ኤቨረስት ላይ ጠፍቶ የነበረው ኬንያዊ ተራራ ወጪ ህይወቱ አልፎ ተገኘ

ኪሩይ ህልፈተ ህይወት በዚህ ሳምንት በኤቨረስት ላይ የተመዘገበ አራተኛው ሞት ነው

የፎቶው ባለመብት, JAMES MUHIA

በኤቨረስት ተራራ ጫፍ አካባቢ ጠፍቶ የነበረው ኬንያዊው ተራራ ወጪ ህይወቱ አልፎ ተገኘ።

የአርባ ዓመቱ ጆሹዋ ቼሪዮት ኪሩይ እና የ44 ዓመቱ ኔፓላዊ አስጎብኚው ናዋንግ ሼርፓ ረቡዕ ዕለት የጠፉ ሲሆን ኪሩይ ያለተጨማሪ ኦክሲጅን ኤቨረስት ተራራን የወጣ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ለመሆን ጥረት በማድረግ ላይ ነበር ተብሏል።

ጥንዶቹን ለማግኘት የተሰማራው የፍለጋ ቡድን አስጎብኚውን እስካሁን እንዳላገኘው የአካባቢው የቱሪዝም ባለስልጣን ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግረዋል።

የዓለማችንን ረዥሙን ተራራ ኤቨረስትን መውጣት ልምድ ላላቸውም ጭምር በጣም ከባድ እና አደገኛ ነው ተብሎ ይታሰባል።

የኔፓሉ ሂማሊያን ታይምስ ጋዜጣ ሼርፓ ያስተላለፈውን መልዕክት ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ኪሩይ “ያልተለመደ ባህር” እንዳሳየ እና “ለመመለስም እና የታሸገ ኦክስጅንን ለመጠቀም ፈቃደኛ እንዳልሆነ” ተናግሯል።

ከመልዕክቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከሁለቱ ግለሰቦች ጋር የነበረው ግንኙነት መቋረጡን ባለሥልጣናቱ ለጋዜጣው ተናግረዋል።

የኪሩይ የቅርብ ጓደኛ ኪፕኬሞይ ሊሞ ደግሞ ወድቆ ህይወቱ ማለፉን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቤተሰቦቹ እና ጓደኞቹ ኪሩይ በኤቨረስት ለመቀበር ፍቃድ ስለመስጠቱ ወይም 190 ሺህ ዶላር በማውጣት አስከሬኑን ወደ ኬንያ እንዲመለስ ስለመናዘዙ እየጠየቁ ናቸውው ብሏል።

ባለፈው ሳምንት ኪሩይ ከቢቢሲ በነበረው ቆይታ ከባዱን ተራራ ለመውጣት ከመጋፈጡ በፊት በቂ የአካል ብቃት ዝግጅት እንዳደረገ ተናግሮ ነበር።

"ዋናው ዝግጅት ባለፈው ዓመት መስከረም በዓለም ስምንተኛ የሆነውን ረዥሙን ምናስሉ ተራራ መውጣት ነበር" ሲል ለቢቢሲ በላከው ኢሜይል ጽፏል።

"ነገር ግን በኬንያ ተራራዎችን እየወጣሁ ነበር። ብዙ ደረጃዎችን መውጣት፣ በጂም አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እና በልዩ ዝግጅት እሮጥ ነበር። በተጨማሪም ለ 10 ዓመታት ያህል በማራቶን እና በአልትራ ማራቶን በመሮጥ አጠቃላይ ዝግጅቶችን ማድረግን ይጨምራል" ሲል አክሏል።

ኪሩይ በመጨረሻው የኢንስታግራም ልጥፉ ላይ ያለ ተጨማሪ ኦክስጅን ኤቨረስትን መውጣት እንደሚችል ያለውን እምነት ገልጿል።

ነገር ግን አስጎብኝው ናዋንግ ሼርፓ የአደጋ ጊዜ የኦክሲጅን ድጋፍ እና ችግር ካጋጠመው በሚል ደግሞ ለአደጋ ጊዜ የሚያገለግሉ ነገሮች ማዘጋጀቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

ኪሩይ ኬንያ ውስጥ የባንክ ባለሙያ ሆኖ ያገለግል ነበር።

ህልፈተ ህይወቱ በኬንያ የሚገኙ ተራራ ወጪዎችን ክፉኛ አስደንግጧል።

ስለ ኪሩይ ሙከራዎች ወቅታዊ መረጃዎችን ሲያካፍል የነበረው ሌላው ኬንያዊ ተራራማ ወጪ ጀምስ ሙሂያ በኤክስ ላይ "ወንድማችን በተራራው ላይ አርፏል” ሲል ጽፏል።

ሙሂያ ቀደም ሲል በለጠፈው ጽሁፍ ደግሞ በትክክል በመዘጋጀቱ፣ የአካል ብቃት ስላለው፣ ጠንካራ እና በደንብ የሰለጠነ መሆኑን በመጥቀስ ኪሩይን ተራራውን መውጣቱን በስኬት እንዲያጠናቅቅ ተመኝቶ አስፍሮ ነበር።

ባለፈው ዓመት በምናስሉ በተካሄደው ጉባኤ ላይ ኪሩይን ማግኘቱን ለቢቢሲ ተናግሯል።

የኪሩይ ህልፈተ ህይወት በዚህ ሳምንት በኤቨረስት ላይ የተመዘገበ አራተኛው ሞት ነው።

ሮማኒያዊ እና እንግሊዛዊ ተራራ ወጪዎች የኔፓል ዜግነት ካለው አስጎብኚያቸው ጋር ማክሰኞ ዕለት ሞተው መገኘታቸውን ሂማሊያን ታይምስ ዘግቧል።