መካከለኛው ምሥራቅን ያጥለቀለቁት የቻይና ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይና የወጪ ንግድ መረጃ እንደሚያሳው ባለፉት ስድስት ዓመታት ወደ ቀጣናው የሚላኩ ተሽከርካሪዎች ሽያጭ በስድስት እጥፍ አድጓል።
እ.አ.አ በ2019 150 ሺህ ተሽከርካሪዎችን የሸጠችው ቻይና፤ በ2024 ደግሞ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጥ ተሽከርካሪ ሸጣለች።
በገልፍ አገራት 'ኤስዩቪ' እና አነስተኛ ተሽከርካሪዎች በሁለገብነታቸው እና በተጨባጭነታቸው ምክንያት በሰፊው ተመራጭ ናቸው።
ባለፉት አስርት ዓመታት 'ላንድ ሮቨር ድፌንደር' እና 'ኒሳን ላንድ ፓትሮል' ተባሉ የተሽከርካሪ ዓይነቶች መለያ እስኪመስሉ ድረስ በመንገዶች በስፋት ይታዩ ነበር።
ይሁን እንጂ በማይታወቁ የቻይና አምራቾች አማራጭ ሆነው እየቀረቡ ያሉ ተሽከርካሪዎች ተመራጭነታቸው እያደገ ነው።
ጃፋር አል-ሀይኪ ቴክኖሎጂ ወዳጅ ባህሬናዊ ሲሆን፤ በ'ቻንጋን አውቶሞቲቭ' በሸንዘን ከተማ የሚመረት 'ኤስዩቪ' መኪና ያሽከረክራል።
ከአምስት ዓመት በፊት የገዛው ተሽከርካሪ በተገጠመለት የቴክኖሎጂ ዓይነት እና ጥራት እንደተገረመ ይናገራል።
"ሰዎች ተሽከርካሪዎች ቀላል የመጓጓዣ መንገዶች አድርገው ያስባሉ። ነገር ግን ቻይናዎች የተለያዩ የመዝናኛ፣ የደኅንነት መሳሪያዎች ላይ ያተኩራሉ። ሲታዩ የሚያምሩ ተሽከርካሪዎችን መስራት ላይም ተክነውበታል" ይላል።
"የእኔ መኪና ከፊት እና ኋላ ራዳር አለው፤ ዙሪያው ሙሉ ሴንሰር ተገጥሞለታል። . . . ይህን ጃፓን ወይም ኮሪያ ሰራሽ መኪኖች ላይ በተመሳሳይ ዋጋ አታገኝም።"

የቻይና አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ በምዕራቡ ዓለም በተለይም በኤሌክትሪክ መኪኖች አምራች በሆኑ እንደ 'ቢዋይዲ' ባሉ ኩባንያዎች ይታወቃል።
ይሁን እንጂ በመካከለኛው ምሥራቅ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተወዳጅ እየሆኑ ቢመጡም የቻይና የነዳጅ ተሽከርካሪዎችም ብዙ አሽከርካሪዎችን ከመሳብ ወደ ኋላ አላሉም።
በምሥራቅ የሳዑዲ አረቢያ ዳርቻ የሚኖረው ናስር አላ-ማሪ በቅርቡ አሜሪካ ሰራሽ 'ጂኤምሲ ዩኮን' የነበረውን መኪናውን በገልፍ አገራት በጣም እየተወደደ በመጣው 'ጄቱር' በተባለው የቻይና ተሽከርካሪ ቀይሯል።
"የቻይና መኪና ለመግዛት የወደድኩት ምክንያት የጀርመን መኪኖችን የመሰለ ጥራት ያለው እና በተመጣጣኝ ዋጋ በመቅረቡ ነው" ይላል።
"እንደውም የተገጠሙለት መሳሪያዎች ከአንዳንድ የጃፓን መኪኖች የተሻሉ ናቸው" ሲልም በቆዳ የተሰሩ ውስጣዊ ክፍሎችን፣ ጥራት ያላቸው የድምፅ ማጉያዎችን፣ ትልቅ ስክሪን፣ የውጭ ካሜራ እና ብርሃን የሚያስገባ ጣራን ለአብነት ያነሳል።

ምንም እንኳ የጥራት ስጋት የነበረው ቢሆንም አል-ማሪ በድረ ገፅ የተሰጡ አስተያየቶችን ካነበበ እና ቪዲዮዎችን ከተመለከተ በኋላ ተሽከርካሪውን ለመግዛት መወሰኑን ይናገራል።
በርካታ የቲክቶክ ተከታይ ያላት እና ኳታር የምትኖረው ራጋድ ያሰር በቻይና ተሽከርካሪዎች ጥርጣሬ ላላቸው ሰዎች ምላሽ ትሰታለች።
"መኪናየ ቻይና ሰራሽ በመሆኑ ብቻ አልወደድከውም? ምን?"ስትል ያሰር 'ጄቱር' በተባለው ተሽከርካሪዋ ዙሪያ ለተሰጠ የማጣጣል አስተያየት በድምፅ የሚከፈተውን ጣሪያ እያሳየች ለተቺዎች ምላሽ ስትሰጥ በአንድ ቪዲዮ ትታያለች።
"በል የ'ሮል-ሮይስ' መኪናህን አሳየኝ እስኪ" ስትል ለአጣጣዩ ወገን ጥያቄ ትወረውራለች።
ወደ መኪናዋ ዞር ብላ እያየች "ለማይገባቸው ሰዎች ለምን ራሴን አደክማለሁ? ሄለው ጄቱር ጣራውን ዝጋው" ትላለች።
የደኅንነት ስጋት እና ቀጣናዊ አዝማሚያ
መቀመጫውን ዱባይ ያደረገ ካርማ የተሰኘ የመገናኛ ብዙኃን ዳሳሽ ድርጅት በቅርብ ባተመው ጥናት 79 በመቶ የሳዑዲ የጥናቱ ተሳታፊዎች ለቻይና ተሽከርካሪዎች አዎንታዊ እይታ ሲኖራቸው፤ 42 በመቶ የአሜሪካ ተሳታፊዎችም ደጋፊ ምላሽ ሰጥተዋል።
የአሜሪካ አሽከርካሪዎች ከገልፍ አገራት አሽከርካሪዎች ጋር ሲነፃፀር የቻይና ተሽከርካሪዎችን እምብዛም አያውቁም። ይህም በንግድ ገደቦች ምክንያት የቻይና ተሽከርካሪዎች ያን ያህል የአሜሪካን ገበያ አልተቀላቀሉም።
የካርማ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ማሪያ ታላኪና ለቻይና ተሽከርካሪዎች ያለው አዎንታዊ እይታ ከተሽከርካሪዎች ጋር ካለ የቀጥታ ግንኙነት ጋር የተያያዘ ነው ብለዋል።
የድርጅቱ ግኝቶች ኒው ዮርክ ከሚገኘው አሊክስ ፓርትነርስ ከተባለው አማካሪ ድርጅት ጋር ይመሳሰላል።
አሊክስ ፓርትነርስ በ2030 የቻይና ተሽከርካሪዎች የመካከለኛውን ምሥራቅ እና የአፍሪካን አንድ ሦስተኛ የገበያ ድርሻ ይይዛሉ የሚል ትንበያ አውጥቷል።
የገልፍ አገራት ገበያ ድርሻ ለቻይና አምራቾች አስፈላጊ ቢሆንም እንኳ የቻይና ተሽከርካሪዎች ከዚህ ቀጠና ባሻገር ከፍተኛ ተወዳዳሪ እየሆኑ ነው።
ከአውሮፓውያኑ 2014 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ገበያ የቻይና ተሽከርካሪዎች አንደኛ ተቀባይ ኢራን ስትሆን፤ በአሜሪካ ማዕቀብ ምክንያት ይህ አዝማሚያ ሊገታ ችሏል።
ቻይና በጋዛ ያለውን ጦርነት በመተቸት በእስራኤል ያላት ስም በተወሰነ መልኩ ቢጎድፍም፤ የቻይና ተሽከርካሪዎች በፍጥነት ከገበያው ድርሻቸውን እያገኙ ነው።
የምዕራብ አገራት አጋር በሆነችው እስራኤል የቻይና ተሽከርካሪዎች በተገጠመላቸው የፍለጋ እና የግንኙነት መስመር ምክንያት የግል መረጃ አሊያም የብሔራዊ ደኅንነትን ስጋት ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ፍርሃት ቢኖርም ገበያቸው ግን እየጨመረ ነው።
አንዳንድ ባለሙያዎች መሳሪያዎቹ የተሳፋሪዎችን እና በዙሪያቸው ያለን መረጃ በመሰብሰብ እና ጥራት ያለው ድምፅ እና ምስል ያሰራጫሉ የሚል ስጋት ያሰማሉ።
ባለፈው ነሐሴ የመረጃ ደኅንነት ስጋት ያደረበት የእስራኤል ጦር ቻይና ሠራሽ ተሽከርካሪዎች ወደ ጦር ሰፈሮች እንዳይገቡ ከልክሏል።
እንዲህም ሆኖ እንኳ እንደ እስራኤል የተሽከርካሪ አስመጪዎች ማኅበር መረጃ በ2024 እስራኤል ከየትኛውም አገር የበለጠ ተሽከርካሪ ከቻይና አስገብታለች።
እየጨመረ የመጣ ስጋት
በዱባይ ሳምንታዊ ፕሮግራም የሚያቀርበው የአውቶሞቲቭ ጋዜጠኛ ዴሚየን ሪድ ስለ ቻይና ተሽከርካሪዎች ለመጠየቅ የሚደውሉ አድማጮች ቁጥር በጣም ጨምሯል ይላል።
በቻይና የፖለቲካ ሹማምንት በስፋት የሚሽከረከውን ተሽከርካሪ የሚያመርተው ሆንግኪ እንደ 'ቢኤምደብሊው' እና 'መርሴዲስ-ቤንዝ' የቅንጦት ተሽከርካሪዎች ስሙን ለመትከል እየተሯሯጠ መሆኑን ይናገራል።
"በተደጋጋሚ የሚቀርብልኝ ጥያቄ 'በበርሃ ተሰባብሮ ይቀራል? መንገድ ላይ ገትሮኝ ይቀራል ወይስ ቤቴ ያደርሰኛል?' የሚል ነው" ይላል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቻይና ተሽከርካሪ ባለቤቶች በዘላቂነት ትልቁ ስጋታቸው ከመሆኑ ይልቁ ሁሉም በሚያስብል ደረጃ ትልቁ ራስ ምታታቸው የመለዋወጫ እጦት እና የጥገና ባለሙያ ማጣት እንደሆነ ተናግረዋል።
ካፋር አል-ሀይኪ በባህሬን አንድ መለዋጫ ለማግኘት ለአምስት ወራት መመኮሩን ይናገራል።
አንዳንዶችም የመለዋወጫ ዋጋ እና እጦት እንዲሁም የጥገና አገልግሎት ማጣት የቻይና ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት እንዲያቅማሙ እንዳደረጋቸው ሲናገሩ፤ አንድ ባለቤት ደግሞ የተጭበረበረ ያህል እንደተሰማው ገልጿል።
ማምረቻን ወደ ቀጣናው ማምጣት
አንዳንድ የቻይና የተሽከርካሪ አምራቾች ተሽከርካሪዎች የሚጠገኑበት መሠረት ልማት ራሳቸው ለመገንባት እየሞከሩ ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካቶች በቀጠናው የመለዋወጫ ማከፋፈያ ማዕከል እየከፈቱ ነው አልያም አሳውቀዋል።
ጥቂቶቹ ደግሞ ተሽከርካሪዎችን በክልሉ ለማምረት ፋብሪካ የመገንባት እቅዶቻቸውን አሳውቀዋል።
ያለፈው ዓመት 10 ኩባንያዎች በግብፅ፣ ቱርክ፣ አልጀሪያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለመገንባት ያላቸውን ውጥን ያሳወቁበት ነው።
ግብፅ ስድስት የቻይና ኩባንያዎች ለቀጣናው ገበያ የሚውል ማምረቻ ለመገንባት ላይ ታች እያሉ ሲሆን፤ ይህም አገሪቱን የቻይና ተሽከርካሪ ማምረቻ መናኸሪያ ያደርጋታል።
በርካታ አገራት የቻይና የተሽከርካሪ ፋብሪካዎችን ለመሳብ ፍላጎት አላቸው። የሥራ እድል ከመፍጠር ባሻገር ኢኮኖሚን እና ምርትን የሚያሳድግ ዘመኑን የዋጀ ቴክኖሎጂ ያመጣሉ የሚል ተስፋ አለ።
ይሁን እንጂ በመካከለኛው ምሥራቅ ይገነባሉ ተብለው የሚጠበቁ የቻይና የተሽከርካሪ ፋብሪካዎች፣ ከቻይና በሚመጡ መለዋወጫዎች ለገበያ ዝግጁ የሚያደርጉ መገጣጠሚያዎች ናቸው።
ኩባንያዎች በቀጣናው ዘመናዊ ማምረቻ ከከፈቱ፣ በሥልጠና እና በቴክኖሎጂ አበርክቶ የሚኖራቸው ሲሆን የቻይና ተሽከርካሪዎች በመካከለኛው ምሥራቅ ገበያ መብዛታቸው ግዙፍ የምጣኔ ኃብት አስተዋፅኦ ይኖረዋል።












