ትግራይ፡ በእስር ላይ የሚገኙት የህወሓት አመራር አባላት 'ክሳችን ፖለቲካዊ ነው' ማለታቸው ተነገረ

አቶ አባይ ወልዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር)፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ እና አቶ ስብሐት ነጋ

አዲስ አበባ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙት የቀደወሞው ህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ ተናገሩ።

እስረኞቹ ይህንን የተናገሩት ስለእስር አያያዛቸው ሁኔታ ለመመልከት ለጎበኟቸው ለኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ለዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) እና ለኮሚሽኑ ከፍተኛ ባለሙያዎች ነው።

ኮሚሽኑ ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 27/2013 ዓ.ም የጎበኟቸው አብረሀም ተከስተ (ዶ/ር)፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሃት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ፣ ሰለሞን ኪዳኔ (ዶ/ር)፣ አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ 21 እስረኞችን ነው።

ከታሰሩት ግለሰቦችና ከፖሊስ ኃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉን የገለጸው ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ ላይ "አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ አቅርበዋል" ብሏል።

ኮሚሽኑ እንዳለው ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት የሚገኙ ሲሆን የተያዙበት አጠቃላይ ሁኔታ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ተመልክቶ፤ የተጠቀሱት ታሳሪዎች ወደ ፌዴራል ፖሊስ እስር ቤት ከመጡ ወዲህ "ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር የሚሰሩ መሆኑን" ገልጸዋል ብሏል።

በተጨማሪም የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ጋር ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን እንደተናገሩ ኮሚሽኑ በመግለጫው ላይ አመልክቷል።

ታሳሪዎቹ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ከጠበቆች ጋር የሚገናኙበት ጊዜ ማጠሩን እንዳነሱና የተወሰኑ ታሳሪዎች የራሳቸውና የቤተሰቦቻቸው የባንክ ሒሳብ በመታገዱ ቤተሰቦቻቸው መቸገራቸውን እንደተናገሩ ገልጸዋል ብሏል።

አስረኞቹ አሁን ካሉበት ሁኔታ ባሻገር ገጠሙን በሚሏቸው ጉዳዮች ላይ ቅሬታቸውንም ለኮሚሽኑ አባለት መግለጻቸውን አመልክቷል።

ከዚህም ውስጥ "ከተያዙ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀለ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራትና ተኩስ እንደነበረ እንዲሁም የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው" ገልጸዋል ብሏል።

በተጨማሪም ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ "ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ" በማንሳት ቅሬታቸውን ያቀረቡ እስረኞች እንደነበሩ ኢሰመኮ ገልጿል።

ኮሚሽኑ ታሳሪዎቹ አሁን በእስር የተያዙበት ሁኔታ በተገቢው ደረጃ መሆኑን ማረጋገጡንና በታሳሪዎች የተነሱ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ከእስር ቤቱ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ማድረጉን አመልክቷል።

የቀድሞ የህወሓት አመራሮች አዲስ አበባ ውስጥ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል ምርመራ ቢሮ በሚገኘው እስር ቤት ያሉበትን ሁኔታ ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ከተመለከቱ በኋላ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገውን "ምርመራ በተቻለ ፍጥነት በማጠናቀቅ፤ የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መልኩ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን ታሳሪዎች መለየት አስፈላጊ ነው" በማለት ማሳሰባቸው ተገልጿል።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ህወሓት ከሥልጣን መወገዱ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ አድርገው ነበር።

ለእስር ማዘዣውም ዋነኛ ምክንያቶቹ ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑ መገለጹ ይታወሳል።