ሠራተኞችን ወደ ውጭ የሚልኩ ኤጀንሲዎች ከ5 እስከ 20 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲኖራቸው ሊገደዱ ነው

ለሥራ ወደ ውጭ አገር እየተጓዙ ያሉ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, የኢትዮጵያ የዉጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች አሰሪ ፌዴሬሽን

ኤጀንሲዎች የውጭ ሀገር ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝነት ፈቃድ ለማግኘት ከአምስት እስከ ሃያ ሚሊዮን ብር ካፒታል እንዲኖራቸው የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ምክር ቤቱ ኤጀንሲዎች ከ50 ሺህ እስከ 250 ሺህ አሜሪካ ዶላር የዋስትና ገንዘብ በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የባንክ ሂሳብ ማስቀመጥን ያስገድዳል።

ረቂቅ አዋጁ ኤጀንሲዎች በራሳቸው ሠራተኞችን የሚመለምሉበትን አሠራር የሚያስቀር ድንጋጌ ተካትቶበታል።

በሥራ ላይ በሚገኙ የውጭ አገር ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጄንሲዎች ረቂቅ አዋጁ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አዋጅ' የሚል ርዕስ ያለው ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሐሙስ ሰኔ 5/2017 ዓ.ም. ነው።

አዋጁን ለማብራራት በ11 ገጾች የተዘጋጀው ሰነድ "የዜጎች መብት፣ ክብር፣ ደኅንነት እና ጥቅም በተሻለ መልኩ ሊያስጠብቅ" የሚችል አዋጅ መዘጋጀቱን ጠቁሟል።

ማብራሪው የረቂቁ መነሻ ግብ እና ዓላማ "ዜጎች መብታቸው፣ ደኅንነታቸው እና ክብራቸው በዘላቂነት መጠበቁን" ማረጋገጥ እንዲሁም "አገራችን ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ማስጠበቅ" እንደሆነ ያስረዳል።

በሰባት ክፍል እና 85 አንቀጾች የተዘጋጀው ረቂቅ ከስምንት ዓመታት በፊት የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ እና ከአራት ዓመታት በፊት የጸደቀውን ማሻሻያ የሚሽር ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እስካሁን ድረስ በሥራ ላይ የነበረው አዋጅ እና ማሻሻያው "በዋናነት የቤት ውስጥ ሠራተኞች ወደ ተቀባይ ሀገር ለሥራ ለማሠማራት ብቻ" ተፈጻሚነት የነበራቸው መሆኑን የረቂቁ ማብራሪያ ላይ ሰፍሯል።

በመሆኑን በዚህ ምክንያት "የሰለጠኑ ዜጎችን ለማሠማራት አለመቻሉን" ያክላል። በ2013 የጸደቀው የአዋጅ ማሻሻያ "የሠለጠነ የሰው ኃይልን ወደ ሥራ ለማሠማራት. . .በበቂ ሁኔታ ችግሩን ሊፈታ አለመቻሉ" ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም "ሁለቱ አዋጆች የማያውቋቸው ጉዳዮች በመከሰታቸው እና ለማስተናገድ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በመፈጠራቸው" አዲስ አዋጅ ማዘጋጀት ማስፈለጉ ማብራሪያው ላይ ሰፍሯል።

በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ መሠረት የስምሪት ሂደቱ ላይ ያለውን "የደላሎችን ሕገ-ወጥ ድርጊት" ለማስቀረት የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ያበለጽጋል።

ስለትርጓሜዎች እና የተፈጻሚነት ወሰን ከሚያትተው የመጀመሪያ ክፍል ቀጥሎ የሚገኘው የአዋጁ ድንጋጌ የሚያወራው ስለዚሁ የመረጃ ሥርዓት ነው።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር "የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት አገልግሎት ለመስጠት" የተዘረጋውን የገበያ መረጃ ሥርዓት ተግባራዊ እንደሚያደርግ ረቂቁ ይገልጻል።

ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ አፈጻጸሙን የመከታተል፣ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ቋት የማደራጀት ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ይኼው የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አገልግሎቶች "በሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት ውስጥ ማለፍ እና መረጃው በአግባቡ መያዝ" እንደሚኖርበት ረቂቅ አዋጁ ይደነግጋል።

የሠራተኛ ምልመላ እና ስምሪት አገልግሎት "ከደላላ ነጻ በሆነ መንገድ" የሥራ ምደባ እንደሚከናወን የረቂቅ አዋጁ እንደሚከናወን ያስቀምጣል።

በረቂቁ መሠረት ለውጭ ሀገር ሥራ የሚሰማሩ "ሥልጠና የወሰዱ እና ብቃታቸው የተረጋገጠ" ሠራተኞች ኤጀንሲዎች በሚያቀርቡት የሥራ ትዕዛዝ መሠረት በሚኒስቴሩ ይመደብላቸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ወደ ውጭ ሀገር መሰማራት የሚፈልግ ዜጋ ምልመላ የሚከናወነው "ከአንድ ማዕከል አገልግሎት ጀምሮ በተዘረጋው የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በኩል ብቻ መሆን አለበት" የሚል ድንጋጌ በረቂቁ ላይ ተካትቷል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር "የሠራተኞችን ምልመላና ስምሪት በሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት በኩል መሆኑን ይከታተላል።"

ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና የውጭ አገር ሥራ ስምሪት ኤጀንሲዎች ጋር የሠሩ ሁለት ግለሰቦች ለዚህ አዲስ አሠራር የተለያየ አቋም አላቸው።

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ እና በዘርፉ ላይ ዘጠኝ ዓመት ገደማ የሠሩ ግለሰብ፤ "ሥራ ላይ ያለው ምልመላ እና ሥልጠና ጥራቱን የጠበቀ ካልሆነ [አዲሱ አሠራር] ጥሩ ሊሆን ይችላል" ይላሉ።

"በቂ ሥልጠና ሳያገኙ ምዘናውን ባልተገባ መንገድ ይታለፋል ተብሎ ከተፈራ አሁን መንግሥት ያደረገው ነገር የተሻለ ነው" ሲሉ ያክላሉ።

ላለፉት አምስት ዓመታት በተመሳሳይ ዘርፍ ላይ የቆዩት አቶ አብዱልቃድር ኢብራሂም በበኩላቸው ይህ አሠራር "የአገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ያላደረገ ነው" ሲሉ ይቃወማሉ።

"ይሄ አሠራር ከአንድ ዓመት በፊት ተሞክሮ ነበር ከአንድ ሳምንት በላይ ግን መቆየት አልቻለም" የሚሉት አብዱልቃድር፤ "በወቅቱ አሠራሩ የከሸፈው በሕግ ክፍተት ሳይሆን ያንን ነገር ማስኬድ የሚችል አቅም ካለመኖሩ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"ተሞክሮ ያልሠራን ነገር በሕግ አስገዳጅ አድርጎ ማምጣቱ አስፈላጊነቱ ብዙም የሚታይ አይደለም" ይላሉ።

አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለውጭ አገር ሥራ ስምሪት ብቁ የሚያደርገው የትምህርት መስፈርት ላይም ማሻሻያ አድርጓል።

ከዘጠኝ ዓመት በፊት ወጥቶ ሥራ ላይ የዋለው አዋጅ ለሥራ ወደ ውጭ አገር የሚሄዱ ሠራተኞች "ቢያንስ ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ" መሆን እንዳለባቸው ያትታል።

በ2013 ዓ.ም. የወጣው የአዋጅ ማሻሻያ ይህን የትምህርት መስፈርት "በሚቀጠርበት የሥራ መስክ ሥልጠና" በመውሰድ ተክቶታል።

የረቂቁ ማብራሪያ "የትምህርት ደረጃን ጨርሶ ማውጣትም ሆነ የትምህርት ደረጃን እንደ መስፈርት ማስቀመጡ የየራሳቸው አሉታዊ እና አዎንታዊ ተጽዕኖ" እንዳለው ያስረዳል።

በመሆኑም "የግድ እና በቀጥታ እንደ መስፈርት ሳያስቀምጥ" ነገር ግን ወደ ውጭ ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎችን የትምህርት "ፍላጎት ተነሳሽነት ላይ ግን አሉታዊ ተጽዕኖ በማያስከትል" መልኩ በረቂቁ መካከቱን ያትታል።

የረቂቁ አራተኛ ክፍል ለኤጀንሲዎች ስለሚሰጥ የሥራ ፈቃድ እና ለፈቃድ ብቁ ስለሚያደርጉ መስፈርቶች በዝርዝር ያስቀምጣል።

ረቂቁ "ኤጀንሲ ሆኖ ለመሥራት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ከሚኒስቴሩ ፈቃድ ማግኘት ይኖርበታል" ይላል።

የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር በረቂቅ አዋጁ ተዘረዘሩ መስፈርቶችን መሠረት በማድረግ ለኤጀንሲዎች ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ የያዘ ፈቃድ እንደሚሰጥ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።

እነዚህ መስፈርቶች ኤጀንሲዎች የሚያሰማሩት የሰው ኃይል ብዛት߹ ክህሎት߹ እና የሙያ ዘርፍ እንዲሁም መነሻ ካፒታል ናቸው።

ረቂቁ ኤጀንሲዎች ለጠየቁበት ደረጃ የሚጠበቅባቸውን የካፒታል መጠን ማሟላት እንዳለባቸውም አስገዳጅ ድንጋጌ አለው።

ለደረጃ አንድ ኤጀንሲ ፈቃድ ለማውጣት የሚፈልግ አመልካች 20 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወይም አክሲዮን ወይም መዋጮ ሊኖራቸው ይገባል።

ለደረጃ አራት 12 ሚሊዮን፣ ለደረጃ ሦስት 10 ሚሊዮን ብር፣ ለደረጃ አራት 7.5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለደረጃ አምስት 5 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወይም አክሲዮን ወይም መዋጮ እንዲኖራቸው ረቂቁ ያስገድዳል።

በሥራ ላይ ባለው የውጭ አገር ሥራ ስምሪት አዋጅ አመልካቾች የሚጠበቅባቸው "ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ ካፒታል" ነበር።

አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት ግለሰብ ይህ ቅድመ ሁኔታ "[የኤጀንሲዎችን] ቁጥር በጣም ይቀንሰዋል afford የሚያደርገው [መክፈል የሚችለው] በጣም ጥቂት ነው የሚሆነው። ወደ ሥራው መግባትን በጣም ከባድ ያደርገዋል። ስለዚህ ወደዚህ ሥራ መግባት አዋጭ አይሆንም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ አብዱልቃድር ኢብራም በበኩላቸው "እኛ አምራች አይደለንም፤ አገልግሎት ነው የምንሰጠው። በውጭ ያለውን ሠራተኛ ፈላጊ እና እዚህ ያለውን ሥራ ፈላጊ ማገኛነት ነው [የምንሠራው]። ይሄ እጅግ በጣም አላስፈላጊ እና የተጋነነ ነው" የሚል ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በተጠቀሱት ቅድመ ሁኔታዎች ለኤጀንሲዎች ፈቃድ ከመስጠት በተጨማሪ የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ፈቃድ የማገድ እና የመሰረዝ ሥልጣን ተሰጥቶታል።

የፈቃድ ስረዛ ከሚያስከትሉ ጉዳዮች መካከል "አዋጁ እና ተከትለው በሚወጡ ደንብ እና መመሪያዎች መሠረት ፈቃድ በወቅቱ አለማሳደስ" አንደኛው ነው።

"የሕዝብን ጤና ወይም ሞራል በሚጎዳ ወይም የአገሪቷን ክብር እና ገፅታ ለሚያጎድፍ ሥራ ሠራተኛን ማሰማራት" እንዲሁም "የሥራ ስምሪት አገልግሎትን ምክንያት በማድረግ ከሠራተኛ ገንዘብ በጥሬም ሆነ በዓይነት መቀበል" ስረዛ የሚያስከትሉ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም "ሠራተኛን በፀደቀው የሥራ ውል ከተመለከተው አሠሪ ውጭ የሥራ ውሉ ሳይስተካከል ወይም ሳይቀየር ለሌላ አሠሪ ማስተላለፍ" ኤጀንሲዎችን እንዲሰረዙ ያደርጋል።

ፈቃዱ የተሰረዘበት ኤጀንሲ ሥራ እና ሠራተኛ የማገናኘት ተግባሩን እንደሚያቆም የጠቆመው ረቂቁ፤ ነገር ግን ውሳኔው "ፈቃድ የተሰረዘበት ኤጀንሲ የላካቸው ሠራተኞች ከሚያነሱት የመብት ጥያቄ ነፃ አያደርገውም" ይላል።

ረቂቅ አዋጁ ከካፒታል መጠን በተጨማሪ ማንኛውም ኤጀንሲ "ለሠራተኛው መብት ክብር እና ደኅንነት ዋስትና ማስከበሪያ የሚውል ገንዘብ" እንዲያስቀምጡ የሚያስገድድ ድንጋጌ አለው።

በሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የባንክ ሂሳብ ቁጥር የሚቀመጠው ይህ የዋስትና ገንዘብ በአሜሪካን ዶላር ወይም በተመጣጣኙ የኢትዮጵያ ብር ነው።

እንደ ካፒታል መጠኑ ሁሉ የዋስትና ማስከበሪያ ገንዘብ መጠን በኤጀንሲዎች ደረጃ ይለያያል። የደረጃ አንድ ኤጀንሲዎች 250 ሺህ የአሜሪካን ዶላር የዋስትና ገንዘብ ማስቀመጥ ይኖርባቸዋል።

ከደረጃ አምስት እስከ ሁለት ያሉት ኤጀንሲዎች ደግሞ እንደቅደም ተከተላቸው ከ50 ሺህ እስከ 200 ሺህ አሜሪካ ዶላር የዋስትና ገንዘብ የማስቀመጥ ግዴታ ተጥሎባቸዋል።

ኤጀንሲዎች ሠራተኛን ወደ አገር መመለስን የተመለከተውን ግዴታ ካልተወጡ "ሚኒስቴሩ ተቀማጭ ከሆነው የዋስትና ገንዘብ ላይ ወጪ በማድረግ ለሠራተኛው መብት፣ ክብር እና ደኅንነት ዋስትና ማስከበሪያ" እንደሚያውል ረቂቁ ይገልጻል።

ከእነዚህ ግዴታዎች መካከል "የሥራ ውል እንደተቋረጠ የአየር ትራንስፖርት ወጪን በመሸፈን ሠራተኛውን እና የግል መጠቀሚያ ንብረቶቹን ወደ ሀገሩ መመለስ" ቀዳሚው ነው።

"ሠራተኛው ከባድ የአካል ጉዳት ሲደርስበት ወይም ሲሞት. . .ስለደረሰበት ጉዳት ወይም ሞት ከሚገልጽ ሕጋዊ የሕክምና ማስረጃ ጋር በማያያዝ በ15 ተከታታይ ቀናት ውስጥ ወደ ሀገሩ የመመለስ እና ተያያዥነት ያላቸው ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን" ሌላኛው የኤጀንሲዎች ግዴታ ነው።

በሥራ ላይ ባለው አዋጅ ከኤጀንሲዎች "ለሠራተኛው መብት እና ደኅንነት ዋስትና ማስከበሪያ" ማስቀመጥ የሚጠበቅባቸው 100 ሺህ ዶላር ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የዋስትና ገንዘቡን የሚያስቀምጡት በራሳቸው ዝግ የባንክ ሂሳብ ነው።

አቶ አብደልቃድር የዋስትና ገንዘቡ ወደ 250 ሺህ ዶላር ከማደጉ በተጨማሪ የሚቀመጥበት ሁኔታ ላይ ቅሬታ አላቸው።

ከዚህ በፊት የዋስትና ገንዘብ "ከባንኮች ጋር በሚኖረን ስምምነት በብድር መልክ ብሩ አካውንታችን ላይ በዝግ ሂሳብ ገብቶ ነበር የሚሰጠው" ሲሉ የቀደመውን አሠራር ያስረዳሉ።

አቶ አብዱልቃድር "የዋስትና ገንዘቡ በፊት እኛ ከባንኮች ጋር በሚኖረን አሠራር ብድሮች እያገኘን በራሳችን አካውንት በዝግ ሂሳብ ነበር የሚቀመጠው፤ አሁን ግን የተደረገው ሙሉ በሙሉ በጥሬ ገንዘብ የሚኒስቴሩ አካውንት ላይ እንዲገባ ነው የተደረገው" ሲሉ ነባሩን እና አዲሱን አሠራር ያነጻጽራሉ።