ራሷን፣ እህቶቿንና የአካባቢዋን ልጆች ከግርዛት ያተረፈችው ተማሪ

መስከረም በምታስተምርበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, UNICEF Ethiopia/2020/Tadesse

የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሆና ፖሊሶች የማኅበረሰብ ትምህርት ለመስጠት መምጣታቸውን ታስታውሳለች። ፖሊሶቹ በሰንደቅ ዓላማ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው "ስለ ሴት ልጅ ግርዛት ጉዳት ታቃላችሁ?" ብለው ሲጠይቁ ተማሪው በአንድነት "አናውቅም" ሲል መመለሰ።

ከዚያ በኋላ የእርሷን እንዲሁም የሌሎች ህይወትን መስመር የሚቀይር ትምህርት ሰማች።

መስከረም ሙለታ ትባላለች። ሴት ልጅን መግረዝ ጉዳት እንዳለው ያወቀችው ያኔ የአካባቢያቸው ፖሊስ አባላት ትምህርት ቤታቸው መጥተው ባስተማሩበት ወቅት ነው። ትምህርቱን የሰጠው ፖሊስ "ሴት ልጅን መግረዝ ጣታችሁን ከእጃችሁ ላይ ቆርጦ እንደመጣል ነው" ሲል ማስተማሩንም ታስታውሳለች።

የተወለደችው በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ማረቆ አካባቢ፣ ሐሙስ ገበያ በምትባል መንደር ውስጥ ነው።

አሁን እድሜዋ 17 የሆነው መስከረም በማረቆ በሚገኘው ቆሼ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ነች።

ከሁለት ዓመት በፊት ስለ ሴት ልጅ ግርዛት አስከፊነት የሰማችው ትምህርት ሥራ ላይ የሚውልበት ቀን ሩቅ አልነበረም።

እናቷ አንድ ቀን ልታስገርዛት እየተዘጋጀች እንደሆነ አወቀች።

"የሰፈሩ ልጆች ሁሉ ተገርዘው አንቺ ከቀረሽ ቀልቃላ ትሆኛለሽ፤ እቃ ትፈጂያለሽ" ማለታቸውን ታስታውሳለች።

ስለዚህም እናቷ የሚገርዘውን ሰው ለማምጣት ማሰባቸውን ሲናገሩ ሰማች።

በዚህ ጊዜም ትምህርት ቤት ሴት ልጆች ከተገረዙ በወሊድ ጊዜ ብዙ ደም እንደሚፈስሳቸው። ከፍም ሲል በርካታ ደም ከመፍሰስ ጋር ተያይዞ ሊሞቱ እንደሚችሉ መማሯን ለእናቷ ተናገረች።

አክላም ድርጊቱ ኋላ ቀር ልማዳዊ ድርጊት ነው በማለት ለእናቷ አስረዳች።

እናቷ ግን በአቋማቸው ፀንተው ባለሙያውን ለማምጣት እንደወሰኑ ስታውቅ "እምቢ ብለሽ ካመጣሽው እከስሻለሁ" ስትል ማስፈራራቷን ታስታውሳለች።

ይሁን እንጂ የተፈራው አልቀረም። አንድ ቀን ከትምህርት ቤት ስትመለስ 'ባለሙያ' የተባለው ግለሰብ ካፖርቱን ደርቦ፣ ባርኔጣ ደፍቶ፣ ምላጭ ይዞ ከቤት ጠበቃት።

መስከረም፣ እናቷና ግለሰቡ ሲጨዋወቱ ትንሿን እህቷን ይዛ ከአካባቢው ጠፋች።

ከዚያም እርሱ ከሄደ በኋላ ወደ ቤት መመለሳቸውን ታስታውሳለች። እናትየው በመስከረም እምቢተኝነት ተስፋ ቢቆርጡም ታናናሾቿ ግን ገና በጨቅላነታቸው መገረዝ እንዳለባቸው ወሰኑ።

የመስከረም ታናናሽ እህቶች የስምንት እና የስድስት ዓመት ልጆች ናቸው።

"እንዳንቺ ሳያድጉ መገረዝ አለባቸው፤ ቁስሉም ቶሎ ይደርቅላቸዋል" እናቷ በማለት መጀመራቸውን ትናገራለች።

ከዚያ በመስቀል በዓል ላይ ድግስ ተደግሶ፣ ለልጆቹ ስጦታ እየመጣላቸው የግርዛት ሥነ ሥርዓቱ ሊፈፀም መሰናዶው መጀመሩን አስተዋለች።

ግርዛቱን የሚያከናውነው ግለሰብም ቤት መምጣቱን የምትናገረው መስከረም፤ የስድስት እና የስምንት ዓመት የነበሩት እህቶቿን በመውሰድ ሰው ቤት መደበቋን ትናገራለች።

ከዚያም ወደ ቤት በመመለስ ለግለሰቡ ድርጊቱ ትክክል እንዳልሆነ ስትናገር "የዚህ ዘመን ልጆች ለሰው ክብር የላቸውም" በማለት መቆጣቱን ታስታውሳለች።

ግለሰቡ የምትለውን አልሰማ ሲልም የአገር ሽማግሌዎች እና የማኅበረሰብ መሪዎች ኋላ ቀር ድርጊትን ሊፈጽም እንደሆነ በመግለጽ ተቃውሞዋን ገለፀች።

መስከረም እና ቤተሰቦቿ

የፎቶው ባለመብት, UNICEF Ethiopia/2020/Tadesse

በኋላም የመስከረም ጩኸት ሰሚ አግኝቶ፣ ሽማግሌዎቹ ከድርጊቱ የማይቆጠብ ከሆነ እንደሚከሰስ በመናገራቸው ትቶ ሄደ።

መስከረም ወደ ሰባተኛ ክፍል ስትዘዋወር ግን ሌላ ተግዳሮት ገጠማት። ሰባተኛ ክፍል የምትማርበት ትምህርት ቤት ከመኖሪያ አካባቢዋ ርቆ ስለሚገኝ እንደ ሁልጊዜው መንደሯ ውስጥ የሚከናወነውን ሁሉ በንቃት መከታተል አላስቻላትም።

የአካባቢዋ ሰዎችም ሴት ልጆቻቸውን ራቅ ወዳሉ አካባቢዎች እወሰዱ ማስገረዝን እንደ ብልሃት መጠቀም ጀመሩ።

ይህንን ያወቀችው መስከረም ከምትማርበት አካባቢ ወደ መንደሯ ስትመለስ ታዳጊዎቹን በመሰብሰብ መገረዝ እንደሌለባቸው ትመክራቸው ነበር።

አብረዋት በአንድ ክፍል ውስጥ ከሚማሩ ተማሪዎች መካከል ሊገረዙ መሆኑን በመጥቀስ ምክር ሲጠይቋት፣ አልገረዝም እንዲሉና ካልሆነ ግን ለፖሊስ እንዲያሳውቁ ትመክራቸው እንደነበር ትናገራለች።

የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሃገራት
የምስሉ መግለጫ, የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ሃገራት

'እኔ አልተገረዝኩም እያልኩን ኅብረተሰቡን አስተምራለሁ'

በምትማርበት ትምህርት ቤት እንደ እርሷ ካልተገረዙ ልጆች ጋር በመሆን በየ15 ቀኑ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እየሄዱ ስለ ሴት ልጅ ግርዛት ጉዳት ማስተማር ጀመሩ።

የአካባቢው የሴቶች ጉዳይ ቢሮም ስልጠናዎችን በመስጠት እና መድረኮችን በማዘጋጀት ያግዛቸው ጀመር።

ማኅበረሰብን ማስተማር ከራስ ይጀምራል የምትለው መስከረም፣ እኔ አልተገረዝኩም፤ በማለት እስከ ገጠር ትምህርት ቤቶች ድረስ በመሄድ እንደምታስተምር ትናገራለች።

የተገረዙት ሴት ልጆችም እንዳያፍሩና እነርሱ ላይ የደረሰው ሌሎች ላይ እንዳይደገም ከእርሷ ጋር በመሆን እንዲያስተምሩ ታደርጋለች።

ይህች ታዳጊ በአካባቢውና በትምህርት ቤቶች የምትሰጠው ትምህርት ተቀባይነት እያገኘ ሲሄድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ያበረታቷት ጀመር።

በዚህም ደስተኛ መሆኗን የምትናገረው መስከረም፤ ዘመዶቿም በጥንካሬዋና በጽናቷ እንደኮሩባት ገልጻለች።

የተባበሩት መንግሥታት በዓለማችን ላይ ካሉ ሴቶችና ህጻናት መካከል ወደ 200 ሚሊዮን የሚጠጉት የተለያየ ደረጃ የግርዛት ተግባራት ተፈጽሞባቸዋል ይላል።

የሴት ልጅ ግርዛት በስፋት እየተፈጸመ ያለው ወደ 30 በሚጠጉ የአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ሲሆን፤ በእስያ እና ደቡብ አሜሪካ በሚገኙ አገራትም የሴት ልጅ ግርዛት ይፈጸማል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ከሆነ በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ አበውስትራሊያ እና በኒው ዚላንድ የሚኖሩ ስደተኞች ሕግን በመተላለፍ ሴት ልጆቻቸውን ያስገርዛሉ።

የሴት ልጅ ግርዛት ሆነ ተብሎ የሴት ልጅን የመራቢያ አካልን ክፍልን መቁረጥ ማለት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ምንም እንኳ የሴት ልጅ ግርዛት በ29 የአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ በሕግ የተከለከለ ቢሆንም በ24 አገራት ውስጥ በስፋት እንደሚፈፀም ይጠቁማል።

የግርዛት አይነቶች

አራት አይነት የግርዛት አይነቶች አሉ።

  • ክሊቶሪዲክቶሚይ (Clitoridectomy)፡ ይህ ማለት በቂንጥር እና በአከባቢው የሚገኝ ስስ ቆዳ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።
  • ኤክሲሺን (Excision)፡ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልትን የውስጠኛውን ከንፈር ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ማስወገድ ማለት ነው።
  • ኢንፊቢዩሊሽን (Infibulation)፡ ይህ ማለት ቂንጥርን እና የብልት ክንፈሮችን ቆርጦ በመጣል ብልትን በመስፋት የግብረ ስጋ ግንኙነት ምቹ እንዳይሆን ማድረግ ማለት ነው። ይህ ተግባር የሚያስከትለው ህመም ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ለኢንፌክሽን ተጋላጭነትን ከፍ ያደርጋል። በተጨማሪም ሽንት እና የወር አበባ ፍሳሽ በቀላሉ እንዳይወጣ ያደርጋል።
  • ሌላኛው የግርዛት አይነት የሴት ልጅ የመራቢያ አካላትን መውጋት፣ መብሳት፣ መቧጠጥ እና ማቃጠል የመሳሰሉትን ያካትታል።