ቻይና በተለያዩ ዘርፎች ዓለምን እንዴት ለመቀየር ቻለች?

የቻይናን ባንዲራ የያዘች ታዳጊ ልጅ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images

የቻይና ከፍተኛ መሪዎች በዚህ ሳምንት በቤይጂንግ ተሰብስበው የቀሪዎቹ አስር ዓመታት የአገሪቱ ቁልፍ ግቦች እና ፍላጎቶች ላይ ይወስናሉ።

በየዓመቱ ወይም ከዚያ በላይ የአገሪቱ ከፍተኛ የፖለቲካ አካል የሆነው የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንድ ሳምንት ይሰበስባል፣ ይህም ምልዓተ ጉባኤ ይባላል።

በዚህ ጊዜ የሚወሰነው የቻይና የአምስት ዓመት ዕቅድ ላይ ይሆናል። በዓለም ሁለተኛዋ ትልቁ ኢኮኖሚ ያላት አገር ከ2026 እስከ 2030 የምትከተለውን የልማት ግብ ያስቀምጣል።

ሙሉ ዕቅዱ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ይፋ አይሆንም። ነገር ግን ባለሥልጣናቱ ይዘቱን በተመለከተ ረቡዕ ዕለት ፍንጭ ሊሰጡ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ይሰጣሉ።

በእስያ ሶሳይቲ ፖሊሲ ኢንስቲትዩት የቻይና ፖለቲካ ተመራማሪ የሆኑት ኒል ቶማስ "የምዕራባውያን ፖሊሲ በምርጫ ዑደቶች ላይ ይሠራሉ፣ የቻይና ፖሊሲ ግን በዕቅድ ዑደቶች ላይ ይሠራል" ብለዋል።

አክለውም "የአምስት ዓመት ዕቅዶች ቻይና ምን ማሳካት እንደምትፈልግ ይገልፃሉ፤ አመራሩ ወደ የት መሄድ እንደሚፈልግ አቅጣጫውን ያመለክታሉ እና የአገሪቱን ሀብቶች ወደ ተቀመጡ አቅጣጫዎች ያንቀሳቅሳሉ" ብለዋል።

ላይ ላዩን ሲታይ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ አቋም ያላቸው ቢሮክራቶች እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ እና ዕቅድ ነደፉ የሚለው ሃሳብ አሰልቺ ሊመስል ይችላል።

ነገር ግን የወሰኑት ውሳኔ ብዙ ጊዜ በዓለም ላይ ትልቅ ተጽእኖ እንዳለው ታሪክ ይነግረናል።

የቻይና የአምስት ዓመት ዕቅድ የዓለምን ኢኮኖሚ የለወጠባቸው ሦስት ቁልፍ ጊዜያት እነሆ።

ከ1981-1984 "ተሃድሶ እና በርን መክፈት"

ቻይና ኃያል የኢኮኖሚ ባለቤት ለመሆን ጉዞዋን የጀመረችበትን ጊዜ በትክክል መለየት ከባድ ነው። ነገር ግን በርካታ የፓርቲው አባላት በአውሮፓውያኑ ታኅሣሥ 18/1978 ነበር ማለትን ይመርጣሉ።

ለሦስት አስርት ዓመታት ያህል የቻይና ኢኮኖሚ በመንግሥት ጠንካራ ቁጥጥር ስር ነበር። ነገር ግን የሶቪየት ዓይነት ማዕከላዊ ዕቅድ ብልጽግናን ማምጣት አልቻለም። እናም ብዙዎች በድህነት ውስጥ መዳከራቸውን ቀጥለው ነበር።

አገሪቱ አሁንም ከማኦ ዜዱንግ አስከፊ አገዛዝ በማገገም ላይ ነበረች። በኮሚኒስት ቻይና መሥራች መሪነት የአገሪቱን ኢኮኖሚ እና ኅብረተሰብ ለመቅረጽ የተካሄዱት ዘመቻዎች፣ የባህል አብዮቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቻይናውያንን ለሞት ዳርገዋል።

በቤይጂንግ በተካሄደው 11ኛው የኮሚቴው ምልዓተ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት አዲሱ የአገሪቱ መሪ ዴንግ ዣዎ ፒንግ አንዳንድ የነፃ ገበያ መርሆዎችን ለመቀበል ጊዜው አሁን ነው አሉ።

በአውሮፓውያኑ 1981 የጀመረው የ"ተሃድሶ እና በሮችን የመክፈት" ፖሊሲ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ወሳኝ አካል ሆነ።

ነፃ የንግድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መፈጠር እና የሳበው የውጭ ኢንቨስትመንት በቻይና የሰዎችን ሕይወት በተጨባጭ ለውጧል።

ዴንግ ዣኦ ፒንግ የቻይናን ኢኮኖሚ በከፈቱበት ወቅት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ጋር ታሪካዊ ስምምነት ተፈራርመዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዴንግ ዣኦ ፒንግ የቻይናን ኢኮኖሚ በከፈቱበት ወቅት ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጂሚ ካርተር ጋር ታሪካዊ ስምምነት ተፈራርመዋል

እንደ ቶማስ ገለጻ፣ የአምስት ዓመት ዕቅድ ዓላማዎች የበለጠ ትኩረት ተሰጥቷቸው በመሠራቱ ሊሳኩ ችለዋል።

"ብሔራዊ ኩራትን ወደ ቀድሞ ሁኔታው ​​ከመመለስ እና ከዓለም ታላላቅ ኃያላን መካከል ያላትን ቦታ ከማስቀመጥ አንፃር" ይላሉ ቶማስ "ቻይና ዛሬ በ1970 ዎቹ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ህልም በላይ ሆናለች።"

ከዚህ ሁሉ ባሻገር ግን የዓለምን ኢኮኖሚ በመሠረታዊ መልኩ ቀይሮታል። በ21ኛው ክፍለ ዘመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ የምዕራባውያን የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎች በቻይና የባሕር ጠረፍ አካባቢዎች ለሚገኙ አዳዲስ ፋብሪካዎች ተሰጥተዋል።

ኢኮኖሚስቶች ይህንን "የቻይና መመንደግ" (the China shock) ብለውታል። በቀድሞው ባለ ኢንደስትሪዋ አውሮፓ እና አሜሪካ ሕዝባዊ ፓርቲዎች እንዲነሱ ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ነው።

ለምሳሌ፣ የዶናልድ ትራምፕ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች፣ ታሪፋቸው እና የንግድ ጦርነታቸው ባለፉት ጥቂት አስርተ ዓመታት በቻይና ያጡትን የአሜሪካን የማኑፋክቸሪንግ ሥራዎችን ለመመለስ የተነደፉ ናቸው።

ከ2011 - 2015 "አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቻይና የዓለም ንግድ ድርጅትን በ2001 ከተቀላቀለች በኋላ የዓለም ኃያል የምጣኔ ሃብት ባለቤት እና የማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ማዕከል መሆኗ ተረጋገጠ።

ነገር ግን በክፍለ ዘመኑ መባቻ ላይ የኮሚኒስት ፓርቲ አመራር የሚቀጥለውን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ እያቀደ ነበር።

ቻይና "የመካከለኛ ገቢ ወጥመድ" እየተባለ በሚጠራው ሥርዓት ውስጥ ችግር ውስጥ እንዳትወድቅ ግን አስግቶ ነበር።

ይህ የሚሆነው ወደ ላይ እየተመነደገ የሚሄድ አገር ከአሁን በኋላ በዝቅተኛ ክፍያ መሥራት የሚችል የሰው ኃይል ማቅረብ በማይችልበት ጊዜ ነው።

በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ የላቀ ኢኮኖሚ ያላቸው አገራት እንደሚያመርቱት ከፍተኛ ደረጃ ያላቸውን ምርቶች እና አገልግሎቶችን ለማቅረብ የሚያስችል የፈጠራ አቅም ከሌለው ነው።

ስለዚህ ቻይና በርካሽ ማኑፋክቸሪንግ ብቻ ሳይሆን "ስልታዊ ታዳጊ ኢንዱስትሪዎች" የምትለውን መፍጠር ነበረባት። ይህ አገላለጽ በይፋ ጥቅም ላይ የዋለው በአውሮፓውያኑ 2010 ላይ ነው።

ለቻይና መሪዎች ይህ ማለት እንደ የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች እና የፀሐይ ኃይልን ወደ ኤሌትሪክ የሚቀይሩ ሳህኖችን በጥቅሉ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ ማለት ነው።

በምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ አስፈላጊ እየሆነ ሲመጣ፣ ቻይና ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ መጠን ያላቸውን ሀጃብት ወደ እነዚህ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች አሰባስባለች።

ዛሬ ቻይና በታዳሽ ኃይል እና በኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች በማይከራከር ሁኔታ የዓለም መሪ ብቻ ሳትሆን እነሱን ለመገንባት በሚያስፈልጉ ብርቅዬ ማዕድናት ላይ በብቸኝነት የበላይነት ለመያዝ በቅርብ ርቀት ላይ ትገኛለች።

ቻይና ለቺፕ ማምረቻ እና ለአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (ኤአይ) ወሳኝ የሆኑት እነዚህ ቁልፍ ማዕድናት ያሏት መሆኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ ቦታ ላይ አስቀምጧታል።

ስለዚህም ቤይጂንግ በቅርቡ ብርቅዬ የሆኑ ማዕድናትን ወደ ውጭ መላክ ላይ ቁጥጥርን ለማጥበቅ የወሰደችው እርምጃ በትራምፕ "ዓለምን በምርኮ ለመያዝ" ትፈልጋለች በሚል አስፈርጇታል።

ምንም እንኳ በአውሮፓውያኑ 2011 "ስልታዊ ታዳጊ ኃይሎች" በሚቀጥለው የአምስት ዓመት ዕቅድ ውስጥ ቢደነገግም፣ አረንጓዴ ቴክኖሎጂ በ2000ዎቹ መጀመሪያ ላይ በቻይና መሪ በሁ ጂንታዎ የዕድገት እና የጂኦፖለቲካል ኃይል አንቀሳቃሽ ሊሆን እንደሚችል ተለይቶ ተቀምጦ ነበር።

ኒል ቶማስ "ይህ ቻይና በኢኮኖሚዋ፣ በቴክኖሎጂዋ፣ በድርጊት የበለጠ ራሷን እንድትችል ያለው ፍላጎት ብዙ ወደ ኋላ ይሄዳል፤ የቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም የተሠራበት ገመድ ነው" ሲሉ ያስረዳሉ።

በዢ አመራር ስር የቻይና የአምስት ዓመት ዕቅዶች “ከፍተኛ ጥራት ያለው ልማት” ላይ ያተኮሩ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, Grigory Sysoev/RIA Novosti/Pool/Anadolu Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዢ አመራር ስር የቻይና የአምስት ዓመት ዕቅዶች "ከፍተኛ ጥራት ያለው ልማት" ላይ ያተኮሩ ናቸው

2021 - 2025: "ከፍተኛ ጥራት ያለው ዕድገት"

ይህ በአውሮፓውያኑ 2017 በ ዢ ጂን ፒንግ በይፋ የተዋወቀው፣ የቻይና የአምስት ዓመት ዕቅድ በቅርቡ ትኩረቱን ወደ "ከፍተኛ ጥራት ያለው ልማት" ወደሚል ያዞረው ለምን እንደሆነ ያብራራል።

ይህ ማለት የአሜሪካን በቴክኖሎጂ የበላይነት መገዳደር እና ቻይናን በዘርፉ ግንባር ቀደም ማድረግ ማለት ነው።

እንደ ቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያ ቲክ ቶክ፣ የቴሌኮሚዩኒኬሽን ግዙፉ ተቋም ሁዋዌ እና የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ሞዴል የሆነው እንደ ዲፕሲክ (DeepSeek) ያሉ የአገር ውስጥ የስኬት ታሪኮች ሁሉም በዚህ ክፍለ ዘመን የቻይና የቴክኖሎጂ ዕድገት ማሳያ ናቸው።

ነገር ግን ምዕራባውያን አገራት ይህንን ለብሔራዊ ደኅንነታቸው ስጋት አድርገው ይመለከቱታል።

አስከትለው የታወቁ የቻይና ቴክኖሎጂዎች ላይ የጣሉት እገዳ ወይም ለማገድ መሞከር በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ጎድተዋል እንዲሁም የተካረሩ ዲፕሎማሲ ምልልሶችን አስከትለዋል።

እስካሁን ድረስ ቻይና ለቴክኖሎጂ ስኬቷ እንደ ኒቪዲያ የላቁ ሴሚኮንዳክተሮች ያሉ የአሜሪካን ፈጠራዎችን ተጠቅማለች።

አሁን እነዚህ ምርቶች ለቻይና ኩባንያዎች እንዳይሸጡ በዋሽንግተን ቢታገዱም "ከፍተኛ ጥራት ያለው ልማት" ወደ "አዲስ ጥራት ያለው አምራች ኃይል" እንዲሸጋገር ይጠበቃል።

በ2023 በፕሬዝዳንት ዢ የተዋወቀው አዲስ መሪ ቃል ወደ የአገር ውስጥ ኩራት እና ብሔራዊ ደኅንነት ማተኮር ላይ ያጋድላል።

ይህ ማለት በምዕራቡ ዓለም ቴክኖሎጂ ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ እና ከእገዳ እና ክልከላዎች ነጻ ሆኖ ቻይናን በቺፕ ማምረቻ፣ በኮምፒዩተር እና በአይአይኤ ቁንጮ አድርጎ ማስቀመጥ ማለት ነው።

በሁሉም መስኮች ራስን መቻል፣ በተለይ በፈጠራ ከፍተኛው ጫፍ ላይ መገኘት፣ የቀጣዩ የአምስት ዓመት ዕቅድ ዋና ዋና መርሆዎች አንዱ ሊሆን ይችላል።

ቶማስ "የብሔራዊ ደኅንነት እና የቴክኖሎጂ ነፃነት አሁን የቻይና ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተልዕኮ ናቸው" ሲሉ ያስረዳሉ።

"በቻይና ውስጥ ኮሚዩኒዝምን ወደሚደግፈው የብሔርተኝነት ፕሮጀክት በመመለስ ዳግመኛ የውጭ አገራት የበላይነት እንዳይኖርባቸው ለማድረግ ነው" ሲሉ ያብራራሉ።