የቻይናው ቢዋይዲ ቴስላን በመቅደም በዓለም ላይ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መኪና ሻጭ ሊሆን ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይናው ቢዋይዲ የኤለን መስክ ቴስላን በመቅደም በዓለም ላይ ትልቁ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሻጭ እንደሚሆን ተነገረ።
ሐሙስ ዕለት ቢዋይዲ እንደገለጸው ባለፈው ዓመት በባትሪ የሚሰሩት መኪናዎቹ ሽያጭ በ28 በመቶ አድጎ ወደ 2.25 ሚሊዮን ከፍ ብሏል።
ቴስላ የ2025 ሽያጩን በሰዓታት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ ቢጠበቅም፤ ተንታኞች ባለፈው ሳምንት ባሳተሙት ግምታቸው ኩባንያው በዓመቱ በአጠቃላይ 1.65 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎችን እንደሸጠ ይጠቁማል።
የአሜሪካው ኩባንያ አዳዲስ ምርቶቹ የነበረው አቀባበል ድብልቅ ከመሆኑም ባለፈ መስክ በፖለቲካ ውስጥ መሳተፉ እና ከቻይና ተቀናቃኞች ጋር ያለው ፉክክር እየጨመረ በመምጣቱ አስቸጋሪ ዓመት እንዲያሳልፍ አስገድዶታል።
ቴስላ በጥቅምት ወር የአሜሪካ ሽያጩን ለማሳደግ በሚል ከፍተኛ ሽያጭ ያላቸውን ሁለት ሞዴሎቹን በዝቅተኛ ዋጋ አስተዋውቋል። ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቆየት አዳዲስ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው አማራጮችን ለመልቀቅ ቀርፋፋ ሆኗል በሚል ተተችቷል።
የዓለማችን ቁጥር አንዱ ባለሃብት በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ የቴስላን የሽያጭ እና የአክሲዮን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ኃላፊነት የተሰጠው ሲሆን ይህንን ካሳካ ክብረ ወሰን ሆነ ክፍያ የሚያገኝ ይሆናል። ከወራት በፊት በባለአክሲዮኖች በፀደቀው ስምምነት መሠረት እስከ አንድ ትሪሊዮን ዶላር ክፍያ ሊያገኝ ይችላል።
ከስምምነቱ አንዱ መስክ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ አንድ ሚሊዮን የሰው መሳይ ሮቦቶችን መሸጥ ይጠበቅበታል። ቴስላ "ኦፕቲመስ" ምርቱ እና በአሽከርካሪ አልባ "ሮቦታክሲው" ላይ ከፍተኛ ኢንቨስት አድርጓል።
መስከ በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የነበረውን ሚና በመቃወም የቴስላ ሽያጭ በ2025 የመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት ውስጥ ዝቅተኛ ሆኖ ነበር።
መስክ ከቴስላ በተጨማሪ የማህበራዊ ሚዲያው ኤክስ፣ የሮኬት ኩባንያው ስፔስኤክስ እና ዋሻዎችን የሚቆፍረውን ቦሪንግንም ኩባንያ ያካትታሉ።
ከእነዚህ ሥራዎች ጎን ለጎን የትራምፕን የመንግስት ብቃት መምሪያ (ዶጅ) ከማስተዳደሩ ጋር ተዳምረው አንዳንድ ባለሃብቶች መስክ በቴስላ ላይ በቂ ትኩረት እንዳላደረገ እንዲጠቁሙ አድርጓቸዋል።
ከዚያን ወዲህ ግን መስክ በአሜሪካ መንግስት ውስጥ ያለውን ሚና "በከፍተኛ ደረጃ" ለመቀነስ ቃል ገብቷል።
ቢዋይዲ በቅርብ ዓመታት ውስጥ ፈጣን መስፋፋት ቢያሳይም፣ የ2025 የሽያጭ ዕድገቱ ግን በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ ዝቅተኛ ሆኖ ተመዝግቧል።
መቀመጫውን ሼንዘን ያደረገው ድርጅቱ ትልቁ የገበያው መሠረት በሆነው በቻይና እንደ ኤክስፒንግ እና ኒዮ ካሉ የኤሌክትሪክ መኪና አምራቾች ውድድሩ ጨምሮበታል።
ቢዋይዲ ካለው አነስተኛ ዋጋ አንጻር አሁንም ዓለም አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ መኪና የበላይ ሆኖ ቀጥሏል።
ብዙ አገሮች በቻይና የኤሌክትሪክ መኪናዎች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ቢጥሉም ኩባንያው በተለይም በላቲን አሜሪካ፣ በደቡብ ምስራቅ እስያ እና በአውሮፓ ክፍሎች በፍጥነት ተስፋፍቷል።
ቢዋይዲ በጥቅምት ወር እንደገለጸው ከሆነ ዩናይትድ ኪንግደም ከቻይና ውጭ ትልቁ ገበያው ሆናለች። ኩባንያው በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ የብሪታንያ ሽያጩ በ880 በመቶ ማደጉን ገልጿል። ይህንን ያሳካው ሲል ዩ የተሰኙት ተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ፍላጎት በመኖሩ ነው።















