"ፈተና በማለፌ እንደ ሽልማት እንድገረዝ ተደረገ"

ልጆቿን ልታስገርዝ የማትወስድ እናት ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Jilla Dastmalchi

የተባበሩት መንግሥታት አካል የሆነው ዩኒሴፍ ያወጣው አንድ መረጃ እንደሚያመለክተው በግብጽ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 49 የሚገኙ ሴቶች 87 ከመቶ በሚሆኑት ላይ ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል።

50 ከመቶ የሚሆኑት ግብጻዊያን ግርዛትን ሐይማኖታዊ ግዴታ አድርገው ይመለከቱታል።

በግብጽ ጥብቅ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በተለይም በገጠሩ ክፍል የሚኖሩ ሴቶች ካልተገረዙ ንጹህ እንዳልሆኑ ይታሰባል። ለትዳርም ዝግጁ እንዳልሆኑ ነው የሚታመነው።

እንደ አውሮፓውያኑ ከ2008 ወዲህ ግብጽ የሴት ልጅ ግርዛትን ከልክላለች።

ሐኪሞች የሴት ልጅ ግርዛትን ከፈጸሙና ካስፈጸሙ እስከ 7 ዓመት በሚደርስ እስራት ሊቀጡም ይችላሉ። የግርዛት ጥያቄን የሚያቀርቡ ሴቶችም ሆኑ ቤተሰብ እስከ 3 ዓመት ድረስ እስር ሊጠብቃቸው ይችላል።

ይሁን እንጂ ግብጻውያን አሁንም ይህን ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት እርግፍ አድርገው አልተዉትም። እንዲያው በዓለም ላይ በከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶች ግርዛት ከሚፈጽሙባቸው አገሮች ተርታ ተሰልፋለች፤ ግብጽ።

ሐኪም ቤቶችም "ፕላስቲክ ሰርጀሪ" በሚል ሽፋን የሴቶች ግርዛት አገልግሎትን በኅቡዕ ይሰጣሉ የሚሉ መረጃዎች አሉ።

በዚህ ዘገባ የሦስት ሴት ግብጻውያንን ተሞክሮ እናስነብባችኋለን።

"ፈተና በማለፌ ግርዛት ሸለሙኝ" ለይላ

"እጄን ጥፍር አድርገው አሰሩኝ። ጭኔን ፈለቀቁት። እግሬን ግራና ቀኝ አንፈራጠው ያዙት። ይህ ሁሉ ለምን እንደሆነ አላውቅም ነበር። በሕይወቴ አሰቃቂው ነገር ነበር የተፈጸመብኝ። ምን እንዳስቀየምኳቸው እንጃ። እነዚህ የምወዳቸው ቤተሰቦቼ የኔን ስቃይ ለምን እንደናፈቁም አይገባኝም። ቆይ ግን፣ ጭኖቼ ውስጥ ስለት ይዘው ምን ይሠራሉ?"

ይህን የምትናገረው ለይላ ገና የ11 ወይም የ12 ዓመት ልጃገረድ እያለች ነበር አሰቃቂ ግርዛቱ የተፈጸመባት።

"ብዙውን ጊዜ ፕላስቲክ ሰርጀሪ በሚል የዳቦ ስም ነው ይህን ድርጊት የሚፈጽሙት" ይላሉ ሬዳ ኢልዳቡኩ። ኤልዳቡክ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪ ሲሆኑ ጉዳት ለደረሰባቸው ሴቶች የነጻ የሕግ አገልግሎት የሚሰጡ ሰው ናቸው።

መቀመጫውን ካይሮ ያደረገው የሴቶች መብት ንቅናቄ 3 ሺህ የፍርድ ቤት ፋይሎችን ከፍቶ 1 ሺህ 800ዎችን ማሸነፍ ችለዋል።

ኢልዳንቡኪ ለቢቢሲ እንዳሉት ፖሊስና ፍርድ ቤት ብዙውን ጊዜ ግርዛት የሚፈጽሙ ሰዎችን ለመቅጣት ዳተኛ ናቸው።

ለይላ ከአራት አስርታት በኋላ በ11 ዓመቷ የተፈጸመባትን አሰቃቂ ግርዛት አልረሳችውም። አሁንም ስታስበው ያንዘፈዝፋታል።

ያን ጊዜ ገና የትምህርት ቤት ፈተና መጨረሷ ነበር።

"ፈተናውን በማለፌ ይሸልሙኛል ስል ቤተሰቦቼ አዋላጅ አምጥተው፤ ከል ለብሰው ከበውኝ ግርዛትን ሸለሙኝ" ትላለች።

ሐኪም ቤት ውስጥ ያሉ ሰዎች ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Jilla Dastmalchi

ለይላ አሁን 44 ዓመቷ ሆኖ፤ አራት ልጆችን ወልዳ ታሳድጋለች።

ያም ሆኖ ያን ጊዜ በ11 ዓመቷ ስለሆነው ነገር መናገር ትፈራለች። ግብጻዊያን ፊት ስለግርዛት መጥፎነት መናገርን ትፈራለች። ግርዛትን ማውገዝ ምን ያህል በዚያ ማኅብረሰብ ዘንድ አስፈሪ እንደሆነ ማሳያ ናት።

አያቷ ሁለት ሴት ጎረቤቶች ነበሯቸው። ያኔ በ11 ዓመቷ ለግርዛት ከከበቧት ሰዎች መካከል እነሱ ይገኙበታል።

ለይላ ሌላም የምታስታውሰው ነገር አለ፤ ጎረቤቶቿና አያቷ ከበው እግሯን ፈልቅቀው የብልቷን ጫፍ ከቆረጡ በኋላ የቆረጡትን ለወፎች ሲወረውሩላቸው።

"በገጠር እንደመኖራችን ዶሮዎች ነበሩን። ልክ የቆረጡትን አካሌን ለወፎች ወረወሩላቸው። ወፎቹ ሊበሉት ተረባረቡ"

ያን ጊዜ የበዓል ወቅት ነበር። ሰዎች በበዓል ስሜት ሲጫወቱ አስታውሳለሁ። እኔ ግን መራመድ እንኳ አልችልም ነበር። እግሬን አንፈራቅቄ ነበር በሰው እርዳታ ወዲያ ወዲህ የምለው።

ለይላ በእሷ ላይ በትክክል ምን እንደደረሰባት ለመረዳት ረዥም ጊዜ ወስዶባታል። አድጋ ትዳር ስትመሠርት ነው የመገረዝ ጣጣውን ይበልጥ የተረዳችው።

"ለእነዚያ የግብጽ የገጠር ሰዎች ያልተገረዘች ሴት ማለት ሃጥያትን ተሸክማ የምትዞር እንደማለት ነው። ለእነዚያ ገጠር ሰዎች የተገረዘች ሴት ንጽህት ናት። እኔ ግራ እኮ የሚገባኝ! እንዴት ግርዛት መልካም ሰው ከመሆንና ካለመሆን ጋር ይያያዘ? እንደገባኝ ያው እነሱም ላይ የተጫነና የማያውቁትን ባሕል ነው እየተከተሉ ያሉት። መቼስ ምን ማድረግ ይቻላል?"

ግርዛትን የሚቃወሙ ሴቶች ስዕል

የፎቶው ባለመብት, Jilla Dastmalchi

ለይላ የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ ሴት ሆነች። እሷ ያለፈችበትን ስቃይ ግን በልጇ ልትደግም አልፈቀደችም።

ነገር ግን ይህን የግርዛት ሥነ ሥርዓት ባሏ ሲያሰናዳ ማስቆም አልቻለም። ለምን? ምክንያቱም ባሏ ቤተሰቦቹን ማስደሰት ይፈልጋል።

የመጀመሪያ ልጇ እሷ ያየችውን መከራ አየች። የተቀሩት ልጆቿም እንዲያ ሊሆኑ ነበር። በዚህ ጊዜ አንድ አዲስ ዜና ተሰማ። ግርዛት በግብጽ ሕገ ወጥ ተግባር መሆኑ ታወጀ።

ለይላ ከዚህ በኋላ ሴቶች መብት ተቆርቋሪዎችን ምክር መስማት ጀመረች። ትምህርት ተከታተለች። ግርዛት ለሞት ሊያበቃ እንደሚችል አወቀች።

"ስለምን ብዬ ነው ሴት ልጄን ወደሞት የምነዳት? ለአንድ በድንቁርና ውስጥ ላለ ባሕል ለመገዛት ስል ልጄን ለስቃይ ልዳርጋት? አላደርገውም።"

ሆኖም ግን ነገሩን ማስቆም አልቻለችም።

"የመጀመሪያ ልጄን ለዚህ ስቃይ ስለዳረኳት ይጸጸተኛል። ሆኖም ማድረግ የምችለው ነገር አልነበረም። ባሌን ማስቆም አቃተኝ። እሱን ባስቆም ደግሞ የእሱ ቤተሰቦች አሉ። የእሱን ቤተሰቦች ባስቆም መላው የአካባቢው ሰው አለ። ልጄን አትገርዙብኝም ባልኳቸው ጊዜ አንቺ ማነሽና ነው ዓለምን ለትቀይር የምትሞክሪው? አሉኝ።"

ለይላ የጾታ ትምህርት ከወሰደች በኋላ ግን ቆረጠች።

ባሏን ማስጠንቀቂያ ሰጠችው። "የተቀሩት ሴት ልጆቼን የምታስገርዛቸው ከሆነ ፍቺ እፈልጋለሁ፤ አሁኑኑ" የምሯን ነበር።

"የተቀሩትን ልጆቼን በዚህ መንገድ ባድንም የበኩር ልጄን ግን አሳልፌ ሰጠኋት። ደግሞ ብዙ ደም ነበር የፈሰሳት። በጣም ከመጨነቄ የተነሳ አጠገቧ እንኳ ለመሆን አቃተኝ።"

"እናቴ መገረዜን ስትሰማ ራሷን ስታ ሆስፒታል ገባች" ሸሪፋ

ሸሪፋ ያን ጊዜ 10 ዓመቷ ነበር። አባቷ አስገረዛት።

"እናቴ መገረዜን አጥብቃ ትቃወም ነበር። አባቴ ግን የእሱን እናት ለማስደሰት ሲል ጨከነብኝ። የቤቱ አባወራና አዛዥ ናዛዥ እሱ እንደሆነ ለማስመስከርም ፈልጓል። ለእናቴ ሳይነግራት ሆስፒታል ሊያስገርዘኝ ይዞኝ ሄደ።"

ሸሪፋ እንደምትገምተው ሐኪሙ ማደንዘዣ ወግቷት ነበር።

"ሆኖም እያለቀስኩ ነበር። አባቴ ይህን እኔ ላይ ማድረግ ለምን እንደፈለገ አልገባኝም። ሐኪሙ ብልቴ ውስጥ ገብቶ ምን እንደሚሰራ አልተረዳሁም ነበር። የሆነ ትክክል ያልሆነ ነገር እየሆነ እንደሆነ ግን ገብቶኝ ነበር።"

"ሐኪሙ የሆነ ሹል ነገር ተጠቅሞ ስለነበር ደሜ እንደ ጎርፍ መፍሰስ ጀመረ። ተደናገጡ። አባቴ በጣም ጥፋተኝነት ተሰማው። የሚያደርገው ሲጠፋው እናቴን ደውሎ ነገራት። እናቴ የእኔን መገረዝ ስትሰማ ራሷን ስታ ወደቀችና እኔ ወደነበርኩበት ሆስፒታል አመጧት። በዚያ ላይ ደም ግፊት ነበረባት። በዚያው በድንጋጤ ሞተች።"

የሸሪፋ አባት አሁን ሌላ ሚስት አግብቶ ይኖራል።

«ገንዘብ ይልክልኛል። ሕግ ማጥናት ነው የምፈልገው። በዚህ ጎጂ ልማድ ዙርያ ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ።"

"በወሲብ ተደስቼ አያውቅም" ጀሚላ

ጀሚላ 39 ዓመቷ ነው። በዘጠኝ ዓመቷ ነበር የተገረዘችው። ታሪኳን አጋርታናለች።

"ትዝ ይለኛል ክረምት ነበር። እናቴ አንዲት የሰፈር አዋላጅን ቤታችን ይዛ መጣች። ሁለቱ ጎረቤቶቻችንም ነበሩ። ሁሉንም ነገር አዘገጃጅታ ጥላኝ ወጣች። ውድ ልጇን ለአራጆች አሳልፋ ሰጠች።

"ቀሚሴን አወለቁ። ሁለቱ ጎረቤቶቼ ሁለቱን እግሮቼን ግራና ቀኝ ጠፍረው ያዙ። የልምድ አዋላጇ የሆነ ስለት ያለው ነገር ይዛለች። በቃ ሁሉም ነገር ህመም ነበር። በእርግጥ እናቴ አብራኝ ያልሆነችው የሚደርስብኝን ስቃይ ማየት ስላቃተት ነበር።"

ጀሚላ በልጅነቷ የደረሰባት ሕመም ለአቅመ ሄዋን ስትደርስ አስተሳሰቧ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ አመጣ።

"አንድ ቀን ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ይቺን የልምድ አዋላጅ መንገድ ላይ አገኘኋት። ቶሎ ብዬ መንገድ ቀየርኩ። ከእሷ ጋር አንድ መንገድ መጋራት ሁሉ አልፈለኩም ነበር።"

ጀሚላ የጾታ ትምህርት ትከታተላለች።

"ከዕለታት አንድ ቀን የግርዛትን አስከፊነት በምንማርበት ወቅት አንድ ሰውዬ ዘው ብሎ ገባና እንዲህ ተናገረ። ሴቶቻችንን ልክ እንደ አሜሪካ ሴቶች ሴተኛ አዳሪ ለማድረግ ነው አይደል አይገረዙ የምትሉት?"

አሁንም ደረስ ጀሚላ ወሲብ በምትፈጽምበት ወቅት ሕመም ይሰማታል። ወሲብ አስደስደስቷት ሁሉ አያውቅም።

"ሕይወት ራሱ አሰልቺ ናት፣ እንኳንስ ሕመም የተሞላበት ወሲብ ተጨምሮበት። ከባሌ ጋር የማደርገው ወሲብ የሕይወትን መከራ እንድረሳ የሚያደርግ ቢሆንልኝ እንኳ ምን ነበረበት?"