በአፍሪካ ዋንጫ የሚጠበቁ ስድስት ተጫዋቾች እነማን ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ከእሁድ ታኅሣሥ 12 ጀምሮ በሞሮኮ የሚካሄድ ሲሆን የፍፃሜ ጨዋታ ጥር 10 በራባት ይከናወናል።
አዘጋጇ ሞሮኮ ከአውሮፓውያኑ 1976 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዋንጫውን ለማንሳት ትፋለማለች። ሞሐመድ ሳላህ ደግሞ ከሊቨርፑል ጋር የገባውን እሰጥ አገባ ወደኋላ በመተው አገሩ ግብፅን ወክሎ ይጫወታል።
ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ በዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ዐይን የሚጣልባቸው ያላቸውን ስድስት ተጠባቂ ተጫዋቾች መርጧል።
አዘዲን ኡናሂ (የሞሮኮ አማካይ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞሮኮ በዘንድሮው የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች አሽራፍ ሐኪሚ አምበልነት ትመራለች።
የሪያል ማድሪዱ ብራሒም ዲያዝ በማጣሪያ ጨዋታዎች 7 ግቦችን አስቆጥሯል። ነገር ግን በርካታ ሞሮኳዊያን ዐይናቸውን የጣሉበት ወጣቱ አማካይ አዘዲን ኡናሂ ነው።
ከእውቁ ሞሐመድ ስድስተኛ አካዳሚ የወጣው ኡናሂ በ2022 የዓለም ዋንጫ ባሳየው ድንቅ ብቃት ምክንያት የፈረንሳዩን ክለብ ማርሴ ተቀላቅሎ ነበር። ነገር ግን አስደናቂ ብቃቱ መታየት የጀመረው የስፔኑ ጂሮናን ከተቀላቀለ በኋላ ነው።
ሞሮኮ በምድብ ሀ ከኮሞሮስ፣ ከማሊ እና ከዛምቢያ ተደልድላለች። ግብ ጠባቂው ያሲን ቦኑ እና አጥቂው ዮሱፍ ኤን-ናሲሪ ለብሔራዊ ቡድናቸው ወሳኝ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ነገር ግን ሐኪሚ በጉዳት ካልተሰለፈ የእሱን ቦታ ሊተካው የሚችለው ኡናሂ እንደሆነ ይገመታል።
ሞሐመድ አሙራ (የአልጄሪያ አጥቂ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በአፍሪካ በርካታ ግቦች ያስቆጠረው አሙራ ዘንድሮ ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።
የጀርመኑ ዎልፍስበርግ አጥቂ ለአገሩ አልጄሪያ ካለፈው መጋቢት ጀምሮ በስምነት ጨዋታዎች 11 ግቦችን አስቆጥሯል። ሞዛምቢክ ላይ ያስቆጠረው ሀት-ትሪክ የሚረሳ አይደለም።
የ25 ዓመቱ አጥቂ ወቅታዊ አቋሙ አስደናቂ በመሆኑ ለአገሩ መመኪያ እንደሚሆን ይገመታል።
የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት አልጄሪያ በሪያድ ማህሬዝ እየተመራች ወደ ሞሮኮ ታቀናለች። ማህሬዝ እና አሙራ ያላቸው ጥምረትም ውዳሴ ተችሮታል።
ሱዳን፣ ቡርኪና ፋሶ እና ኢኳቶሪያል ጊኒ የአልጄሪያ የምድብ ተቀናቃኞች ሲሆኑ አሙራ ከባድ ፈተና ሊደቅንባቸው እንደሚችል ጠንቅቀው ያውቃታሉ።
ቪክተር ኦሲምሄን (የናይጄሪያ አጥቂ)

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የናይጄሪያ ዕጣ ፈንታ በጋላታሳራዩ አጥቂ ወቅታዊ አቋም ላይ የተመሠረተ ይመስላል።
ናይጄሪያ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ማግኘት ካለባት 15 ነጥብ ያገኘችው 4 ብቻ ነው። በእነዚህ ጨዋታዎች ቪክተር ኦሲምሄን አልተሰለፈም። በዚህም ምክንያት ለ2026 ዓለም ዋንጫ ሳታልፍ ቀርታለች።
ከዲሞክራቲክ ኮንጎ ጋር በነበረው የመጨረሻ የማጣሪያ ፍልሚያ ኦሲምሄን በጨዋታው አጋማሽ ተጎድቶ ወጥቷል። ናይጄሪያም ተሸንፋ ወድቃለች።
የቡድን አጋሩ ፍራንክ አንየካ "ሌላ ደረጃ ላይ የሚገኝ" እያለ የሚልገጸው ኦሲምሄን አገሩ ዋንጫ እንድታነሳ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይጠበቃል።
ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍፃሜው ደርሳ በአይቮሪ ኮስት የተረታችው የሦስት ጊዜ የአህጉሪቱ ዋንጫ አሸናፊዋ ናይጄሪያ በምድብ ድልድሉ ከታንዛኒያ፣ ከኡጋንዳ እና ከቱኒዚያ ጋር ተመድባለች።
ኢብራሒም ምባየ (የሰኔጋል የፊት መስመር ተጫዋች)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የ2021 የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊዎቹ ሴኔጋሎች በሳዲዮ ማኔ እየተመሩ ይፎካከራሉ። የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ከዋክብቱ ኢሊማን ንዲያየ እና ኢስማኢላ ሳር ከማኔ ጋር በመጣመር አስፈሪ የፊት መስመር እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።
ነገር ግን የወደፊቱ የሴኔጋል ተስፋ ተደርጎ የሚቆጠረው ምባየ አስደናቂ ብቃቱን እንደሚያሳይ ይገመታል።
ሴኔጋል በምድብ ማጣሪያው ቦትስዋና፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ እና ቤኒንን ትገጥማለች።
የቀድሞው የፈረንሳይ ወጣት ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹ ምባየ በያዝነው የውድድር ዘመን ለፓሪስ ሳን ዠርማ እየተሰለፈ ይገኛል። ፒኤስጂ በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍልሚያ ባርሴሎናን ሲረታ ተሰልፎ ተጫውቷል።
ምባየ ባለፈው ወር ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ሴኔጋልን ወክሎ የተጫወተው።
ሮጀርስ ማቶ (የኡጋንዳ የፊት መስመር ተጫዋች)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡጋንዳ ከ2019 በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ተመልሳለች።
የፖል ፑት ቡድን በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከልጄሪያ ቀጥላ ሁለተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ሮጀርስ ማቶ በማጣሪያ ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን አስቆጥሯል።
የ22 ዓመቱ የግራ መስመር አጥቂ ባለፈው መስከረም አገሩ ኡጋንዳ ሞዛምቢክን ስትረታ ሁለት ድንቅ ግቦችን ማስቆጠር ችሏል። በሰሜን ሜቂዶኒያ ለቫርዳት የሚጫዋተው ማቶ ለክለቡም ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።
ኡጋንዳ በምድባ ማጣሪያው ከናይጄሪያ፣ ከቱኒዚያ እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ ጎረቤቷ ታንዛኒይ ከባድ ፈተና ይጠብቃታል።
ሬይኒልዶ (የሞዛምቢክ ተከላካይ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሞዛምቢክ ከዚህ ቀደም አምስት ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ ስትሳተፍ አንድም ጊዜ ከምድቧ ማለፍ አልቻለችም።
ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ተጫዋቾች ይዛ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መጥታለች።
ባለፈው ሐምሌ ከአትሌቲኮ ማድሪድ የእንግሊዙን ሰንደርላንድ የተቀላቀለው ሬይኒልዶ አገሩን እየመራ ወደ ሞሮኮ ያቀናል።
የ31 ዓመቱ የግራ መስመር ተከላካይ ለሰንደርላንድ የጀርባ አጥንት መሆኑን እያሳየ ይገኛል። ለአገሩ ሞዛምቢክም ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ብዙዎች ይጠብቃሉ።
ሞዛምቢክ ከባድ ምብድ የምትገኝ ሲሆን ያለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ባለቤት አይቮሪ ኮስት፣ እንዲሁም ለዋንጫው ትልቅ ግምት የተሰጣት ካሜሩን እና ጋቦን የምድብ ተፎካካሪዎቿ ናቸው።















