ያለ ቀጣሪ እና ያለ ቢሮ 'የሚሠሩት' ቻይናውያን ሥራ አጦች

ማንም ሰው ያለ ደመወዝ መሥራት አይሻም። ለአለቃ ደመወዝ እየከፈሉ መሥራትም የሚታሰብ አይደለም።
ቻይናውያን ሥራ አጦች ግን ለቀጣሪዎች እየከፈሉ ነው።
ወጣቶቹ ሥራ እንደተቀጠሩ በማስመሰል ወደ መሥሪያ ቤቶቹ ይሄዳሉ። ለዚህ አገልግሎትም ክፍያ ይፈጽማሉ።
የቻይና ምጣኔ ሃብት መቀዛቀዝ እና የሥራ አጥነት መስፋፋት ነው ለዚህ ምክንያቱ። እውነተኛ ሥራ አግኝቶ መቀጠር ለብዙዎች ሕልም ነው።
ሆኖም ግን ሥራ ፈት ሆኖ ቤት ከመቀመጥ እየከፈሉ የውሸት መሥሪያ ቤት መመላለስ የተሻለ አማራጭ ሆኖ ተገኝቷል።
ሹይ ዦው 30 ዓመቱ ነው። ምግብ ይሸጥ ነበር።
አምና ግን ንግዱ ከሰመ።
በአንድ ሰዓት 4 ዶላር (30 የን፣ የቻይና ገንዘብ) እየከፈለ የውሸት መሥሪያ ቤት መመላለስ ጀመረ።
'ፕሪቴንድ ቱ ወርክ ካምፓኒ' የተባለው ተቋም መሥሪያ ቤትን የማስመሰል አገልግሎት ይሰጣል።
ከሆንግ ኮንግ በ114 ኪሎሜትር ርቀት ይገኛል።
ሹይ የሚመላለሰው እዚህ ተቋም ነው። ልክ እንደእሱ ሌሎች አምስት ሰዎችም ወደዚህ ተቋም ይመጣሉ።
ማንኛቸውም እውነተኛ ሥራ የላቸውም። ግን ተቀጣሪ እንደሆኑ አስመስለው ቀኑን ያሳልፋሉ።
"ደስታ ይሰማኛል። አብረን እየሠራን እንዳለን ነው የማስበው" ይላል ሹይ።
በቻይና ግዙፍ ከተሞች ሸንዘን፣ ሻንጋይ፣ ናንጂንግ፣ ዉሃን፣ ቼንግዱ እና ሙናሚንግ እንዲህ ያሉ ተቋማት እየተስፋፉ ነው።
ተቋማቱ ትክክለኛ መሥሪያ ቤት ነው የሚመስሉት። ኮምፒውተር፣ የስብሰባ አዳራሽ እና ካፌ አላቸው።
በተቋማቱ ኮምፒውተሮች ላይ ሥራ የሚያፈላልጉ ብዙ ናቸው። የራሳቸውን ሥራ መጀመር የሚፈልጉም መረጃ ያስሳሉ።
ከ30 እስከ 50 የን በመክፈል በእነዚህ ተቋማት ምሳ መብላትም ይቻላል።
የቻይና የሥራ አጥነት መጠን ከ14 በመቶ በላይ በመሆኑ ነው ተቋማቱ እየተስፋፉ የመጡት።
በዚህ ዓመት ተመርቀው ገበያውን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር ከ12 ሚሊዮን በላይ እንደሚሆን ይገመታል። እስካሁን ከታየው የሥራ ፈላጊ ቁጥር ከፍተኛው ነው።

ሹይ፣ 'ፕሪቴንድ ቱ ወርክ' ተቋምን ያገኘው በበይነ መረብ ነው። እንደ መሥሪያ ቤት ያለ ተቋም መሆኑ "የሥራ ሥነ ምግባርን ለመማር" እንደሚረዳው ይናገራል።
ከሦስት ወራት በላይ በዚህ ተቋም ሠርቷል።
የተቋሙን ምሥል ለቤተሰቦቹ ሲልክ ደስታቸውን ገልጸውለታል። ሥራ አጥ ሆኖ ቤት ከሚውል የተሻለ አማራጭ አድርገው ወስደውታል።
የዚህ ተቋም ተገልጋዮች ባሻቸው ሰዓት መግባት እና መውጣት ይችላሉ። ሹይ ግን ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 3 ሰዓት ባለው ጊዜ ነው የሚገባው። እስከ 11 ሰዓት ድረስ ሊቆይም ይችላል።
የተቋሙ አመራሮች ከወጡ በኋላ ይወጣል።
አብረውት ወደ ተቋሙ የሚመላለሱ ወጣቶት ሥራ በመፈለግ በማይጠመዱበት ወቅት ያወራሉ። የወዳጅነት ትስስርም ፈጥረዋል።
ሲወጡ አብረው እራት ይበላሉ፤ ጌሞችም ይጫወታሉ።
ሹይ እንደሚለው እንደዚህ ያሉ ክንውኖች ከሥራ ባልደረቦች ጋር እንዴት መኖር እንደሚቻል ያስተምራሉ።
ወደዚህ ተቋም ከመምጣቱ በፊት ካለው በበለጠ አሁን ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል።
በሻንጋይ የምትኖረው ዢዋን ታንግም ተቀጣሪ እንደሆነች በማስመሰል ወደ አንድ ተቋም ትመላለሳለች።
የ23 ዓመቷ ወጣት ከዩኒቪርስቲ ከተመረቀች በኋላ ሥራ አላገኘችም።
የተማረችበት ዩኒቨርስቲ ባወጣው ሕግ መሠረት ተመራቂዎች በአንድ ዓመት ውስጥ መቀጠራቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ማስገባት አለባቸው።
"ማስመሰል ካለብኝ እስከ መጨረሻው ጥግ ድረስ ማስመሰል አለብኝ" ትላለች።
በጀርመን የሚገኘው ማክስ ፕላንክ ኢንስቲትዩት ፎር ሶሻል አንትሮፖሎጂ ኃላፊ ዶ/ር ቢዎ ዢንግ እንደሚሉት ቻይናውያን ወጣቶች እንደ ሠራተኛ ሆነው የሚያስመስሉት የሥራ ዕድሎችን ባለማግኘታቸው "በጣም ተስፋ በማጣት እና አቅም አልባ በመሆናቸው" ምክንያት ነው።
"ወጣቶች እየሠሩ እንደሆነ በማስመሰል ራሳቸውን ይደብቃሉ። ከማኅበረሰቡ ትንሽ ገለል የሚሉበትም መንገድ ነው" ይላሉ።

'ፕሪቴንድ ቱ ወርክ' የተመሠረተው በ30 ዓመቱ ፋይ ነው።
"እኔ እያቀረብኩ ያለሁት አማራጭ መሥሪያ ቤት አይደለም። አንድ ሰው ሥራ አጥ በመሆኑ ከንቱነት እንዳይሰማው ነው የማደርገው" ይላል።
ነጋዴ የነበረው ፋይ በኮሮናቫይረስ ወረርሽን ወቅት ከስሮ ሥራ አጥነት ምን ማለት እንደሆነ አይቶታል።
"በጣም ተደብሬ ነበር። ራሴን ጠልቼ ነበር። አቅም አልባነት ነበር የሚሰማኝ" ይላል።
ተቋሙን እንደመሠረተ ነበር ብዙዎች አገልግሎቱን እንደሚፈልጉ የገለጹት።
40 በመቶ ደንበኞቹ በቅርቡ ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቁ ይገልጻል። የተቋሙን ፎቶ ለቀድሞ መምህሮቻቸው ይልካሉ። ሥራ እንደያዙ ማስረጃ ማሳየት ስላለባቸው ነው ምሥሎች የሚልኩት።
ከቤተሰቦቻቸው የሚደርስባቸውን ጫና ለመቋቋም ወደ ተቋሙ የሚያመሩም አልታጡም።
የተቋሙት አገልግሎት ከሚሹት መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት በበይነ መረብ ሥራ ለመፈለግ ተቋሙን ይጠቀሙበታል። ያገኙትን ሥራ ሠርተው ወደ ቀጣዩ ሥራ ይሻገራሉ።
አብዛኞቹ ወጣቶች 30 ዓመታቸው ሲሆን ትንሹ ዕድሜ 25 ነው።
ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ዝግጁ ከሆኑት መካከል ሹፌሮች ይገኙበታል።
ፋይ "ውሸትን ተጠቅሞ አክብሮትን ለማግኘት ነው ተቋሙ የተመሠረተው። አንዳንዶች እውነተኛ ማንነታቸውን ያገኙበታል። ምን ዓይነት ባህሪ ማሳየት እንዳለባቸው የሚማሩበትም አሉ" ይላል።
ሐሰተኛውን የሥራ ቦታ ወደ እውነተኛ ቦታ ለመለወጥ አቅም የሚሰጥ ተቋም እንደሆነ ያምናል።
ሹይ፣ ተቋሙን ማዘውተር ከጀመረ ወዲህ የሰው ሠራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ችሎታውን ለማዳበር ራሱን እያስተማረ ነው።
መሥሪያ ቤቶች የሰው ሠራሽ አስተውሎት ክኅሎትን ስለሚጠይቁ ራሱን ዝግጁ እያደረገ ነው።
"የሙሉ ጊዜ ሥራ ለማግኘት ያስችለኛል" ይላል።















