"ከተመረቅኩ በኋላ አንድ ሥራ ለማግኘት 647 ቦታዎች አመልክቻለሁ"

የፎቶው ባለመብት, Caitlin Morgan
ካትሊን ሞርጋን ከዩኒቨርስቲ ከተመረቀች በኋላ ሲቪዋን አደራጅታ፣ ግሩም ማመልከቻ ጽፋ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ሥራዎች ብታመለክትም የሚቀጥራት ባለማግኘቷ ተስፋ እየቆረጠች ነበር።
የ23 ዓመቷ ካትሊን ተስፋዋ እየተሟጠጠ በሄደበት ወቅት 647ኛ ማመልከቻዋ ተለማማጅ የሂሳብ ሠራተኛ ሆኖ የመቀጠር ዕድል አስገኘላት።
ነገር ግን ከ18 ወራት የሥራ መፈለግ ጥረት በኋላ ኬትሊን "ለአራት ዓመታት ዩንቨርስቲ ተምሮ ዲግሪ ማግኘቱ ምን እርባና አለው?" ስትል ትጠይቃለች።
ተማሪዎችን በሚቀጥሩ ተቋማት ላይ የተደረገ የቅርብ ጊዜ ጥናት እንደሚያሳየው ባለፈው ዓመት ለ17 ሺህ ክፍት የሥራ መደቦች 1.2 ሚሊዮን አመልካቾች ተወዳድረው ነበር።
ያለውም ፉክክርም ቢሆን "ከፍተኛ ሆኖ የተመዘገበ" ነው።
ካትሊን በቀን ሁለት ማመልከቻዎችን ለማስገባት ዓላማ አድርጋ ነው የጀመረችው።
150 ጊዜ ማመልከቻዋ ያለ ምንም ግብረ መልስ ውድቅ ተደርጓል።
ለሌሎች 271 ማመልከቻዎቿም ይህ ነው ብሎ አስተያየት የሰጣት አልነበረም።
እሷም "በማመልከቻዎቼ ላይ ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፤ እናም ከእነሱ ምንም ምላሽ ሳላገኝ ስቀር ማመልከቻዬ ምላሽ የማያገኘው ለምንድን ነው? ስል እጠይቅ ነበር።"
ኬትሊን ከስዋንሲ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ እና የሂሳብ ዲግሪዋን ካገኘች በኋላ ለአንድ ዓመት በኢንዱስትሪ ውስጥ ሰርታለች።
ይህም ማመልከቻዋ ከሌሎች አመልካቾች በተለየ ሞገስ ያስገኝልኛል ብላ ተስፋ አድርጋ ነበር።
ከዚያ በተቃራኒው ከመስከረም 2023 ጀምሮ ማመልከቻዎቿ ሁሉ የቅርጫት ሲሳይ ሆኑ።
"ለዲግሪዬ ጠንክሬ ሰርቻለሁ፤ ልምድም ነበረኝ ስለዚህ እያሰብኩ የነበረው ይህን ያህል መልፋት አለብኝ?" የሚል ነበር።
"ፈጽሞ ተነሳሽነት ያጣሁበት ጊዜ ነበር፤ እናም ዩኒቨርሲቲ መግባት ወይም ዲግሪ ማግኘት እርባና የለውም ያልኩበት ጊዜ ነበር።"

ካትሊን ኩባንያዎች አመልካቾችን ለመለየት የሰው ሠራሽ አስተውሎትን መጠቀማቸው ምናልባትም የእርሷ ማመልከቻዎች ውድቅ ለመሆናቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ትገምታለች።
በመጀመሪያ አካባቢ ሲቪዋ የተጻፈው ሰው ሠራሽ አስተውሎት ማመልከቻዎችን ለማንበብ በሚጠቀምባቸው ፕሮግራሞች እንዲነበቡ ተደርገው እንዳልሆነ ታስታውሳለች።
ካትሊን "በቀጥታ ውድቅ እየተደረግኩ ነበር፤ ነገር ግን ካስተካከልኩት በኋላ አንዳንድ ጊዜ ለምዘና መጠራት ጀመርኩ" ብላለች።
"ይህንን ከመጀመሪያው ጀምሮ ባውቅ ኖሮ፣ ለሌሎች ማመልከቻዎቼ ይረዳኝ ነበር።"
ካመለከተቻቸው ሥራዎች ሁሉ ለምዘና የተጠራችው ለ221 ሲሁን፣ በአምስቱ ደቅሞ ለቃለ መጠይቅ ቀርባለች።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በ2024 ለእያንዳንዱ ሥራ በአማካይ 140 ማመልከቻዎች ይመጣሉ።
አንድ የምርመር ተቋም ወደ 40 ሺህ የሚጠጉ አዳዲስ ተማሪዎችን የቀጠሩ 145 ኩባንያዎችን አነጋግሮ ይፋ እንዳደረገው የአመልካቾች ቁጥር ካለፉት 30 ዓመታት ሁሉ ከፍተኛው ነው።
ይህም ከ2023 ጋር ሲነጻጸር ከ50 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ።
አሃዞች እንደሚያሳዩት ከሂሳብ ጋር ለተያያዙ ሥራዎች ለእያንዳንዱ ክፍት የሥራ ቦታ በአማካኝ 188 ማመልከቻዎች ይገባሉ።
ካትሊን ተለማማጅ የሂሳብ ሠራተኛ ሆና የተቀጠረችበት ሥራዋን ለመጀመር በመጪው መስከረም ወደ ለንደን ትጓዛለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በትክክል የምፈልገው ነበር እና በፋይናንስ ውስጥ ማድረግ የምፈልጋቸውን ትምህርቶች ሁሉ ይሰጥ ነበር" ብላለች።
"በጣም በፍጥነት ባገኝ ምኞቴ ነበር።"
ምንም እንኳን ዌልስ በዩናይትድ ኪንግደም የሰው ኃይል ውስጥ ዝቅተኛ የተመራቂዎች ድርሻ ቢኖራትም፣ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚወክለው ቡድን የድኅረ ምረቃ ተማሪዎች ቁጥር በ2035 እንደሚያድግ ያምናል።
የዌልስ ዩኒቨርስቲዎች ቃል አቀባይ "የዛሬው የሥራ ገበያ ለብዙ ሰዎች ተግዳሮቶች እንዳለው ብንገነዘብም፣ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አንድ ዲግሪ የዕድሜ ልክ ገቢን፣ የሥራ ዕድልን እና የግል ዕድገትን ያፋጥናል" ብለዋል።
"ዩኒቨርሲቲው ግለሰቦችን ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባችን እንዲሁም ኢኮኖሚያችንን የሚያጠናክር የለውጥ ተሞክሮ ይሰጣል።"
በዚህ የበጋ ወራት በሺዎች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ተማሪዎች የካትሊንን ፈለግ ለመከተል በዝግጅት ላይ ናቸው።
ሁው ዊሊያምስ በሚቀጥለው ዓመት ወደ ትምህርት ከመመለሱ በፊት ለ12 ወራት ያህል የባንጎር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ኅብረት የዌልስ ኦፊሰር በመሆን ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው።
የ 21 ዓመቱ ወጣት ሁው "የታሪክ መምህር ለመሆን በተለማማጅ መምህርነት የማመለክት ይመስለኛል፤ ሁልጊዜም ሳስበው የነበረው የሙያ መስመር ነው" ይላል።
ሁው የሚቀጥለው ዓመት ለእርሱ ምን እንደሚመስል ቢያውቅም፣ ለባንጎር ተመራቂው አላው ሲምፕሰን ግን መጪው ጊዜ ግልፅ አይደለም።

ዲግሪዋን በቅርቡ ያገኘችው የ21 ዓመቷ አላው ሲምፕሰን ሥራ አገኛለሁ ብላ ወዳሰበችበት የመኖሪያ አካባቢዋ አምርታለች።
እሷም "ከትምህርት ፋታ ወስጄ የተለየ ነገር መሞከር እፈልጋለሁ። ይህ ከባድ ነው ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ በተመረቅክበት ሥራ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል።"
የቅጥር ባለሙያዎች አሁን ብዙ አሠሪዎች በአመለካከት እና በግል ባህሪ ላይ ያተኩራሉ ብለዋል።
በሮበርት ሃፍ ሪክሩትመንት የሚሠሩት ጄምስ ፎርትናም "ከትምህርት በኋላ የመጀመሪያ ሥራ ማግኘት ትልቁ እርምጃ ነው፤ ምክንያቱም ብዙ ልምድ ላይኖራቸው ይችላል" ብለዋል።
"በርካታ አመልካቾች በአሠሪዎች ዘንድ ዕድለኛ ሆነው ለመገኘት ብዙ ሲሉ እሰማለሁ። ለቀጣሪዎች የአመልካቾችን ቁጥር ማሳነስ በጣም ከባድ ነው። እውነታው አመልካቾች ሲቪያቸውን ለሥራው በሚመጥን መልኩ ማደራጀት ይኖርባቸዋል።"
ፎርትናም አንዳንድ ኩባንያዎች የአመልካቾችን ችሎታ ለመገምገም ቴክኖሎጂን ይጠቀማሉ።
"ኩባንያዎች የአንድን ሰው ሲቪ ከሥራው ጋር ለማዛመድ ሶፍትዌሮችን ይጠቀማሉ" ብሏል።
"ብዙ ተመራቂዎች አንዳንድ ጊዜ ያላቸው ልምድ ከሥራው ጋር ተዛማጅ የመሆን ዕድሉ አነስተኛ ነው።"















