"ወርቅ አጣሁ ብዬ ማሰብ አልፈልግም" - አትሌት ትዕግሥት አሠፋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጃፓን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን የብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው አትሌት ትዕግሥት አሰፋ ወርቅ አጣሁ ብዬ ማሰብ አልፈልግም አለች።
በ20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሴቶች ማራቶን ውድድር አትሌት ትዕግሥት አሰፋ 2ኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቋን ተከትሎ ለዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረገጽ በሰጠችው አስተያት ነው ይህንን የተናገረችው።
አትሌት ትዕግስት ከኬንያዊቷ አትሌት ፔሬስ ጂፕችርችር ጋር ብርቱ ፉክክር አድርጋ ነው የብር ሜዳሊያ ለአገሯ ያስገኘችው።
በሴቶች ብቻ የማራቶን የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቷ ትዕግሥት አሰፋ ርቀቱን ለማጠናቀቅ 2 ሰዓት 24 ደቂቃ ከ45 ሰከንድ ወስዶባታል።
አትሌት ትዕግሥት እና ጂፕቺርቺር በጃፓን ብሔራዊ ስታዲየም ትከሻ ለትከሻ ተያይዘው የገቡ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹን 100 ሜትሮች ኬንያዊቷ አትሌት ኃይሏን በመጨመር ቀዳሚ መሆን ችላለች።
ኬንያዊቷ ጂፕቺርቺር በሁለት ሰከንድ በመቅደም 2:24:43 በሆነ ሰዓት በመግባት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን ችላለች።
ጂፕቺርቺር "አሸንፋለሁ ብዬ አላሸነፍኩም ነበር" ያለች ሲሆን ከቶኪዮ በፊት ዓመቱን በሙሉ የማራቶን ውድድር አለማድረጓ ተጠቅሷል።
"ነገር ግን ከውድድሩ ማብቂያ መስመር 100 ሜትር ርቀት ላይ መሆኔን ስመለከት ፍጥኔቴን ጨመርኩ። የሆነ ድብቅ አቅም አገኘሁ" ስትል የነበረውን ሁኔታ ገልጻዋለች።
ትዕግሥት ባለፈው ዓመት በለንደን በጂፕቺርቺር ተይዞ የነበረውን የሴቶች ብቻ ክብረ ወሰን 2:15:50 በመግባት ሰብራው ነበር።
"ወርቅ እንዳጣሁ አንዲሰማኝ አልፈልግም" ያለችው ትዕግሥት "ባለፈው ዓመት በለንደን የዓለምን ክብረ ወሰን ከሰበርኩ በኋላ ረዥም እረፍት በመውሰዴ ለቶኪዮ በምዘጋጅበት ወቅት ችግሮች ነበሩብኝ። ስለዚህ ውድድሩን በብር ሜዳሊያ በመጨረሴ ደስተኛ ነኝ" ብላለች።
ትዕግሥት ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በለንደን በተደረገ የማራቶን ውድድር ላይ ሴቶች ብቻ በተሳተፉበት የማራቶን ውድድርን ክብረ ወሰንን ለግማሽ ደቂቃ በቀረበ ጊዜ ለማሻሻል ችላለች።
በፓሪስ ኦሊምፒክ ላይ ከኔዘርላንዳዊቷ ሲፈን ሐሰን ጋር እስከ መጨረሻው ድረስ ተፎካክራ ሁለተኛ በመሆን የኦሊምፒክ ብር ሜዳሊያ አሸናፊ የሆነችው ትዕግሥት በለንደን ማራቶን አሸናፊ የሆነችው ውድድሩን ከአራት ዓመት በፊት ያሸነፈችውን ኬንያዊቷን ጆይስሊን ጄፕኮስጌይን አስር ኪሎ ሜትር እየቀራት በሰፊ ልዩነት ርቃት በመምራት ነበር።
ውድድሩን ስታጠናቅቅም ሁለት ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከ50 ሰከንድ የሆነ ጊዜን አስመዝግባለች።















