ፓሪ ሳን ዠርሜይን ለኪሊያን ምባፔ 60 ሚሊዮን ዩሮ እንዲከፍል ፍርድ ቤት ወሰነ

ኪሊያን ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኪሊያን ምባፔ

የፈረንሳዩ እግር ኳስ ቡድን ፓሪ ሳን ዠርሜይን ለታዋቂው አጥቂ ኪሊያን ምባፔ 60 ሚሊዮን ዩሮ እንዲከፍለው አንድ የፓሪስ ፍርድ ቤት ወሰነ።

የተጫዋቹ የቀድሞ ቡድን ላይ ይህ ቅጣት የተጣለበት ለምባፔ ሊከፍለው ይገባ የነበረው ደሞዝ እና ጉርሻን መሠረት አድርጎ ባቀረበው ክስ ነው።

ኮከብ ተጫዋቹ ፓሪ ሳን ዠርሜይን (ፒኤስጂ) 263 ሚሊዮን ዩሮ እንዲከፍለው በመጠየቅ ያቀረበው ክርክር በዋና ከተማዋ ፓሪስ ለሚገኘው የሠራተኞች ጉዳይን ለሚመለከተው ችሎት ባለፈው ኅዳር ወር አቅርቦ ነው ከአሁኑ ውሳኔ ላይ የተደረሰው።

የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮን የሆነው ክለቡ በበኩሉ በተመሳሳይ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አምበል በሆነው ኪሊያን ምባፔ ላይ የ240 ሚሊዮን ዩሮ ክስ አቅርቦ ነበር።

የ26 ዓመቱ የሪያል ማድሪድ ተጫዋች ምባፔ ያልተከፈለውን 55 ሚሊዮን ዩሮን ጨምሮ በሚሊዮን የሚቆጠር የገንዘብ ካሳ የጠየቀው ከቡድኑ ጋር ለገባበት የኮንትራት ውዝግብ እና በክለቡ ተገቢ አያያዝ አልተደረገልኝም በሚል ነው።

ነገር ግን ተጫዋቹ ፍርድ ቤት እንዲያስከፍልለት ከጠየቀው ገንዘብ የበየነለት የተወሰነውን ብቻ ነው።

ችሎቱ ፒኤስጂ ለተጫዋቹ የባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የሚያዝያ፣ የግንቦት እና የሰኔ ወራት ደሞዙን እንዲሁም በስምምነቱ መሠረት ደግሞ መደበኛ እና የፊርማ ጉርሻውን አልከፈለውም ብሏል።

"በችሎቱ ውሳኔ ደስተኞች ነን። ደሞዝ ሳይከፈል ሲቀር የሚከተለው ቅጣት ይህ መሆኑን መጠበቅ ይኖርብናል" ሲሉ የምባፔ ጠበቃ ፍራንክ ካሴሩ በችሎቱ ውሳኔ መርካታቸው ተናግረዋል።

ቡድኑ ፓሪ ሳን ዠርሜይን ተጫዋቹ በ2023 ወደ ሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል ቡድን በ300 ሚሊዮን ዩሮ እንዲዘዋወር ያቀረበለትን ጥያቄ ባለመቀበሉ ካሳ እንዲከፍለው ጥያቄ አቅርቦ ነበር።

ነገር ግን ኪሊያን ምባፔ የቡድኑን ሃሳብ ውድቅ ካደረገ በኋላ በነበረው የዝውውር ጊዜ ወደ ስፔኑ ታላቅ ቡድን ሪያል ማድሪድ በነጻ ዝውውር ማቅናቱ ይታወሳል።