ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና እየተዘጋጁ የሚገኙት የ61 ዓመት አዛውንት

የ61 ዓመት ጎልማሳ አቶ ቆንጮሪ ቦሩ

አቶ ቆንጮሪ ቦሩ የ61 ዓመት አዛውንት ናቸው። ይህ ግን በግምት የደረሱበት እንጂ እርግጠኛ የሆኑበት አይደለም።

በምዕራብ ጉጂ በሱሮ በርጉዳ ወረዳ ነው ተወልደው ያደጉት፣ የአፍላ እድሜያቸውን ዓመታት እንዲሁም ጉልምስናቸውን በግብርና እና ከብት በማርባት አሳልፈዋል።

የ11 ልጆች አባት የሆኑት አቶ ቆንጮሪ፣ ዛሬ ከከብቶች ጋር አይታገሉም። ወቅት ጠብቀው፣ የሰማይን ሆድ ተከትለው ማረስን ብቻ አያስቡም። አሁን የሚያስጨንቃቸው ሌላ ነገር አለ።

ሒሳብ ይቀምራሉ። ፊዚክስ ያሰላሉ። ሥነ ህይወት እና ሥነ ዜጋ ይሸመድዳሉ። የልጅ ልጆቻቸው ከሚሆኑ ተማሪዎች ጋር ይፎካከራሉ።

በሽምግልና ዘመናቸው ወደ ቀለም ቆጠራ የመጡት በአካባቢያቸው የተጀመረን የመሠረተ ትምህርት አስታከው ነው።

አቶ ቆንጮሪ እድሜያቸውን በትክክል ባያውቁም “አሁን እድሜዬ 61 ይሆናል” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አዛውንቱ ቆንጮሪ፣ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ በዝግጅት ላይ ናቸው።

“አያቴም አልተማሩም። አባቴም አልተማረም። እኔም እንዲህ እስከ ማረጅ ድረስ አልተማርኩም ነበር” ሲሉ ስለትምህርት ጥማታቸው ይናገራሉ።

በሚኖሩበት ወረዳ በ2000 ዓ.ም መሠረታዊ ትምሀርት መማራቸው ነው ያላቸውን የትምህርት ረሃብ እንደ አዲስ ቀሰቀሰባቸው።

“መሠረታዊ ትምህርት ብለው ከቀበሌያችን 25 ሰው ሰብስበው ማስተማር ጀመሩ። እኔ ድሮውኑም ቁጭት ስለነበረኝ በጣም ደስ አለኝ። ከእኔ ጋር የመሠረተ ትምህርቱን የጀመሩ ሁሉ አቋረጡ። እኔ ግን እርሱን ጨርሼ 1ኛ ክፍል ገባሁ” ሲሉ ትምህርት የጀመሩበትን አጋጣሚ ያስታውሳሉ።

በ2001 ዓ.ም አንደኛ ክፍል ገቡ።

የልጆቻቸውን ልጆች አቅፈው ለመሳም የበቁት አቶ ቆንጮሪ

“አንደኛ ክፍል ስገባ ሰዉ ተደነቀ። ‘ወደ ቤት ገብቶ ከብት አይጠብቅም። ትምህርት ቤት ገብቶ ከልጆች ጋር ከሚውል’ አለኝ። እኔ ግን ተምሬ ይህንን ሕዝብ ማሳመን ስለምችል ቁብ አልሰጠኋቸውም። ትምህርቴን ቀጠልኩኝ።”

የ61 ዓመት ጎልማሳ አቶ ቆንጮሪ ቦሩ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

አንደኛ ክፍል ሲገቡ የትምህርት ቤቱ ጥበቃ ታሪክን ለሌሎች ትምህርት እንዲሆን ለበርካቶች ይናገሩ ነበር።

“አንደኛ ክፍል ስገባ ትምህርት ቤታችን አንድ ጥበቃ ነበር። አልተማረም። ግን ትምህርት ቤት ነው የሚውለው። ቤቱም እዚያው ትምህርት ቤቱ አጠገብ ነው። ለምን አትማርም ብዬ ስጠይቀው በስተርጅና ትምህርት ምን ያደርግልኛል አለ። እኔ ያኔ ጀመርኩ። አሁን 12ኛ ክፍል ደርሻለሁ። እርሱ ግን አሁንም የፊደል ዘር አይለይም።”

አቶ ቆንጮሪ ዓለም ላይ ሞልቶ የተረፈው ዕውቀት ይርባቸዋል።

ሌሎች ያወቁትን ማወቅ በብርቱ ይፈልጋሉ።

“ውስጤ ያለው ሰው ያወቀውን እኔ እንዴት ሳላውቅ ቀረሁ የሚል ጥያቄ ነው። . . .እኔ ጤነኛ ሆኜ እንዴት በጣቴ እፈርማለሁ ስል እቆጫለሁ። በቀረኝ እድሜም ትምህርቴን ጨርሼ ውጤት አገኝበታለሁ።”

አቶ ቆንጮሪ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚከታተሉት በቡሌ ሆራ መሰናዶ ትምህርት ቤት ነው።

ባለፈው ሳምንት ሰኞ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ እየተዘጋጁ ነው።

በዚህ መልቀቂያ ፈተና የሚጠበቀውን ውጤት ካመጡ ዩኒቨርስቲ ገብተው መመረቅ ትልቁ ግባቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

“ይህንን የሚመጣውን ፈተና እግዚአብሔር ካሻገረኝ ዩኒቨርስቲ እገባለሁ። አንድ አስተማሪዬ ውጪ አገር አንድ አዛውንት ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ልጆቻቸ ግራ እና ቀኝ ይዘውት ፎቅ እየወጣ እንደተማሩ ነግሮኛል። ይህም የሞራል ስንቅ ሆኖኛል” ሲሉ ይናገራሉ።

“እኔ ሽማግሌ ነኝ እንጂ አጥንቴ ብርቱ ነው። የትኛውም ዩኒቨርስቲ ብገባ፣ የትኛውንም ፎቅ ወጥቼ ወርጄ መማር እችላለሁ።”

የወደፊት እቅዳቸውንም ሲናገሩ "ከዩኒቨርስቲ ተመርቄ ቤተሰቤን፣ አስተማሪዎቼን እንዲሁም የአካባቢዬን ነዋሪዎችን ማስደሰት እፈልጋለሁ።"

"በተጨማሪም በተማርኩት ሙያ እንጀራ ብበላበት ደስ ይለኛል።"

ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ልጆች ወልደው፣ እድሜያቸው ከገፋ በኋላ ወደ ዩኒቨርስቲ የገቡ ግለሰቦችን ታሪክ አቅርቦ ነበር።

ከእነዚህም መካከል ጅማ ዩኒቨርስቲ የተመደቡት የ69 ዓመቱ አቶ ታደሰ ጊቺሌ አንዱ ናቸው።

አቶ ቆንጮሪ በ69 ዓመታቸው ዩኒቨርስቲ ስለገቡት አቶ ታደሰ ጊችሌ ሲጠየቁ፣ አለመስማታቸውን ገልፀው

"እንደኔው ጠንካራ ነው ማለት ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልፀዋል።