ኮሮናቫይረስ፡ የኮቪድ-19 ክትባት ነው በማለት ሶስት ልጆቹን ግብፃዊ ያስገረዘው አባት ተከሰሰ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሦስት ሴት ልጆቹን ያስገረዘው ግብፃዊ አባትና ግርዛቱን ፈፅሟል የተባለው ዶክተር ተከሰዋል።
አባት፤ ልጆቹን የኮሮናቫይረስ ክትባት ሊሰጣችሁ ነው ብሎ በማታለል ነው ገራዡ ዶክተር ወደ ቤታቸው እንዲመጣ ያደረገው ሲል አቃቤ ሕግ አስታውቋል።
ሶስቱም ሴት ልጆች ዕድሜያቸው ከ18 በታች ሲሆኑ ዶክተሩ ታዳጊዎቹን በመድኃኒት በማደንዘዝ ግርዛቱን እንደፈፀመ የክስ መዝገቡ ተመልክቷል።
ምንም እንኳ ግብፅ የሴት ልጅ ግርዛትን ከ2008 [በግሪጎሪ አቆጣጠር] ጀምሮ ብታግድም ድርጊቱ ሙሉ በሙሉ አልተቀረፈም።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን የሚመክት ክትባት እስካሁን ባይገኝም በርካታ ምርምሮች እየተካሄዱ ነው።
ሦስቱ ሴት ልጆች ከአባታቸው ጋር ፍቺ ፈፅማ ሌላ ቦታ ለምትኖረው እናታቸው የደረሰባቸውን ከነገሯት በኋላ ነው እናት ድርጊቱን ለባለሥልጣናት ያሳወቀችው።
አቃቤ ሕግ ባወጣው መግለጫ 'ሕፃናቱ ራሳቸውን ስተው ነበር፤ ነገር ግን ሲነቁ ባዩት ነግር እጅግ ተደናገጡ። እግራቸው ተጠፍሮ ብልታቸው አካባቢ ከፍተኛ ሕመም ይሰማቸው ነበር' ሲል ሁኔታውን አስርድቷል።
ግብፅ ውስጥ የግርዛት አገልግሎት መስጠት ወንጀል የሆነው ከአራት ዓመታት በፊት ነበር። ሲገርዙ የተገኙ ዶክተሮች እስከ 7 ዓመት እሥር ይጠብቃቸዋል። ልጆቹን ያስገረዘ ደግሞ እስከ 3 ዓመት ሊታሠር ይችላል።
ቢሆንም እስካሁን ድረስ በማስገረዝ ወይም በመግረዝ ወንጀል የተቀጣ ሰው አልነበረም። የሴቶች መብት ተሟጋቾች፤ ዳኞችና ፖሊሶች ጉዳዩን ከቁምነገር አይወስዱትም ሲል ይተቻሉ።
ባለፈው ጥር የ14 ዓመቷ ናዳ አብድል ማቅሱድ በግርዛት ምክንያት ብዙ ደም ፈሷት መሞቷ ብዙዎችን አስቆጥቶ ነበር። በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉት ቤተሰቦቿና ዶክተሩ በጊዜው በቁጥጥር ሥር ቢውሉም ፍርድ ይሰጣቸው አይሰጣቸው አይታወቅም።
የሴት ልጅ ግርዛት ግብፅ ውስጥ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የተለመደ ነው። ድርጊቱ ኃይማኖታዊ ዳራ ቢሰጠውም ዋነኛ ዓላማው የሴት ልጅን ወሲባዊ እርካታ መገደብ ነው።
ከአራት ዓመታት በፊት የተባበሩት መንግሥታት ያወጣው መረጃ ዕድሜያቸው ከ15-49 ከሆኑ ግብፃውያን ሴቶች መካከል 87 በመቶው ተገርዘዋል ይላል።
የሴት ልጅ ግርዛት በበርካታ ሃገራት ቢከለከልም ሙሉ በሙሉ ሊቆም አልቻለም። የተባበሩት መንግሥታት ቢያንስ 200 ሚሊዮን ሴቶች የግርዛት ሲሳይ ሆነዋል ይላል።












