'ለሴቶች መቻል' የታተረችው ጋዜጠኛ እና ደራሲ የምወድሽ በቀለ አረፈች

ጋዜጠኛ እና ደራሲ የምወድሽ በቀለ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Media Women Association

ለሴቶች ብርታት በመቆም የምትታወቀው ጋዜጠኛ እና ደራሲ የምወድሽ በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።

በጋዜጠኝነት ለረጅም አመታት ያገለገለችው እና በርካታ የድርሰት እና የግጥም መጽሐፍትን ለአንባቢያን ያበረከተችው የምወድሽ በቀለ በሕክምና ስትረዳ ቆይታ አርብ፣ ነሐሴ 23/2017 ዓ.ም በ66 ዓመቷ ማረፏን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

በ1951 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለደችው የምወድሽ በቀለ በፖሊስ እና እርምጃው ጋዜጣ በዋና አዘጋጅነት ለረጅም አመታት ያገለገለች ሲሆን ከሚዲያ ሥራዎች እና ከሥነ ጽሑፍ ሳትርቅ ቆይታለች።

በፖሊስና እርምጃው በቆየችባቸው በርካታ ዓመታት የወንጀል ዘገባዎችን በመስራት ከፍተኛ ልምድ እንዳደበረች ተገልጿል።

ሳቂታዋ የሚል ተቀፅላ ያላት የምወድሽ ሲቪል መርማሪ ሆና ባገለገለችበት ወቅት አሰቃቂ እና ዘግናኝ የወንጀል መዝገቦችን በአደባባይ ያወጣች እንደሆነችም ይነገርላታል።

በዚህም በርካታ ወንጀሎች ፍትሕ እንዲያገኙ አበርክቶዋ የላቀ እንደሆነ የሚያውቋት ይመስክራሉ።

በርካታ ወጣት ጸሐፊያንን በተለይም ሴቶችን በማበረታት እና በማገዝ የምትታወቀው የምወድሽ፣ ሴት ደራሲያንን ለማበረታት በተቋቋመው የኢትዮጵያ ሴት ደራሲያን ማኅበርን በፕሬዚደንትነት መርታለች። በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር ውስጥም ጉልህ ድርሻ አበርክታለች።

የምወድሽ በ1979 ዓ.ም ካሳተመችው አብዮታዊ ግጥሞች ከሚለው ሥራዋ ጀምሮ ከ16 በላይ የሥነ ጽሑፍ ትሩፋቶችን አበርክታለች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እብዷ በለጠች፣ አብዮታዊ ግጥሞች፣ የባከነ ጊዜ፣ ያላፈራ ፍሬ ካበረከተቻቸው የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች መካከል ይጠቀሳሉ።

በተለይም እብዷ በለጠች የተሰኘው ስራዋ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የስነ ጽሁፍ ማስተማሪያነት ሆኖ እንዳገለገለ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ህልፈቷን አስመልክቶ ያሰፈረው ጽሁፍ ያስረዳል።

ከአስር በላይ የረጅም እና አጫጭር ልቦለዶቸን፣ የግጥም መድብሎች እንዲሁም እውነተኛ ታሪኮች ስብስብ ለአንባቢያን ያበረከተችው የምወድሽ ብዙውን ጊዜ ሥራዎቿ በሴቶች ላይ የሚያተኩሩ እና የወንጀል የአጻጻፍ ስልት ትከተላለች።

ለዚህም ሲቪል መርማሪ ሆና መስራቷ ምክንያት እንደሆነ ይነገራል።

በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ሴቶች ማህበር የነቃ ተሳትፎ እንደነበራት እንዲሁም በስራ አመራር ቦርድነት በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሴቶች ማሕበራት ውስጥም የቦርድ ሰብሳቢ ሆና አገልግላለች።

ለሴቶች መላቅ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራት የምወድሽ 'ሴቶች ይችላሉ' (Women Can do it) የተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት መስርታ በዋና ዳይሬክተርንት ስታገለግል ቆይታለች።

'ሴቶች ይችላሉ' የሚለው ግብረ ሰናይ ድርጅት በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሴቶችን በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በሕግ ለማጎልበት እና ድምጻቸውን ለማጉላት የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ዓላማ ያነገበ አገር በቀል ተቋም ነው።

በአሻም ቴሌቪዥን፣ እና በአሃዱ ሬዲዮም ላይ በሴቶች ላይ ያጠነጠኑ ፕሮግራሞችን እና በሥነ ፅሑፍ ሥራዎቿ፣ በጎነትን ፣ ብረትታን እና መቻልን ሰብካለች።

በእነዚህ በርካታ አበርክቶዎቿም በርካታ ሽልማቶችን እና የምሥክር ወረቀቶችን ያገኘች ሲሆን ባለፈው ዓመትም በጋዜጠኝነት ዘርፍ በአገር ውስጥ በሚዘጋጀው የበጎ ሰው ሽልማት እጩ መሆን ችላ ነበር።

የጋዜጠኛዋን ሕልፈት ተከትሎ በተለይም የሥነ ፅሑፍ አፍቃሪያን እና ወዳጆቿ የተሰማቸውን ሐዘን በማሕበራዊ ሚዲያ እየገለጹ ይገኛሉ።

የምወድሽ በቀለ የአራት ልጆች እና የአምስት የልጅ ልጆች አያት ነበረች።

የጋዜጠኛዋ ስርዓተ ቀብር እሁድ ነሐሴ 25/ 2017 ዓ.ም ጥዋት 5 ሰዓት አየር ጤና ኪዳነ ምሕረት እንደሚካሄድ ተገልጿል።