ኒውካስል በወዳጅነት ጨዋታ በአውስትራሊያ ሊግ ከዋክብት 8 - 0 ተሸነፈ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኒውካስል በክረምቱ የወዳጅነት ጨዋታ ወደ ሜልበርን ተጉዞ በአውስትራሊያ ሊግ ከዋክብት 8 ለምንም ተሸንፏል።
ረቡዕ ዕለት በሌላ የወዳጅነት ጨዋታ ቶተንሀምን ገጥመው የነበሩት የኒውካስሉ አሰልጣኝ ኤዲ ሀው ወጣት ቡድናቸውን ይዘው ነው ወደሜዳ የገቡት።
ከአውስትራሊያ እና ከኒው ዚላንድ ሊጎች የተውጣጡ ከዋክብትን የገጠሙት የኒውካስል ተጫዋቾች ጫናውን መቋቋም ተስኗቸዋል።
ቤን ኦልድ በአምስተኛው ዲቂቃ የመጀመሪያውን ጎል ሲያስቆጥር ኒኮላስ ሚላኖቪች እና አዳም ታጋርት ሁለት ጎሎች አክለው የመጀመሪያው አጋማሽ 3-0 ተጠናቋል።
አፖስቶሎስ ስታሜትሎፖሎስ ከእረፍት በኋላ ሁለት ጎሎች ሲያስቆጥር ጄክ፣ ጆርዳን እና ቦዢዳር አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች ኒውካስልን ረምርመዋል።
የቀድሞው የኒውካስል እና የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ አለን ሺረር ኒውካስል የሊጉን ውድድር እንደጨረሰ ወደ አውስትራሊያ መጓዙን "እብደት ነው" ሲል ገልፆት ነበር።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የተጠናቀቀው ባለፈው ሳምንት እሑድ ነበር።
አሰልጣኙ ኤዲ ሀው "ወጣት ተጫዋቾቻችን ከባድ ፈተና ነው የገጠማቸው። ምናልባትም የልምድ እጥረት ይሆናል" ብለዋል።
ኤዲ አክለው ልምድ ያላቸውን ተጫዋቾቻውን ያላሰለፉት በጣም ብዙ መንገድ ተጉዘው ስለመጡ እና ረቡዕ ዕለት ተጫውተው ስለነበር እንደሆነ ተናግረዋል።
"ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል። እኛ ደግሞ አሁን ይህንን መጋፈጥ አንችልም" ብለዋል።
አሰልጣኙ የአውስትራሊያና ኒው ዚላንድ ከዋክብት በፈጠሩት ጫና ምክንያት የኒውካስል ታዳጊዎች ብዙ ስህተት እንደሠሩ አምነዋል።
ብሩኖ ጉዊማሬዥ እና ሚጌል አልሚሮን በኮፓ አሜሪካ ዋንጫ ሀገሮቻቸውን ለመወከል ሄደዋል።
ከወጣቶቹ ጎን ከተሰለፉት ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች መካከል የእንግሊዙ ተከላካይ ኪዬራን ትሪፒየር ይጠቀሳል።
ትሪፒየርን ጨምሮ ሉዊስ ሆል እና አሊየት አንደርሰን ከሌሎች ወጣት የኒውካስል ተጫዋቾች ጋር በመሆን መራራውን ሽንፈት ቀምሰዋል።
ኒውካስል በአውስትራሊያ የሚኖረውን አጭር ቆይታ አጠናቆ ወደ ሀገር ቤት የሚመለስ ሲሆን በርካታ ተጫዋቾች በጀርመን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የአውሮፓ ዋንጫ ሀገራቸውን ለመወከል ይሄዳሉ።
የ2024 የአውሮፓ ዋንጫ ሰኔ 7/2016 ይጀመራል። ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ ኮፓ አሜሪካ በአሜሪካ አስተናጋጅነት ይካሄዳል።












