በማንቸስተር ደርቢ ማን የኤፍኤ ካፕ አሸናፊ ይሆናል?

ማንቸስተር ሲቲ ከማንቸስተር ዩናይትድ

143ኛው የኤፍኤ ካፕ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በዌምብሌይ ስታዲየም ይካሄዳል። ማንቸስተር ሲቲ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ለዋንጫ ይጋጠማሉ።

ዘንድሮስ ማን ያሻንፋል? ባለፈው ዓመት ዋንጫውን ያነሳው ማንቸስተር ሲቲ ወይስ የ12 ጊዜ የክብሩ ባለቤት ማንቸስተር ዩናይትድ?

የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን የዚህን የፍጻሜ ጨዋታ ውጤት ገምቷል።

“በዚህ ጨዋታ ማንም ማንቸስተር ዩናይትድ ሲቲን ያሸንፋል ብሎ አይገምትም። ዩናይትዶች ለማሸነፍ በጣም ይፈልጋሉ። ይህንን የሚያረጋግጥ ግን ምንም አመክንዮ የለም” ብሏል።

ቅዳሜ - ዌምብሌይ ስታዲየም

አምበሉ ብሩኖ ፈርናንዴዝ ለማንቸስተር ዩናይትድ ቁልፍ ተጫዋች ነው። ከዚህ ቀደም ደጋግሜ ብተቸውም ከተጫወቱ ግን ቀያይ ሰይጣኖች የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ላይ ጫና ሊያሳድሩ ይችላሉ።

ዩናይትዶች አቅማቸውን ማሳየት ከቻሉ ማንቸስተር ሲቲን ጉድ ሊያደርጉ የሚችሉ ተጫዋቾች አሏቸው።

ሆኖም ይህ ጨዋታ እንዴት እንደሚሆን ሁላችንም እናውቀዋለን።

ማንቸስተር ዩናይትድ ለማሸነፍ በመልሶ ማጥቃት መጫወት ይኖርበታል።

ከሲቲ ጋር እኩል ኳስ በመያዝ መፎካከርም ይችላሉ።

ጨዋታው ለአሠልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ የመጨረሻው የዩናይትድ ቆይታቸው ሊሆን ይችላል።

አሠልጣኙ በጉዳት ምክንያት በርካታ ተጫዋቾችን በማጣታቸው አዝንላቸዋለሁ። ሆኖም ግን በዚህ ክረምት ቡድኑን የመልቀቅ ዕድላቸው ሰፊ ነው።

የቼልሲ አሠልጣኝ የነበሩት ማውሪሲዮ ፖቸቲኖ መልቀቃቸው አንድ አማራጭ ሆነው ሊቀርቡ ቢችሉም፤ ይህ ጨዋታ ለኤሪክ ቴን ሃግ የመጨረሻው ይመስለኛል።

ማንቸስተር ሲቲ ከማንቸስተር ዩናይትድ

የውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ማንቸስተር ዩናይትድ ከሲቲ ጋር ያለውን ክፍተት ያጠባል ቢባልም ይልቁንም ሰፍቶ በ31 ነጥብ ልዩነት የሊጉን ውድድር አጠናቋል።

ባለፈው ዓመት መሻሻል ያሳዩት ቴን ሃግ፣ ዘንድሮ ወደ ኋላ ተንሸራተዋል።

ዩናይትድ ዋንጫውን ቢያነሳም በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ ነው።

ፔፕ ጋርዲዮላ በሲቲ ቤት ድንቅ ስኬት አስመዝግበዋል።

ኬቨን ደ ብረይን ጉዳት ሲደርስበት ፊል ፎደን ኃላፊነቱን በመውሰድ በየዓመቱ ቡድናቸው የሚያጋጥመውን ፈተና ማለፍ መቻሉን አሳይተዋል።

ሁለቱ ቡድኖች 100 ጊዜ ቢገናኙ ሲቲ 95ቱን ያሸንፋል። ከዚያ በላይ የማሸነፍ አቅምም አለው። ይህን ያህል ነው ልዩነታቸው።

ሌላው ሲቲ እንዲሸነፍ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ከሊጉ ዋንጫ ድል በኋላ ብዙ ተዝናንተው ከሆነ ነው። ነገር ግን የዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመሆኑ ያላቸውን አቅም በሙሉ ለዚህ ጨዋታ እንደሚያውሉት እገምታለሁ።

ሲቲ ከተሸነፈ ከውድድሩ አስደንጋጭ ውጤቶች አንዱ ይሆናል።

ያላቸውን ጠንካራ የሥነ ልቦና የበላይነት ግን እናውቀዋልን።

ይህ የውድድር ዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ ነው። ያውም ከተቀናቃኝ ጋር የሚደረግ ደርቢ። በኤፍኤ ካፕ ብዙ ያልተጠበቁ አስገራሚ ውጤቶችም ተመዝግበዋል።

ልብ ብለን ውጤቱን እንገምት ካልን ግን አንድ አሸናፊ ይኖራል።

ግምት፡ ማንቸስተር ሲቲ 3 – 1 ማንቸስተር ዩናይትድ