኬት ጋር ተለማምዶ ያለ ልጅ ነው።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጀመረ በኋላ ደግሞ አጥና የሚል ከወላጆቹ ስለመስማቱ ይጠራጠራል።
"ወላጅ ካላስገደደህ ታዲያ ለምን ታጠናለህ? አይሰለችህም?" ሲባል "ባህሪዬም ስለሆነ ሊሆን ይችላል፣ አላውቅም፤ ብቻ ዝም ብዬ አጠናለሁ" ሲል መልሷል።
ብሩክ ፈተናው አልቆም፣ ውጤቱን ወስዶም እያጠና ይሆን?
"አይ አሁን እንኳ አሜሪካና ፈረንሳይ ያሉ ዩኒቨርስቲዎች ጋር እያመለከትኩ ነው" ይላል።
የአሜሪካው ዩኒቨርስቲ ተስፋ ሰጥቶታል። ተጠባባቂ ሳያደርገው አልቀረም።
ያ ካልተሳካ ግን አገር ቤት ተመልሶ ለመማር ቁርጠኛ ነው። እሱን የቸገረው ዩኒቨርስቲው መቼ ሆነና። ብሩክን የቸገረው ምን ዘርፍ ማጥናት እንዳለበት መወሰን ላይ ነው።
ምሕንድስና? ሕክምና? ኮምፒውተር ሳይንስ? የሕዋ ሳይንስ? ለጊዜው አንዱም በአእምሮው ሽው አላለም። ለጊዜው ለየትኛውም ዘርፍ ልቡ አልደነግጠም።
"የሚከብደኝ ትምህርት አለ ብዬ አላስብም ግን ምን እንደምማር ነው ግራ የገባኝ። አንድ ነገር ለመሆን አልፈለኩም። የሆነ ዘርፍ ላይ እንዳተኩር ያነሳሳኝ ነገር ደግሞ የለም መሰለኝ። ብቻ ገና ውሳኔ ላይ አልደረስኩም" ብሏል።
የሚገርመው ብሩክ ከልጅነቱም ጀምሮ አውሮፕላን አበራለው፣ ኢንጂነር እሆናለው፤ ሰው አክማለው ሳይል ነው ያደገው። ሳድግ ይህን እሆናለው ሳይል ያደገ ልጅ ይኖራል?
"ድሮም ይህን እሆናለሁ ብዬ እያሰብኩ አልተማርኩም። ምን እንደምሆን፣ ምን እንደምማር አስቤበትም አላውቅም። ለዚያ ይሆናል አሁን ግራ የገባኝ" ይላል።
ምናልባት መማሩ በራሱ እያስደሰተው ስለቆየ ትምህርቱ የት እንደሚወስደው ለማሰብያ ጊዜ ነስቶት ይሆን?
"ቤተሰቦችህ ይሄን ተማር አላሉህም?"
"እነሱ ቀስ ብለህ አስብበትና ትወስናለህ ነው ያሉኝ።"
ዶ/ር ሔለን በዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ።
"እሱ የሚለን የመጀመርያ ዲግሪዬን በጠቅላላ ሳይንስ ሠርቼ ምን እንድምፈልግ ሳውቅ ብመርጥ ይሻላል ነው። እኛም ቸግሮናል። እሱም ግራ ገብቶታል።"
ብሩክን የዛሬ ስንት ዓመት ምን ሙያ ላይ የት ደርሶ እናገኘው ይሆን?
















