ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች የሚታወቁበት ማራቶን በአየር ንብረት ምክንያት ክብረ ወሰን ለመስበር አዳጋች ይሆናል ተባለ

ትዕግሥት አሠፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአየር ንብረት ለውጥ አትሌቶች የማራቶን ክብረ ወሰኖችን የመስበር ዕድላቸውን እየቀነሰ ነው ሲል አዲስ ጥናት ይፋ አደረገ።

ጥናቱ​ የተካሄደው በአሜሪካ በሚገኘው ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት፣ ክላይሜት ሴንትራል ሲሆን የአየር ሙቀት መጨመር "በአንዳንድ ውድድሮች ክብረ ወሰንን ለመስበር የሚካሄዱ ሩጫዎችን የማይቻል አድርጓቸዋል" ብሏል።

እአአ በ2045 ከ221 የዓለም ማራቶን ውድድሮች 86 በመቶው ያህሉ ለመሮጥ የሚያስችል ምርጥ የአየር ንብረት አይኖራቸውም ብሏል።

ይህም ለወንዶች 4 ዲግሪ ሴንቲግሬድ፣ ለሴቶች ደግሞ 10 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ማለት ነው።

የበርሊን ማራቶን በመስከረም ወር ላይ ወቅቱን ባልጠበቀ የ24 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት የተካሄደ ሲሆን፣ ከሰባቱ የዓለም ዋና የማራቶን ውድድሮች መካከል በሆኑት ቶኪዮ እና ለንደን እንዲሁ በመጋቢት እና በሚያዝያ ወር ከ20 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ በሆነ የሙቀት ውስጥ ተካሂደዋል።

የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዝዳንት ሴባስቲያን ባለፈው ወር እንደተናገሩት አትሌቶችን ከአደጋ ለመጠበቅ እንደ ማራቶን ያሉ ጽናትን የሚጠይቁ ውድድሮች በተናጥል፣ እንደ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባሉ ውድድሮች፣ በዓመቱ በተለያየ ጊዜ ሊደረጉ ሳይገባቸው አይቀርም ብለዋል።

ክላይሜት ሴንትራል ላካሄደው ጥናት ምላሽ ሲሰጡ "ለአትሌቲክስ እና ለሌሎች የበጋ እና የክረምት ስፖርቶች 'በተለመደው መልኩ መቀጠል' የሚባለው ዘመን አብቅቷል" ብለዋል።

"የሙቀት መጨመር፣ የባህሮች ከፍታ መጨመር እና ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ከአሁን በኋላ የተለዩ ክስተቶች አይደሉም፤ አዲሱ መደበኛ እውነታችን ናቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"በዓለም አትሌቲክስ የአትሌቶች ደህንነት ስልጠና እና ታክቲክ ብቻ ሳይሆን ለሞቃታማ ፕላኔት ምላሽ መስጠት እንደሆነ እንገነዘባለን።

"ስፖርታችን ወደፊት እንዲጎለብት ከተፈለገ መምራት፣ ማላመድ እና ማሳደግ አለብን፤ ይህ ማለት ደግሞ አሁን ደፋር እርምጃ መውሰድ ማለት ነው።"

እአአ በ2024 የለንደን ማራቶን ፈጣኗ ብሪታኒያዊት ሴት አሸናፊ ምሂሪ ማክሌናን "በታዋቂ አትሌቶች ዘንድ ውድድሮች የማሸነፍ ወይንም ወድቆ የመቅረት ይሆናሉ።

"በየዕለቱ ለዓመታት ልምምድ እንሰራለን እና ሁሉንም የሕይወታችንን መስመር የምንመራው በምርጥ ብቃት ለመሮጥ ነው። ይህ በጣም አስቸጋሪው ግብ ጥሩ የአየር ሁኔታ እየቀነሰ ሲመጣ ከዓይናችን ስር ርቆ ይሄዳል።

"የአየር ንብረት ለውጥ ውድድሩ እየጠነከረ እንዲሄድ ማድረግ ብቻ አይደለም፤ አየሩ እየሞቀ ሲሄድ ክብረ ወሰን መስበር የማይደረስበት መሆኑንም ማወቅ ነው።"

ጥናቱ በቶኪዮ ለስመጥር ወንድ ሯጮች (69%) ከፍተኛው የሙቀት መጠን የመታየት ዕድል እንዳለው ሲያስቀምጥ፣ ነገር ግን በ2045 እጅግ በጣም ከፍተኛ ቅናሽ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስፍሯል።

የሁለት ሰዓት ከ35 ሰከንድ የወንዶች የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን የተያዘው በ2023 በቺካጎ በሟቹ ኬልቪን ኪፕተም ነው።

ኬንያዊቷ ሩት ቼፕንጌቲች ምንም እንኳን ባለፈው ሳምንት የፀረ አበረታች ቅመሞች ሕግ ጥሰት ፈፅማለች በሚል ለሦስት ዓመታት ብትታገድም በ2024 በቺካጎ የሴቶችን የዓለም ክብረ ወሰን በእጇ አስገብታለች።

ባለፉት ሰባት ዓመታት የወንዶች ክብረ ወሰን በሁለት ደቂቃ ከ22 ሰከንድ የቀነሰ ሲሆን፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉ በአዲስ የጫማ ቴክኖሎጂ ምክንያት ነው ተብሏል።

የቀድሞዋ የሴቶች የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ካትሪን ንደረባ "የአየር ንብረት ለውጥ የማራቶን ውድድርን ለውጦታል።

"ከፍተኛ የውሃ መጠማት እውነተኛ አደጋ ነው፤ እና ቀላል ስህትት የሆኑ ስሌቶች ውድድሩ ከመጀመሩ በፊት ሊያስቆሙ ይችላሉ። እያንዳንዱ እርምጃ አሁን መልእክት ያስተላልፋል። መሬታችንን ካልተንከባከብን የእኛ ጠንካራ እርምጃዎች እንኳን በቂ አይሆኑም።"

በኒውዮርክ እና በቦስተን ማራቶን ያሸነፈው ኢብራሂም ሁሴን "የአየር ንብረቱ አሁን የውድድሩ አካል ነው።

"ካልተከላከልነው፣ የወደፊቱን ክብረ ወሰኖች እና የሚገኙ ደስታዎች እየቀነሱ ይሄዳሉ" ብሏል