በሕንድ ሊዮኔል ሜሲ 'በአግባቡ ሳናየው ተለየን' ያሉ አድናቂዎች ወንበሮችን እና ጠርሙሶችን ወደ ሜዳ ወረወሩ

ሜሲን ለደቂቃዎች ብቻ አይተውት በመግባቱ የተቆጡ ሕንዳውያን ወንበሮችን እና ጠርሙሶችን ወደ ሜዳው ወርውረዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሊዮኔል ሜሲ በሕንድ በኮልካታ በሚገኘው ሳልት ሌክ የእግር ኳስ ስታዲየም የተገኘው ለ20 ደቂቃ ብቻ ነው

አርጀንቲናዊውን ኮከብ ሊዮኔል ሜሲን ለማየት በሕንድ ኮልካታ በሚገኘው ሳልት ሌክ ስታዲየም ቅዳሜ ዕለት የተሰባሰቡ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች በበርካታ ባለሥልጣኖች እና ታዋቂ ሰዎች ታጅቦ ለደቂቃዎች ከታየ በኋላ በመግባቱ በቁጣ ወንበሮች እና ጠርሙሶች ወደ ሜዳ ወረወሩ።

የሊዮኔል ሜሲ አድናቂዎች እና ደጋፊዎች እርሱን ለደቂቃዎች ለማየት 133 ዶላር ያህል ከፍለዋል።

ደጋፊዎቹ የተቆጡት ሜሲ ወደ ሜዳ ሲመጣ በበርካታ ባለሥልጣናት እና ታዋቂ ሰዎች ታጅቦ በመሆኑ እርሱን በበቂ የማየት ዕድል አላገኘንም በሚል ነው።

የአርጀንቲና እና የኢንተር ማያሚ አጥቂው ሜሲ ለ20 ደቂቃዎች በሜዳው ላይ ከቆየ በኋላ ዙሪያውን በከበቡት ጠባቂዎች ወደ ውስጥ እንዲገባ መደረጉ ደጋፊዎቹን አስቆጥቷል።

የዌስት ቤንጋል አስተዳዳሪ ማማታ ባነርጂ "በተከሰተው ድርጊት በጣም እንደተረበሹና እንደተደናገጡ" ተናግረዋል።

ባነርጂ በስታዲየሙ ውስጥ ለተፈጠረው ሜሲን እና "የስፖርት አፍቃሪዎችን" ይቅርታ ጠይቀዋል።

"የምርመራ ኮሚቴው ስለ ተፈጠረው ዝርዝር ምርመራ ያካሂዳል፣ ኃላፊነቱን ይወጣል እና እንደዚህ ዓይነት ክስተቶችን ወደፊት እንዳይፈጠሩ የሚያስችሉ እርምጃዎችን ይወስዳል" ሲሉ ኃላፊው በኤክስ ገጻቸው ላይ ለጥፈዋል።

የሜሲ ቃል አቀባይ ሜሲ ቀደም ሲል የተስማሙበትን የጊዜ ገደብ ማሟላቱን ተናግረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የዝግጅቱን አደረጃጀት በተመለከተ ባነርጂ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያወጡትን ይቅርታ የሚገልጽ ልጥፍ ለቢቢሲ ጠቅሷል።

አንድ የፖሊስ ባለስልጣን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ይህንን ዝግጅት "በበላይነት ያዘጋጁ አካላት" ምንም ዓይነት ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ ሳይሰጡ በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

ባለሥልጣናቱ አዘጋጆቹ ትኬቶችን ለገዙ ሰዎች ገንዘባቸውን ለመመለስ የሚቻልበትን መንገድ ይመለከታሉ ሲሉም ተናግረዋል።

የመላው ሕንድ እግር ኳስ ፌዴሬሽን (AIFF) በ"ግል በተዘጋጀው በዚህ ዝግጅት" ውስጥ አለመሳተፉን ይፋ አድርጓል።

ሜሲ በሕንድ የተገኘው በኮልካታ፣ ሃይደራባድ፣ ሙምባይ እና ዴልሂ ውስጥ ለሚካሄዱ "የምንጊዜም ታላቅ ጉዞ" የማስተዋወቂያ ዝግጅቶች ላይ ለመሳተፍ ነው።

ጉብኝቱ የጀመረው በኮልካታ ውስጥ በ27 ቀናት ውስጥ በ45 ሰዎች የተገጣጠመውን እና 21 ሜትር ርዝመት ያለው ሐውልት በመመረቅ ነው።

ሜሲ በደኅንነት ስጋት ምክንያት የምረቃ ሥነ ስርዓቱን በቪዲዮ ታድሟል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቹ የእግር ኳስ ተጫዋቹን በአካል የማየት ዕድል ለማግኘት ወደ ከተማዋ ስታዲየም ተጉዘዋል።

እነዚህ ደጋፊዎች ማሊያውን ለብሰው፣ እየዘመሩ እና እየጨፈሩ "ሜሲን እወደዋለሁ" የሚል ጭንቅላት ላይ የሚታሰር ጨርቅ አድርገው ነበር።

ሜሲ መጀመሪያ ላይ ለደጋፊዎቹ እጁን እያወዛወዘ ወደ ስታዲየሙ መጣ።

ነገር ግን ይህ የሜሲ የስታዲየም ቆይታ በድንገት ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አንዳንድ የተበሳጩ ደጋፊዎች ወደ ሜዳው ዘልለው በመግባት ባነሮችንና ድንኳኖችን ቀዳደዋል።

ሌሎች ደግሞ የፕላስቲክ ወንበሮችንና የውሃ ጠርሙሶችን ወደ ሜዳው ወርውረዋል።

የ2022ቱ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ፣ ከእግር ኳስ ታላላቅ ተጫዋቾች አንዱ እንደሆነ የሚታሰበው ሜሲን በስታዲየሙ አጭር ጨዋታ እንደሚጫወት እና ኳስ እንደሚያንጠባጥብ ተጠብቆ ነበር ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሊዮኔል ሜሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በርካታ ቁጥር ያላቸው አድናቂዎቹ በተሰበሰቡበት ስታዲየም ቢገኝም በርካታ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች ከበውት ስለነበር አድናቂዎቹ እሱ ለማየት ሳይችሉ ቀርተዋል

"ሜሲን የከበቡት ፖለቲከኞች እና ተዋናዮች ብቻ ነበሩ. . . ታዲያ ለምን ጠሩን? የ12,000 ሩፒ ቲኬት ገዝተናል፤ ነገር ግን ፊቱን እንኳን ማየት አልቻልንም" ሲል በስታዲየሙ ውስጥ የነበረ አንድ ደጋፊ ለሕንድ የዜና ወኪል አኒ ተናግሯል።

አንድ የተናደደ ደጋፊ ደግሞ ለፕሬስ ትረስት ኦፍ ኢንዲያ የዜና ወኪል እንደተናገረው ሊዮኔል ሜሲን ለማየት ሰዎች የአንድ ወር ደመወዛቸውን ያህል ከፍለዋል።

"ለቲኬቱ 5,000 ሩፒ ከፍዬ ከልጄ ጋር የመጣሁት ሜሲን ለመመልከት እንጂ ፖለቲከኞችን ለማየት አይደለም" ብሏል።

"የፖሊስና የጦር ኃይሎች አባላት ከእርሱ ጋር ፎቶ ይነሱ ነበር፣ እናም አስተዳደሩ ተጠያቂ ነው።"

ሜሲ በዚህ የአጭር ጊዜ ጉብኝቱ የኢንተር ማያሚ የቡድን አጋሩ እና የኡራጓይ ኮከብ ሉዊስ ሱዋሬዝ እና የአርጀንቲናው ሮድሪጎ ዴ ፖል አጅበውታል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው የቦሊውድ ተዋናይ ሻህ ሩክ ካንም ቀደም ብሎ ሜሲን አግኝቶታል።

ኮልካታ የሕንድ ግዛት የምዕራብ ቤንጋል ዋና ከተማ ስትሆን የክሪኬት አፍቃሪ በሆነች አገር ውስጥ በርካታ የእግር ኳስ ደጋፊዎች ይገኙባታል።

በከተማ ውስጥ የአካባቢው እግር ኳስ ቡድኖች ሲጫወቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በስታዲየሞች ውስጥ ተሰብስበው ማየት የተለመደ ነው።

ቅዳሜ ማለዳ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሜሲ ባረፈበት ሆቴሉ አካባቢ እርሱን ለማየት በመፈለግ በመንገድ ላይ ተሰልፈው ነበር።

የ24 ዓመቱ የኮርፖሬት ጠበቃ ሂቴሽ ከደቡብ ሕንድ ከተማ ቤንጋሉሩ ወደ 1,900 ኪሎ ሜትር ርቀት በአውሮፕላን የመጣው ሜሲን ለማየት ነው።

"ለእኔ የግል ጉዳይ ነው።በጣም አጭር ነኝ እና ከጓደኞቼ ጋር እግር ኳስ መጫወት እወዳለሁ" ሲል ሂቴሽ ከሐውልቱ ፊት ለፊት ቆሞ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ሜሲ በጣም ቅርቤ የሆነ ተጫዋች ነው፤ ማንም ሰው የእርሱን ተሰጥኦ ሊፎካከር አይችልም። በችሎታ ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደሚቻል ተስፋ የሰጠኝ እርሱ ነው።"