የዓለም ዋንጫን ለመታደም በአንድ ቀን አምስት ሚሊዮን ትኬት መጠየቁን ፊፋ አስታወቀ

ዋንጫ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዓለም ዋንጫን የፍፃሜ ውድድር ለመመልከት የተቀመጠው የትኬት ዋጋ በኳታር ከነበረው በሰባት እጥፍ ይበልጣል

እንደ አውሮፓውያኑ 2026 ለሚካሄደው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ሐሙስ ዕለት በተጀመረው የትኬት ሽያጭ አምስት ሚሊዮን ትኬቶች መጠየቃቸውን የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽን - ፊፋ አስታወቀ።

ይህ የሆነው የትኬት ዋጋው ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች በጨመሩበት ወቅት ነው።

የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው - ፊፋ እንዳለው ሰኔ 27 በኮሎምቢያ እና በፖርቹጋል መካከል በሚያሚ ለሚካሄደው ግጥሚያ ከ200 በላይ አገራት ውስጥ ያሉ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ትኬት ጠይቀዋል።

በሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት በአሜሪካ፣ በካናዳ እና ሜክሲኮ ለሚካሄደው የእግር ኳስ ውድድር የተጠየቀው የትኬት ዋጋ የተተቸ ሲሆን የእግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበርም " ተገቢ ያልሆነ" ብሎታል።

የተወሰኑ ቡድኖች ግጥሚያን ለመመልከት የአንድ ትኬት ዋጋ ከሦስት ዓመት በፊት በኳታር ከነበረው ሦስት እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በጣም ዝቅተኛው 3 ሺህ 119 ፓውንድ (651 ሺህ 768 ብር) ያስወጣል።

የእግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበሩ፣ አባላቱ ፊፋ የትኬቱን ዋጋ እንዲቀንስላቸው እንዲያግባባ ከጠየቁ በኋላ ፌደሬሽኑን አነጋግሯል።

የደጋፊዎች ማኅበሩ ዋጋውን በተመለከተ ከፊፋ ጋር ለመነጋገር የሽያጭ ሂደቱ እንዲቆም ለመጠየቅን በአውሮፓ የእግር ኳስ ደጋፊዎችን ተቀላቅሏል።

" በአውሮፓ ያሉ የእግር ኳስ ደጋፊዎች የትኬት ሽያጭ እንዲቆም ያቀረቡትን ጥሪ እንደግፋለን፤ የእግር ኳስ ማኅበሩ ይህንን ያልተገባ ዋጋ በተመለከተ በቀጥታ ለመገዳደር ከሌሎች ማኅበራት ጋር ለመስራት ጥሪ ያቀርባል" ብሏል በመግለጫው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ሁሉም ብሔራዊ ማኅበራት ከደጋፊዎቻችሁ ጎን እንድትቆሙ ጥሪ እናቀርባለን፤ ያለ እነሱ ሙያዊ ጨዋታ አይኖርም" ብሏል።

ፊፋ እስካሁን በቀረበው ቅሬታ ላይ የሰጠው ምላሽ የለም። የእግር ኳስ ማኅበሩ እንዲሁም የስኮትላንድ የእግር ኳስ ማኅበር በትኬቱ ዋጋ ላይ አስተያየት አልሰጡም።

ሆኖም የእግር ኳስ ማኅበሩ ዋጋው በኢንግላንድ የሚገኙ ደጋፊዎችን እንዳስቆጣ እንደሚያውቅ እና ይህንን ስጋትም ለፊፋ ለማቅረብ ማቀዱን ቢቢሲ ስፖርት ሰምቷል።

በሚቀጥለው ሳምንትም በዶሃ የፊፋ ምክር ቤት ስብሰባ የሚካሄድ ሲሆን የእግር ኳስ ማኅበሩ ሊቀ መንበር ዴቢ ሂዊት በስብሰባው ላይ ይገኛሉ።

ባለፈው ወር ሊቀ መንበሯ ተለዋዋጭ የሆነ የትኬት ዋጋን እንደምትቃወም የገለጸች ሲሆን ዩናይትድ ኪንግደም እና አየርላንድ በሚያዘጋጁት በዩሮ 2028 ይህ እንደማይሆን ቃል ገብታለች።

የአገር ውስጥ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌደሬሽን የ2035ቱን የሴቶች የዓለም ዋንጫ ለማስተናገድ ተስፋ በማድረግ ግዛቶቹ እና ዩኬ መንግሥት ፊፋን ላለማስቆጣት ሊጠነቀቁም ይችላሉ።

የፊፋ የውስጥ ምንጮች እንዳሉት የትኬቱ ዋጋ ለበርካቶች ውድ ቢመስልም፣ የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪው የአሜሪካን የገበያ ዋጋ ከግምት በማስገባት ዋጋ የማውጣት፣ በዓለም ላይ ያሉ ጨዋታዎችን የማሳደግ እና በሚገኘውም ገቢ የወንዶች፣ ሴቶች እና የታዳጊዎች እግር ኳስ የማሳደግ ኃላፊነት አለበት።

የፊፋ ፕሬዚደንት ጊያኒ ኢንፋንቲኖ ከዚህ በፊት ተመዝግቦ የማይታወቅ ከፍተኛ ገቢ ለማግኘት ቃል የገቡ ሲሆን ይህ እጅግ ትርፋማ የሆነው የስፖርት ዝግጅት በ2027 በሚደረገው የፕሬዚዳንትነት ምርጫ የመወዳደር ተስፋቸውን አይጎዳውም።

ይህ በጣም ከፍተኛ የሆነው የትኬት ዋጋ ይፋ የተደረገው ሐሙስ ዕለት ፊፋ ለእያንዳንዱ አገር ለደጋፊ ቡድኖች የትኬት ዋጋ ይፋ ሲያደርግ ነበር።

በኳታር ከሦስት ዓመት በፊት በተካሄደው የዓለም ዋንጫ የምድብ ጨዋታዎች የትኬት ዋጋ ከ68 ፓውንድ (14 ሺህ 209 ብር ) እስከ 219 ፓውንድ (45 ሺህ 763 ብር) ነበር።

ሆኖም በሚጥለው ዓመት ኢንግላንድ ከክሮሽያ እና ስኮትላንድ ከብራዚል በሚያደርጉት ጨዋታ የትኬት ዋጋ ከ198 ( 41 ሺህ 375 ብር) እስከ 523 ፓውንድ (109 ሺህ 289 ብር) ያስወጣል።

ዋጋው በመጨረሻዎቹ ፍልሚያዎች ላይ ይጨምራል።

የትኬቱ ዋጋ ለሁሉም ቡድኖች ለሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች በስታዲየም የመቀመጫ ደረጃዎች 507 ፓውንድ (105 ሺህ 946 ብር) ፣ 757 ፓውንድ (158 ሺህ188 ብር) እና 1 ሺህ 073 ፓውንድ ( 224 ሺህ 221 ብር) የሚያስከፍል ሲሆን ለግማሽ ፍፃሜ ደግሞ 686ፓውንድ (143 ሺህ 351 ብር)፣ 1 ሺህ 819 ፓውንድ (380 ሺህ 111 ብር) እና 2 ሺህ 363 ፓውንድ ( 493 ሺህ 789 ብር) ያስከፍላል።

ለፍፃሜ ውድድር ዝቅተኛው የትኬት ዋጋ 3 ሺህ 119 ፓውንድ ( 651 ሺህ768 ብር) ሲሆን በኳታር ከነበረው ከሰባት እጥፍ በላይ ነው።

ለሕጻናት እና ለሌሎች ቡድኖች የተቀመጠም ቅናሽ የለም።

በመጪው የዓለም ዋንጫ ውድድር ለመጀመሪያ ጊዜ 48 አገራት የሚሳተፉ ሲሆን ከአውሮፓውያኑ ሰኔ 11 እስከ ሐምሌ 19 ድረስ ይካሄዳል።

እስካሁን ኮሎምቢያ ከፖርቹጋል ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ በጣም ተጠባቂው ነው።

ይህም ሰኔ 13 በኒው ጀርሲ ብራዚል ከሞሮኮ፣ ሰኔ 18 በጓዳላጃራ ሜክሲኮ እና ደቡብ ኮሪያ፣ ሰኔ 25 በኒው ጀርሲ ኢኳዶር ከጀርመን እና ሰኔ 24 ስኮትላንድ ከብራዚል ጋር የሚያደርጉት ጨዋታዎችም ቀጥሎ እንደሚካሄድ ፊፋ ገልጿል።

እንደ ፊፋ ከሆነ በርካታ የትኬት ጥያቄዎች የቀረቡት አዘጋጅ ከሆኑት ሦስቱ አገራት ሲሆን ኮሎምቢያ ፣ ኢንግላንድ፣ ኢኳዶር፣ ብራዚል፣ አርጀንቲና፣ ስኮትላንድ፣ ጀርመን፣ አውስትራሊያ ፣ ፈረንሳይ እና ፓናማ ይከተላሉ።