ኤርትራውያን በእስራኤል ጎዳናዎች ላይ ለምን ወደ ሁከት አመሩ?

ኤርትራውያን በእስራኤል የመንግሥት ተቃዋሚ እና ደጋፊ በሚል ተጋጭተው በርካቶች ሲቆስሉ ከ50 በላይ ደግሞ በቁጥጥር ስር ውለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኤርትራ ውስጥ የተቃውሞ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እና ሠላማዊ ሰልፎች እምብዛም ናቸው።

በተለያዩ አገራት የሚኖሩ በርካታ ኤርትራውያን ደግሞ የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ አገዛዝን በመቃወም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እና ሰላማዊ ሰልፎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል።

በአገሪቱ የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዲደረግ፣ ምርጫ እንዲካሄድ፣ የፖለቲካው ምህዳር እንዲሰፋ፣ በፖለቲካ ልዩነት ምክንያት የታሰሩ እንዲፈቱ እና ለብዙ ወጣቶች ፍልሰት ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለት ገደብ የለሽ ወታደራዊ አገልግሎት እንዲቆምና መሰል ጥሪዎች ተደጋግመው ተሰምተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በተለይም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ግን በስርዓቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል ሁከቶች ሲቀሰቀሱ እና ከፍተኛ ጉዳቶች ሲደርሱ ታይተዋል።

የኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች በወርሀ ሐምሌ በጀርመን የጊሰን ዓመታዊ ፌስቲቫልን አዘጋጅተው ነበር። በአዘጋጆቹና ፌስቲቫሉን ለመበተን በተንቀሳቀሱ ወጣቶች መካከል ሁከት ተቀስቅሶ 26 ፖሊሶችን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። በርካቶችም ታሰረው ክስ ተመሰርቶባቸዋል።

እአአ ነሐሴ 3 2023 ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑ ከመላው አውሮፓ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተዘጋጀውን ዓመታዊ ፌስቲቫል ሰብረው በመግባት ጥቃት ፈጸሙ። በሁከቱ ከ50 በላይ ሰዎች ጉዳት ደረሰባቸው። ከ 100 የሚበልጡት ደግሞ መታሰራቸውን ፖሊስ ገልጾ ነበር።

በተመሳሳይ ባለፈው ወር በቶሮንቶ ካናዳ ለሦስት ቀናት ሊካሄድ የነበረ ፌስቲቫል በደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች በተቀሰቀሰ ሁከት ተቋረጠ። ሁከት ሊነሳ ይችላል ብለው በሰጉ እንደ ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ አገራት ደግሞ ፌስቲቫሉ እንዳይካሄድ ከልክለዋል።

ከሁሉም የከፋው ሁከት በእስራኤል ቴል አቪቭ የተፈጸመው ነው።

ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 27 2015 በእስራኤል በሚኖሩ በኤርትራውያን መካከል የተፈጠረው ሁከት ከፍተኛ ጉዳትና ውድመት አስከትሏል። የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስቧል። እስራኤልንም አስቆጥቷል።

ሁከቱ የተፈጠረው በኤርትራ መንግሥት ደጋፊዎች የተዘጋጀ ነው የተባለውን ዝግጅት ለማወክ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የኤርትራ መንግሥት ተቃዋሚዎች፣ ፌስቲቫሉ ወደሚዘጋጅበት ቦታ በኃይል ከገቡ በኋላ ነው።

ሁከቱን ለመቆጣጠር የእስራኤል ፖሊስ ጥይት፣ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይቶችን ለመተኮስ ተገድዷል።

ግጭቱ ተስፋፍቶ ስደተኞቹ ድንጋይ፣ እንጨት እና ብረቶችን በመጠቀም በሚዘገንን ሁኔታ እርስ በእርስ ሲደባደቡ ታይተዋል። ከዚህ ባለፈም መኪኖች እና መስኮቶችን ሰባብረዋል።

የቴል አቪቭ ጎዳናዎች ለሰዓታት የጦር ሜዳ መስለው ነበር። የአደጋ ጊዜ ድምጽ መሰማቱን እና ሂሊኮፕተር ሲያንዣብብ መመልከታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

ከ170 በላይ ስደተኞች እና ከ50 በላይ ፖሊሶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ንብረት ላይም ከፍተኛ ውድመት ደርሷል።

ግጭቱን ተከትሎ “ቀይ መስመር መጣሱን” የገለጹት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤንያሚን ኔታንያሁ፤ በግጭቱ የተሳተፉ ኤርትራውያን እና ሌሎች በሕገ ወጥ መንገድ የገቡ አፍሪካውያንን እንደሚያባርሩ ዝተዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽህፈት ቤት በሁከቱ የተሳተፉ ኤርትራውያንን ወደ ትውልድ አገራቸው ለመመለስ ሚንስትሮችን በአባልነት የሚያቅፍ ግብረ ኃይል ይቋቋማል ብሎ ነበር።

“ባቋቋምነው ካቢኔ አንድ ሺህ የሚሆኑ በግጭቱ የተሳተፉ የስርዓቱ ደጋፊዎችን ማባረርን የሚያጠቃልል እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀናል። ስደተኞች ነን ማለትም አይችሉም። የስርዓቱ ደጋፊዎች ናቸው። የሚደግፉት ከሆነ ወደ አገራቸው መመለስ ይችላሉ” ሲሉ ኔታንያሁ ተናግረዋል።

አንድ ኤርትራዊ እስራኤላዊ ባለ ሱቅ ሁኔታውን “መዓት” ሲል ገልጾታል።

“ሁኔታው አስደንግጦናል። ኃፍረት እና ሐዘን ተሰምቶናል። ደህንነት አይሰማንም። ወዴትስ መሄድ እንችላለን? አገራችን ውስጥ ከነበረው ስቃይ ብንሸሽም፣ አምባገነኑ ስርዓት ግን አፋችን ለመዝጋት እያሳደደን ነው“ ብሏል።

ሌላ ኤርትራዊ ደግሞ “ብዙ የተጎዱ ሰዎች አይቼ አዝኛለሁ። ምክንያቱ ሁለቱም ከኔ ወገን ናቸው “ ብሏል።

ተቃውሞዎቹ ለምን ወደ ሁከት ማምራት ጀመሩ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቀደም ሲል በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥርያ ቤት ያገልገሉት እና በእንግሊዝ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በዲያስፖራ ፖለቲካ እየተከታተሉ የሚገኙት ዘርዓ ሥላሴ ረዳኢ ሸከር፤ በስደተኞች ላይ እየበረታ የመጣው ቁጣ ‘የብዙ ችግሮች ድምር ነው’ ሲሉ ይገልጹታል።

“ከነጻነት በኋላ ለረዥም ዓመታት፣ በተለይም እአአ ከ1998 ጀምሮ፣ ስርዓቱ በዜጎች ላይ ሲፈጽም የቆየው በደል፣ ሕዝብን ያገለለ እና የከፋፈለ የስርዓቱ አካሄድ ያስከተለው ውጤት ነው” ይላሉ።

ጂ-15 በመባል የሚታወቁት በኤርትራ የለውጥ እና ዲሞክራሲ ጥያቄ ያቀረቡ የሠራዊት አመራሮች እና ሚኒስትሮች እአአ መስከረም 2001 በመንግሥት ከታሠሩ በኋላ የገቡበት አይታወቅም።

ከፖለቲካ እና ሃይማኖት ነጻነት ጋር ተያይዞ አገሪቱ ዜጎቿ ላይ የመብት ጥሰት ትፈጽማለች የሚል በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ትከሰሳለች።

ገደብ ያልተበጀለት ወታደራዊ አገልግሎትም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣቶች አገራችው ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።

ኤርትራ ግን ተቋማቱ የምዕራባውያን የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ እንደሆኑ በመግለጽ ለፍልሰቱም የአገራቱን ፖሊሲ ተጠያቂ ታደርጋለች።

በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌስት ለንደን መምህር እና ሳይኮቴራፒስት የሆኑት ሠላም ኪዳነ በበኩላቸው የኤርትራ መንግሥት የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ለተቃውሞ እና ለሁከት ምክንያት መሆናቸውን ይገልጻሉ።

አውሮፓና ሰሜን አሜሪካን ጨምሮ ኤርትራውያን በተሰደዱበት አገር ማኅበረሰቡ “የራሳችሁን በተለይም የጥላቻ እና የጦርነት ፕሮፖጋንዳ እንድታካሂዱ አንፈቅድም” ሲል መቆየቱን ገልጸዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተቃዋሚዎች እና በመንግሥት ደጋፊዎች መካከል በተለያዩ አገራት እየተባባሰ የመጣው ሁከት “መጥፎ አጋጣሚ” እና “ሁሉንም ኤርትራዊ የሚያከስር፤ መሆን የማይገባው” በማለት የዲያስፖራ ፖለቲካ አጥኚው ዘርዓ ሥላሴ ያስረዳሉ።

ሠላማዊ እንቅስቃሴዎች ፍሬ ባለማፍራታቸው የተፈጠረ መሆኑንም ያነሳሉ።

“ስርዓቱ ወደ ቀልቡ እንዲመለስ፣ ችግሮች በዲሞክራሲያዊ መንገድ እንዲፈቱ እና ስልጣን ለሕዝብ እንዲያስረክብ በጽሑፍም በመግለጫም ጥሪ ቀርቧል። በአገር ውስጥም በውጭም እንቅስቃሴዎች ተደርገዋል። ስርዓቱ ግን ጆሮ ዳባ ልበስ አለ። ብዝበዛው በመቀጠሉ እና ተቃዋሚው በመብዛቱ የተቃውሞ ዕድገት መኖሩ ተፈጥሯዊ ነው” ብለዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ፣ በተለይ ውጭ በሚኖሩ ወጣት ስደተኞች እየተካሄዱ ያሉ ሰልፎች፣ ብዙ ሰዎች እየተሳተፉባቸው ያሉ ቢሆኑም፤ ያልተደራጁ እና አስተባባሪዎቹ የማይታወቁ እንደሆኑ ይገለጻል።

የዳያስፖራ ፖለቲካ አጥኚው ግን በዚህ አይስማሙም።

“ማህበራዊ እንቅስቃሴ በባህሪው ሁሉን አቀፍ ነው። እንቅስቃሴው ሁሉንም የስርዓቱን ተቃዋሚዎች ያቀፈ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቲንክታንኮች፣ አንቂዎች፣ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ያሉት በየአካባቢው የተደራጀ ነው“ ይላሉ።

“የተለያዩ ቦታ የተለያዩ መሪዎች አሉ” የሚሉት ሠላም ለምሳሌ በለንደን ተቃውሞ ለማዘጋጀት “ብዙ ወጣቶች እና እናቶች ነበሩ የሚታዩት” ብለዋል።

“ለዛች ሰዓት በሚል የሚደረግ ዝግጅት ነው። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ብዙ ሥራ ይሠራል። ብዙ ሃሳብ እና ሀብት የመሰብሰብ አቅምም ተፈጥሯል። አንድ አስተባባሪ ያለው ነው ማለት ግን አይቻልም” ሲሉ ገልጸዋል።

በእስራኤል ያለውም ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

በእስራኤል ያሉ ኤርትራውያን ዘንድ መንግሥትን የሚደግፍ ሊኖር አይገባም የሚሉት ሠላም፣ ምክንያት ሲባሉ “ከዚህ መንግሥት አስከፊ ጥቃት ሸሽተን የመጣን ነን የሚሉ ናቸው። ሌሎች አገሮች ከስርዓቱ በፊት የመጡ እና የተወለዱ አሉ። በእስራኤል ግን ሁሉም ሸሽተው የመጡ ናቸው። ደጋፊ ሊኖር አይገባም” ብለዋል።

መንግሥት ‘ትንንሽ ልዩነቶችን ተጠቅሞ ትልልቅ ጥላቻ እንዲኖር እና የራሱን ፕሮፖጋንዳ ለማካሄድ ስለሞከረ’ ግጭቱ መፈጠሩን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለተከታታይ ቀናት “መንግሥት እና ደጋፊዎቹ ‘እየተዘጋጀን ነው እናሳያቸዋለን ሲሉ ነበር። 4ጂ የሚባል ቡድን አለን በሚገባ ይጠብቃችኋል።’ ‘ሃደ ልቢ’ የሚባልም ቡድንንም ሲያሰለጥኗቸው እና ሲያዘጋጇቸው የሚያሳይ ቪዲዮ፣ ፎቶ እና ጽሑፍ ሲሰራጭ ነበር” ብለዋል።

የኤርትራ መንግሥትን የሚቃወሙት ደግሞ ራሳቸውን “ብርጌድ ንሐመዱ” ብለው ይጠራሉ። “አገሬን፣ መሬቴን፣ ሕዝቤን ነጻ አወጣለሁ” የሚል ትርጉም እንዳለው ዘርዓ ሥላሴ ይገልጻል።

ኤርትራውያኑ የመንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች ጎራ ለይተው በቴል አቪቭ ያገጠመው ሁከት ከአሁን በፊት ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ ምንጮች ይገልጻሉ። ሆኖም ግን የመጀሪያው አይደለም።

እአአ በ2019 በደቡብ ቴል አቪቭ አጋጥሞ በነበረ ተመሳሳይ ሁከት፤ አንድ ጥገኝነት ጠያቂ የኤርትራ መንግሥት ደጋፊ በስለት ተወግቶ ሕይወቱ አልፏል።

ግጭቶቹ ለስደተኞቹ ለምን ስጋት ሆኑ?

በእስራኤል 18 ሺህ በላይ ጥገኝነት ጠያቂ ኤርትራውያን እንደሚኖሩ ይገመታል። አብዛኛዎቹም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የገቡ ናቸው።

ቀደም ሲል የኢኮኖሚ ስደተኞች ናቸው በሚል ቴል አቪቭ ከአገር ልታስወጣቸው ጥረት አድርጋለች። የፍርድ ቤት ክልከላ ግን ጥረቱ እንዳይሳካ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል።

እስራኤል ውስጥ ስደተኞችን የማይፈልጉ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች አጋጣሚውን ስለሚጠቀሙበት (ግጭቱ) ተጽዕኖ እንደሚኖረው ሠላም ያምናሉ።

“በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት ጥገኝነት የጠየቀን አካል ወደመጣባት ቦታ አትመለስውም” ብለዋል።

ወንጀል የፈጸሙ አሉ ከተባለ “መጠበቅ አለብን። መንግሥታችንን ነው የምንደግፈው ብለው ከኤርትራ ኤምባሲ ጋር ሲሠሩ እና ወገኖቻቸውን ሊያጠቁ ሲዘጋጁ የነበሩት በሚደርስባቸው ነገር ምንም ቅሬታ የለኝም” ሲሉ ገልጸዋል።

ኤርትራውያኑን ወደ ሦስተኛ አገር እንዲሄዱ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ግን ጠቁመዋል።

“በእስራኤል መንግሥት የተሳሳተ ሰለባ ላለመሆን የኤርትራን የተሳሳተ መንገድ ዝም አትልም። ይህንን ከግምት አስገብተው የወሰኑት ነው” ሲሉ ተቃውሞውን ስለተቀላቀሉት ተቃዋሚዎች ተናግረዋል።

“ውጤቱ ጎጂ ነው። አገራቸው ጥሩ ስላልሆነላቸው ነው የተሰደዱት፤ ደልቷቸው አልወጡም” የሚሉት የቀድሞው የኤርትራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባልደረባው ዘርዓ ሥላሴ “የእስራኤል የጥገኝነት ሕግ ከለላ የሚሰጥ አይደለም። [ስደተኞቹን ለማባረር ] ሊጠቀሙበት ይችላሉ። ሚዲያ ላይም እስራኤል እንደዚህ አይነት ነገር አጋጥሟት አያውቅም የሚል ተረክ እየተጠቀሙ ነው” ሲሉ አክለዋል።

ተቃውሞው ከአገር ውጭ ለምን በረታ?

ስርዓቱ የአገሪቱን የጸጥታና ወታደራዊ ኃይል ተጠቅሞ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሕጋዊ ጥያቄዎችን ለሚያነሳ “የአገር ጠላት አድርጎ የማጥቃት ባህርይ ስላለው ነው [ፖለቲካዊ እንቅስቀሴውን] በውጭ አገር የምናየው” ይላሉ።

የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ተቃውሞው ወደ አገር ውስጥም መዛመቱ አይቀርም ሲሉም ግምተቸውን ያስቀምጣሉ።

“በውጭ አገር ያለው መንግሥትን ከተቃወመ በውስጥ ያለውም ስርዓቱን ይቃወመዋል። መች ይገናኛል የሚለው ግን የጊዜ ጉዳይ ነው” ብለዋል።

ከአገር ውጭ በርካታ ተቃውሞች መደረጋቸውን የሚገልጹት ሠላም ‘ተጽዕኖ የነበራቸው እና ያልነበራቸው’ እንደነበሩ ጠቁመዋል።

የእስራኤሉ ሁከት በመላው ዓለም መገናኛ ብዙሃን መዘገቡ የራሱ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ግምታቸውን አስቀምጠዋል።

“ለምሳሌ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በትግራይ ህዝብ ላይ የደረሰውን ነገር እንደ መቀለጃና መጫወቻ፤ ሞታቸውን እንደ ድል እየተቆጠረ የሚደረገው ነገር ሁላችንም ልንቃወመው የሚገባን ነገር ነው። ታዳጊ ወጣቶችን መሳሪያ የሚመሰል መጫወቻ በመስጠት ወታደራዊ ልብስ በማስለበስ ለፕሮፖጋንዳ መጠቀም፤ የኤርትራ መንግሥትን የማይደግፉትን እንደማይረቡና እንደ እንስሳ በማድረግ ለማቅረብ የሚደረግ ፌስቲቫል ለማንም አይጠቅምም” ብለዋል።

ይህን መሠሉን ዝግጅት ቀደም ሲል በሠላማዊ መንገድ ለመቃወም መሞከሩን ጠቅሰው፣ አሁን አልፎ አልፎ ወደ ሁከት ማምራቱን አስታውቀዋል።

ተመሳሳይ ዝግጅት እንደ እንግሊዝ ባሉ አገራት መቅረቱን አንስተው ይህንንም “መልካም ውጤት” ብለውታል።

የኤርትራ መንግሥት ስለተቃውሞ ሠልፎቹ ምን አለ?

የኤርትራ መንግሥት ልሳን በሆነው ሻባይት ጋዜጣ መስከረም 5 2023 የወጣው አጭር ጽሑፍ አንዳንድ አገሮች ባህላዊ ፌስቲቫሉን ለማወክ፤ የተፈጠረው ሁከት “ሲያበረታቱ ታይተዋል” ሲል ከስሷል።

የእስራኤሉ የስለላ ድርጅት ሞሳድንም ወቅሷል።

“የማይበገረው የኤርትራ ሕዝብ የመከላከል አቅም ያስደነገጣቸው ትልልቅ የስለላ ተቋማት (ሞሳድን ጨምሮ) የኤርትራ ሕዝብን አንድነት ለማወክ ጥቂት ባንዳዎች የወጠኑት ከንቱ ተንኮል” በማለት በቀጣይ ዝርዝር መግለጫ አንደሚሰጥ አስታውቋል።